ፈርጉሰን ‹ወጣቶቼን አትንኩብኝ› ይላሉ
On Thursday, January 5, 2012 08:37 AM.
በስዊዘርላንድ የሜዳው ጠርዝ ላይ ሲቁነጠነጡ የታዩት ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ወደ ሜዳ ያስገቡት ጠንካራውን ቡድናቸውን እንደሆነ አልተጠራጠሩም፡፡ ሆኖም ተጨዋቾቻቸው በጨዋታው የአቻነቷን ጎል ማስቆጠር ሲሳናቸው ተመልክተው ዳኒ ዌልቤክን አስገቡት፡፡ ይሄም አላረካቸውም፡፡ ፌዴሪኮ ማኬዳን አከሉ፡፡ ጣልያናዊውም የግቡን አግዳሚ የለተመች ኳስ ከመሞከር በላይ አላገዛቸውም፡፡ አሰልጣኙ እንዲሁ እንዳማጡ ጨዋታው አለቀ፡፡ ባለፉት አራት ዓመታት በቻምፒየንስ ሊግ የሶስት ጊዜ የፍፃሜ ተፋላሚው ቡድናቸው ተሸነፈ፡፡ ምን መሸነፍ ብቻ ከውድድሩ በጊዜ ተሰናበተ፡፡ ለዚያውም በባስል ተረትቶ፡፡ ለፈርጉሰን የሴንት ጃኮብ ፓርክ ሽንፈታቸው ትርጉሙ ብዙ ነው፡፡ በዚያው ሳምንት በአምስተርዳም አሬና እና በኑካምፕ የተፈጠረውን ልብ ብለው ከተመለከቱ ደግሞ የቡድናቸው በትንሹ ባስል የመሸነፍ ትርጉም ይበልጥ ይጋነንባቸዋል፡፡ ረቡዕ ምሽት የሆነው ነገር ‹‹በእርግጥ ማንቸስተር ዩናይትድ በድጋሚ በአውሮፓ መንገስ ይችላል?›› ያስብላል፡፡ ከአያክሱ ጨዋታ በፊት 14 ተከታታይ ጨዋታ ያሸነፉት ጆዜ ሞውሪንሆ ወደ ቀጣዩ ዙር ማለፋቸውን አስቀድመው በማረጋገጣቸው የሆላንድን ሻምፒዮን የገጠሙት በተቀያሪ ተጨዋቾቻቸው ነው፡፡ በላሊጋ ስፖርቲንግ ሂሆንን 3-0 ካሸነፈው የሪያል ማድሪድ 11 ተሰላፊዎች ውስጥ የሆላንዱን ሻምፒዮን ለመግጠም በአምስተርዳም አሬና የቀረቡት ሁለት ተጨዋቾች ብቻ ናቸው፡፡ አራት ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮኖቹ አያክሶች ወደቀጣዩ ዙር ለማለፍ እድሉ ቢኖራቸውም አልቻሉም፡፡ ዋና ተጨዋቾቹን ባሳረፈው ሪያል በሜዳቸው ተሸነፉ፡፡ የአያክስ እና ሪያል ጨዋታ ከመደረጉ 24 ሰዓታት በፊት ፔፕ ጋርዲዮላም ተመሳሳይ ውሳኔ አሳልፏል፡፡ በዕድሜያቸው ያልጠገቡትን የተጠባባቂ ቡድን ተጨዋቾች አቀረበ፡፡ አላሳፈሩትም እንደ ዋናው ቡድን ተጫውተው ባቴቦሪሶቭን 4-0 አቀመሱት፡፡ ፈርጉሰን ለመጨረሻ ጊዜ ተጠባባቂ ተጫዋቾቻቸውን የተጠቀሙበትን ጊዜ እናስታውስ፡፡ በጣም በቅርቡ ክሪስታል ፓላስን ሊገጥሙ ሞክረውታል፡፡ ውጤቱ ግን አስደንጋጭ ነበር፡፡ ዩናይትድ በግዙፉ ኦልድ ትራፎርድ በሻምፒዮን ሺፑ ቡድን ተሸንፎ ከካርሊንግካፑ ተሰናበተ፡፡ ሽንፈቱ አስደንጋጭ የሚሆነው የተጋጣሚውን ማንነት በሚገባ ከተረዳን ነው፡፡ ከሪስታል ፓላስ ወደ ኦልድ ትራፎርድ ከመምጣቱ በፊት ለስምንት ሙሉ ሰዓታት ያህል አንድ ጎል እንኳን ማስቆጠር የተሳነው ነበር፡፡ በኦልድትራፎርድ ግን ጎል ማግባት ብቻ ሳይሆን በአሳማኝ መልኩ አሸነፈ፡፡ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ የዩናይትድ ዋነኛ ተፎካካሪ ማንቸስተር ሲቲ እንመልከት፡፡ ሮቤርቶ ማንቺኒ ለመጨረሻ ጊዜ ከዋነኛ ተመራጭ 11 ተጨዋቾቹ ብዙዎቹን ሳይዝ ወደ ሜዳ የገባው በኢምሬትስ አርሰናልን ሲገጥም ነው፡፡ የኢትላንዱ ክለብ በጨዋታው በአርሰን ቬንገር ወጣቶች ብልጫ ቢወሰድበትም አሸንፎ ከመውጣት አልተገታም፡፡ የሲቲ ዋና ቡድን ግን ከዩናይትድ ዋና ቡድን ጋር ተገናኝቶ የተፈጠረውን ሁላችንም
ተመልክተነዋል፡፡ ፈርጉሰን ዘንድሮ በውድድር ዘመኑ መጀመሪያ በውጤታማነቱ ሁሉንም ያስገረመውን ቡድን ያዘጋጁት ከላይ ተጠቀሱትን ባርሴሎና፣ ሪያል ማድሪድ፣ ማንቸስተር ሲቲ እና ሌሎችን የምር ለመፎካከር ነበር፡፡ በእርግጥ በፕሪሚየር ሊግ አሁንም የፈርጊ ቡድን ከዋንጫ ፉክክሩ አልወጣም፡፡ ዎልቭስን 4-1 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፎ ሩጫውን አጠናክሯል፡፡ ችግሩ የሚመጣው ቡድኑ ከእነባርሴሎና እና ሪያል ጋር ሲተያይ ነው፡፡ ከኤል ክላሲኮው ግጥሚያ በፊት በቬንገር ‹‹የወቅቱ የዓለማችን ጠንካራ ቡድኖች›› የተሰኙት የስፔን ክለቦች በቡድን ስብስብም ሆነ ጥልቀት ዩናይትድን ያስከነዱታል ቢባል ትክክል ይሆናል፡፡ ይህ ሁሉ ማለት ግን ማንቸስተር ዩናይትድ ‹‹ተንኮታኩቷል›› የሚል ድምዳሜ ላይ አያደርስም፡፡ እንዲህም ሆኖ ፈርጉሰን ዋንጫ ሊያነሱ ይችላሉ፡፡ ዩናይትድ ከአስቸጋሪ ወቅቶች በቶሎ የማገገም ባህል እንዳለው ማንም ሊዘነጋ አይችልም፡፡ ሆኖም ቡድኑ ያገግማል እንጂ ከእነ ባርሴሎና ጋር ተፎካክሮ የአውሮፓ የበላይነቱን በእጁ ያስገባል ማለት ያስቸግራል፤ ቢያንስ ለጊዜው፡፡ አሁን ዩናይትድ በመካከለኛ ደረጃ የሚገኝ ቡድን መስሏል፡፡ በተደጋጋሚ ለፍፃሜ የበቃበትን ቻምፒዮንስ ሊግ ተለይቶ የዩሮፓ ሊግ ተወዳዳሪ ሆኗል፡፡ ይህ ምን ማለት እንደሆነ ከቀይ ሰይጣናቱ ከዋክብት መረዳት ይቻላል፡፡ ከባስሉ ሽንፈት በኋላ በምሽቱ የትኛውም የዩናይትድ ተጨዋች ለሚዲያ ቃሉን ለመስጠት አልደፈረም፡፡ አንድ የእግርኳስ ፀሐፊ እንዲያውም ‹‹የወቅቱ የአውሮፓ ቀዝቃዛ አየር በስዊዘርላንድ የዩናይትድ መልበሻ ክፍል ይበረታል›› ሲል ስሜቱን ገልጿል፡፡ ስሜቱን በይፋ ለመናገር ከፉልባኩ ፓትሪስ ኤቭራ የፈጠነ የለም፡፡ ‹‹በዩሮፓ ሊግ መገኘት በራሱ ያሳፍራል፡፡ ለዚህ ራሴን አላዘጋጀሁም›› ሲል ሀዘኑን ገለፀ፡፡ ፈረንሳዊው ለ‹‹ትንሹ›› ውድድር ራሱን አላዘጋጀም ይሆናል፡፡ ሆኖም ወጣቶችን በደባለቀው ዩናይትድ አንጋፋ ሆነው ጥሩ ጥቃት ካላሳዩት ተጫዋቾች አንዱ ነው፡፡ ክለቡ ወደ ተከታዩ ዙር ለማለፍ አቻ ውጤት ብቻ እንደሚበቃው አውቆ የተጠቀመባቸው ተመራጭ ተጨዋቾቹ ምንም አልፈየዱለትም፡፡ አሁን ባለፉት ሁለት ዓመታት ሲነሳ የነበረው ጥያቄ ተመልሶ መጥቷል፡፡ ፈርጉሰን ታላላቅ ተጨዋቾችን ሊያስፈርሙ ይገባል፡፡
የተጨዋቾች ጥራት ብዙዎቹ የእግርኳስ ተንታዮች የወቅቱ የዩናይትድ ችግር የወኔ እና ተነሳሽነት ማጣት አለመሆኑን ይናገራሉ፡፡ ፈርጊ ጥራት ያላቸው ተጨዋቾችን በግዢ ሊያመጡ ይገባል ሲሉ ይከራከራሉ፡፡ የሪያን ጊግስ አስተዋፅኦ እጅግ ወርዷል፡፡ ፖል ስኮልስ በጭራሽ አልተተካም፡፡ ማይክል ካሪክ፣ አንደርሰን እና ዳረን ፍሌቸር ጥሩ ተጨዋቾች ናቸው፡፡ ቡድኑ አሁን ‹‹ጥሩ›› ብቻ ሳይሆን ‹‹ልዩ›› ከዋክብት አስፈልገውታል፡፡ በተለይ ፈርጉሰን ክችች ያሉበት የአማካይ መስመር ዘንድሮ ይበልጥ ተጋልጿል፡፡ እርሳቸውም ችግሩ ሲጠናባቸው ዌይን ሩኒን ሆልዲንግ ሚድፊልደር አድርገው እስከመጠቀም ደርሰዋል፡፡ አሁን ቡድኑ ሁነኛ የአጥቂ አማካይ እንደሚያስፈልገው ሁሉም እርግጠኛ ሆኗል፡፡ በዌስሊ ሽናይደር ወይም ባስቲያን ስዌይንስታይገር ደረጃ የሚገኝ ድንቅ የጨዋታ አቀናባሪ ያሻዋል፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በዳረን ፍሌቸር ላይ የተስተዋለው የዕድገት መገታት ዘንድሮ በአንቴኒዮ ቫሌንሲያ፣ ጂ ሱንግ ፓርክ እና ማይክል ካሪክ ላይ መታየት ጀምሯል፡፡ በጅምሩ ምርጥ ብቃት ሲያሳይ የነበረው አሽሊ ያንግ ጥሩ የሚሆነው ቡድኑ ጥሩ ሲሆን ብቻ እየመሰለበት ነው፡፡ የአሰልጣኙን ራስ ምታት የሚያበረታው ተጨማሪ ጭንቀት የአምበሉ ኒማኒያ ቪዲች ለረጅም ጊዜ (እስከ ውድድር ዘመኑ መጨረሻ) ከሜዳ መራቅ ነው፡፡ ሰርቢያዊው ምርጥ ተጨዋች ብቻ ሳይሆን የከፍተኛ ልምድ ባለቤትም ነው፡፡ ኤድዊን ቫን ደር ሳር እና ስኮልስን ላጣው ቡድን የቪዲች ጉዳት ተፅዕኖው ብዙ ነው፡፡ ቪዲች ሜዳ ላይ ሲኖር እና ሳይኖር ዩናይትድ ይለያል፡፡ የመሀል ተከላካይ ቡድኑን ከኋላ መስመር አስተማማኝ ሲያደርገው የአንድነት መንፈሱንም ይጨምርለታል፡፡ ፊል ጆንስ እና ክሪስ ስሞሊንግን የመሳሰሉ ወጣቶችን በዋና ተሰላፊነት በያዘው የኋላ መስመር ቪዲች ጥቅሙ ብዙ ነው፡፡ እንዲህ አይነት ተጨዋቾችን በጃንዋሪ ዝውውር ማግኘት ከባድ መሆኑ ደግሞ ችግሩን ያከፈዋል፡፡ ምክንያቱም በቪዲች ደረጃ የሚገኙ ተጨዋቾች በትልቅ ክለብ ምናልባትም በቻምፒየንስ ሊግ እየተወዳደሩ ሊሆን ስለሚችል እነርሱን ማስኮብለል ያስቸግራል፡፡ ቪዲች እና ኤቭራ ለዩናይትድ ፊርማቸውን ያኖሩት በጃንዋሪ ቢሆንም ለመደላደል ጊዜ አስፈልጓቸዋል፡፡ ዩናይትድ አሁን የሚፈልገው ጊዜ የሚያስፈልገው ተጨዋች አይደለም፡፡ ፈርጉሰንም በዚህ ሀሳብ ይስማማሉ፡፡ ‹‹ምርጥ ተጨዋቾችን በጃንዋሪ ማግኘት ከባድ ነው›› ይላሉ፡፡
ወጣቶቹ ተጨዋቾች ሌላኛው የኦልድ ትራፎርድ ታዳሚዎች ስጋት ግብ ጠባቂ ነው፡፡ ዴቪድ ደ ሂያ የወደፊቱ ታላቅ በረኛ ለመሆን ተስፋ አለው፡፡ በቃ ይኸው ነው፡፡ ተስፈኛ ነው፡፡ ተስፈኛ በረኞች ደግሞ አስደናቂ ኳሶችን እንደ ሚያድኑት ሁሉ ስህተቶችንም ደጋግመው ይፈፅማሉ፡፡ ታላላቅ ክለቦች ባለተሰጥኦ ተስፈኛ በረኛ ከያዙ ሌላ ለወጣቱ ልምዱን የሚያካፍል አንጋፋ ግብ ጠባቂም ይኖራቸዋል፡፡ በዩናይትድ ከደሂያ በመቀጠል የሚጠቀሰው በትልቅ ሊግ የመጫወት ብዙ ልምድ የሌለው አንድሬስ ሊንደጋርድ ነው፡፡ የቀድሞው የዩናይትድ አማካይ ሮይ ኪን በቡድኑ የሚገኙት ወጣቶች ያለጊዜያቸው ተጋንኖ እንደተወራላቸው ያምናል፡፡ ከዚህ ቀደም በቡድኑ ተጨዋቾች ላይ የሰላ ትችትን ሰንዝሮ ከፈርጉሰን ጋር ግጭት ውስጥ የገባው አየርላንዳዊ ዩናይትድ በባስል ሲሸነፍም ዝም አላለም፡፡ በውድድር ዘመኑ መጀመሪያ ስለ አዳዲሶቹ ተጨዋቾች ከተባለው በተቃራኒ እውነቱ አሁን እንደተገለጠ ጠቁሟል፡፡ በእርግጥ ዘንድሮ ከጅምሩ በተጋጣሚዎቹ ላይ ጎሎች ሲያዘንብ የነበረው ቡድን አሁን ሌላ መስሏል፡፡ ተቀናቃኙ አርሰናልን 8-2 የረታበት ውጤት የቅርብ ጊዜ ታሪክ አይመስልም፡፡ የባርሴሎናን ሀያልነት ሊነጥቁ የታጩት ወጣቶች ከመካከላቸው ቶም ክሌቨርሲን ብቻ አጥተው ለሳምንታት ወደ ወጥ ብቃት መመለስ ቸግሯቸዋል፡፡ በተከበረው ኦልድ ትራፎርድ በሲቲ 6-1 ተሸንፈው ደጋፊያቸውን አሳፍረዋል፡፡ የዚህ ውጤት ቁስል ጨርሶ ሳይሽርላቸው በቻምፒየንስ ሊግ ከደካማው ምድብ ማለፍ አቅቷቸዋል፡፡ ዩናይትድ በምድቡ ማሸነፍ የቻለው ኦቴሉል ጋላቲን ብቻ ነው፡፡ የሮማኒያው ክለብ በምድቡ ስድስቱንም ጨዋታዎች የተሸነፈ የደካሞች ደካማ ነው፡፡ ፈርጉሰን በቡድናቸው የሲዊዘርላንድ አቋም ባይደሰቱም ወጣቶቹ ሲተቹባቸው ይበልጥ ይከፋቸዋል፡፡ የኪንን ትችት ሲሰሙ ‹‹እርሱ ራሱ የማሰልጠን ዕድል አግኝቶ ፈተናውን አይቶታል›› ሲሉ የቀድሞ አምበላቸውን በነገር ወግተውታል፡፡ አክለውም ‹‹ማንም ሰው ቢሆን ትችት ሲወረድበት አይደሰትም፡፡ ከዚህ ቀደምም እንደተናገርኩት ሁለት ጨዋታዎች ከተሸነፋችሁ ሰዎች ይነዘንዟችኋል፡፡ እኛ ምን እየሰራን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ በቡድናችን ብቁ ተጨዋቾችን ይዘናል፡፡ ሁልጊዜም ለመሻሻል እንተጋለን፡፡ እንከን አልባ ለመሆን እንፈልጋለን፡፡ ሆኖም ፍፁማን መሆን አንችልም፡፡ ዘወትር መጣር እና መታገል ወደግባችን ያደርሰናል፡፡ ክለባችን እየሰራ ያለውም ይሄንኑ ነው›› ሲሉ እየደረሰባቸው ያለው ወቀሳ መጋነኑን ይገልፃሉ፡፡ የባስሉ ሽንፈት ብቻ ቡድኑን ለሞራል ውድቀት ሲዳርግ ክለቡን ምናልባትም እስከ 20 ሚሊዮን ፓውንድ ሊያሳጣው ይችላል፡፡ ፈርጊ ግን ማንም ሰው በወጣት ተጨዋቾቻቸው ላይ ክፉ እንዲናገር አይፈልጉም፡፡ ዩናይትድን ጣጣ ውስጥ በከተተው የሳምንቱ አጋማሽ ጨዋታ የተሳተፉትን ጆንስ፣ ስሞሊንግ፣ ናኒ፣ ያንግ እና ደ ሂያ እንዲሁም ተቀይረው የገቡት ጆኒ ኢቫንስ፣ ዌልቤክ እና ማኬዳ አሁንም ያምኑባቸዋል፡፡ ክለቡን ወደ ትልቅ ደረጃ የሚመሩት እነዚሁ ወጣቶች መሆናቸውንም እርግጠኛ ናቸው፡፡ ‹‹ተመሳሳይ ወቀሳ ሲወርድብን ይህ የመጀመሪያችን አይደለም፡፡ ከብዙ ዓመታት በፊት ጊግስ እና ሌሎች ወጣቶች ዋናውን ቡድናችንን ሲቀላቀሉ ተመሳሳይ ወቀሳ ሰምተናል፡፡ በተለይ (በ1995) ከአስቶን ቪላ ጋር ተጫውተን ስንሸነፍ ብዙ ተብለናል፡፡ ከዚያ ወዲህም ዌስ ብራውን፣ ጆን ኦሼ እና ዳረን ፍሌቸር የችግሩ ሰለባ ሆነዋል፡፡ ሆኖም እነዚህ ሁሉ ተጨዋቾች በሂደት የቡድናችን መሰረት መሆናቸውን አስመስክረዋል፡፡ ‹‹ስሞሊንግ፣ ጆንስ እና ዌልቤክ ከወዲሁ ስኬቶች አስመዝግበዋል፡፡ ለብሔራዊ ቡድን ተመርጠዋል፡፡ ረቡዕ ጥሩ አልተጫወቱም ይሆናል፡፡ እኔ እና ሌሎቹ የአሰልጣኞች ስታፍ አባላት ግን እናምንባቸዋለን፡፡ በአንድ መጥፎ ጨዋታ የትችት ናዳ ሊወርድባቸው አይገባም፡፡ ጥሩዎች መሆናችንን ጊዜ ይፈርዳል›› ሲሉ አዳዲሶቹን ቋሚ ተሰላፊዎች ይከላከላሉ፡፡
ዩሮፓ ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድ ከካርሊንግ ካፕ ተሰናብቷል፡፡ በኤፍኤካፕ ደግሞ ከቅርብ ተቀናቃኙ ማንቸስተር ሲቲ ተገናኝቷል፡፡ በፕሪሚየር ሊግም ከዚሁ ጠንካራ ጎረቤቱ ከባድ ፈተና አለበት፡፡ ስለዚህ የክለቡ ሌላ የውድድር መድረክ ፈርጉሰን ‹‹ለድክመታችን መቀጣጫ›› ሲሉ የገለፁት ዩሮፓ ሊግ ይሆናል፡፡ በውድድሩ እዚህ ደረጃ የደረሱትን ተሳታፊዎች ጨምሮ ዩናይትድ ከ32 ቡድኖች ጋር በመጪው አርብ ድልድል ይወጣለታል፡፡ ፈርጊ ውድድሩን ‹‹ቅጣት›› ሲሉ መግለፃቸው የአውሮፓ እግርኳስ ማህበር ፕሬዝዳንቱን ሚሼል ፕላቲኒ አስቆጥቷል፡፡ ስኮትላንዳዊውም ቆይተው ‹‹ዩሮፓ ሊግ ጥሩ ውድድር ነው፡፡ ጠንካራ ፉክክርም ይደረግበታል፡፡ አሁንም በውድድሩ የሚሳተፉትን ክለቦች ስትመለከቱ ጥንካሬውን ትረዳላችሁ፡፡ ውድድሩን አስቀድሜ ለእኛ የቅጣት ያህል መሆኑን የተናገርኩት ክለባችን ለ20 ዓመታት ያህል በቻምፒየንስ ሊጉ እንደነበረ በማስታወስ ነው፡፡ በዚያ መልኩ እየተፎካከርን መቀጠል አለመቻላችን ለዩሮፓ ሊግ እንደበቃን ለመግለፅ የተጠቀምኩት ንግግር ነው፡፡ በተረፈ በዩሮፓ ሊግ ችግር የለብኝም፡፡ ሁሉም ማሸነፍ የሚፈልገው ውድድር ነው፡፡ አሁን እኛም ገብተንበታል፡፡ ልናሸንፈው እንሞክራለን›› ይላሉ፡፡ ፈርጊ የፕላቲኒን አስተያየት ተከትለው ይህንን ቢሉም የቶተንሀሙ አሰልጣኝ ሀሪ ሬድናፕ የኦልድትራፎርዱ ሰውዬ አስቀድመው በተናገሩት ይስማማሉ፡፡ እንደ ሬድናፕ እምነት በዩሮፓ ሊግ መወዳደር ትልቅ ውድቀት እና ‹‹ቅጣት›› ነው፡፡ እንግሊዛዊው ራሳቸው ከዩሮፓ ሊግ ተሸንፈው ሊወጡ ቢቃረቡም ውድድሩ ለታላላቆቹ ክለቦች የማያስደስት መሆኑን ይናገራሉ፡፡ ‹‹ከፕሪሚየር ሊግ ሌሎች ክለቦች በአንዱ ውስጥ ብሆን ኖሮ ቶተንሀም በዩሮፓ ሊግ እንዲቆይ አጥብቄ መፈለጌ አይቀርም ነበር፡፡ ጠላቶችህ በውድድሩ እንድትቆይ የሚመኙልህ ከሆነ በእርግጥም ውድድሩ በራሱ ቅጣት ነው ማለት ነው፡፡ የፕሪሚየር ሊግ ተጋጣሚዎችህ ሐሙስ ምሽት መጫወትህን ይፈልጉታል፡፡ ሁልጊዜም በየሳምንቱ ሐሙስ እና እሁድ እየተጫወትክ ብትቀጥል ደስታቸውን አይችሉም፡፡ ‹‹ውድድሩ ለጉዳቶች ይዳርግሀል፡፡ ተጨዋቾችህ ከጨዋታ መደራረብ የተነሳ በጉዳት ይሳሱብሀል፡፡ እያንዳንዱ ሳምንት የስቃይ ይሆናል፡፡ ሐሙስ ከሜዳህ ውጪ ትጫወታለህ፤ አርብ ትመለሳለህ፡፡ ይህ ደግሞ ለቀጣይ ጨዋታዎች ለመዘጋጀት አይመችም፡፡ ስለዚህ አሌክስ (ፈርጉሰን) የተናገረው እውነቱን ነው፡፡ ለእነርሱ በዩሮፓ ሊግ መጫወት ቅጣት ነው›› ሲሉ የግል አስተያየታቸውን ከልምዳቸው ተነስተው ያስቀምጣሉ፡፡ አሁን የሁሉም ሰው ጉጉት የዩናትድ የዩሮፓ ሊግ ቀጣይ ውጤት አይደለም፡፡ በተለይ የክለቡ ደጋፊዎች በውድድር ዘመኑ መጀመሪያ ላይ የተመለከቱት ብሩህ ተስፋ ወደ ቡድናቸው መመለስ መቻሉን ማየት ይሻሉ፡፡ ዩናይትድ በውጤት ቀመሱ ያገግም ይሆናል፡፡ በፕሪሚየር ሊጉ በሳምንቱ መጨረሻ አራት ጎሎች ማስቆጠሩ የዚህ ምልክት ሊሆን ይችላል፡፡ ሆኖም ደጋፊዎቹ ለረጅም ጊዜ ፈርጉሰን ጆሮ የነፈጉትን የአጥቂ አማካይ ተጨዋች ግዢ ጉዳይ አሁንም ያነሳሉ፡፡ አሰልጣኙ ምርጥ የቦታውን ተጨዋች ለመግዛት ገንዘብን እንደ ምክንያት አያነሱም፡፡ አሰልጣኙ ምርጥ የቦታውን ተጨዋች ለመግዛት ገንዘብን እንደ ምክንያት አያነሱም፡፡ እርሳቸው ከፈለጉ አሜሪካዊያኑ የክለቡ ባለሀብቶች የሚፈልጉትን ተጨዋች እንደሚገዙላቸው በገዛ አንደበታቸው መስክረዋል፡፡ ለወጣቶቹ ደ ሂያ እና ጆንስ ዝውውር ያወጡት ገንዘብ ትንሽ አይደለም፡፡ በቀጣዮቹ ሳምንታት 70ኛ ዓመታቸውን የሚያከብሩት አዛውንቱ በክለቡ ሩብ ምዕተ ዓመት ቆይታቸው የገጠማቸውን የአሁኑን ፈተና ለመወጣት ፈጣን ውሳኔ ያሻቸዋል፡፡ ፈርጊ በጃንዋሪ እርምጃ ካልወሰዱ በኦገስት የተናገሩለት የባርሴሎናን ሀያልነት የመንጠቅ ራዕይ ቅዠት እንዳይሆን የሚሰጉ በርክተዋል፡፡
Posted on January 5, 2012, in ETHIOPIA AMHARIC. Bookmark the permalink. Leave a Comment.
![ETHflag_1__1_[1]](http://ethioandinet.files.wordpress.com/2012/09/ethflag_1__1_1.gif)


![60682_3922603203195_526663258_n[1] 60682_3922603203195_526663258_n[1]](http://farm9.staticflickr.com/8379/8653925962_694f997614_m.jpg)
![532059_547719218612772_154310823_n[1] 532059_547719218612772_154310823_n[1]](http://farm9.staticflickr.com/8101/8647940727_046dbca87f_m.jpg)

![524141_495401087180992_37321768_n[1] 524141_495401087180992_37321768_n[1]](http://farm9.staticflickr.com/8116/8645651087_09f9c14b6c_m.jpg)
Leave a Comment
Comments (0)