ኢትዮ ቻናል ጋዜጣና ሳምሶን አድቨርቲይዚንግ ላልተወሰነ ጊዜ ተዘጉ

- አቶ ሳምሶን ማሞና ባለቤቱ ታስረው በ200 ሺሕ ብር ዋስ ተለቀቁ

በሳምንት ሁለት ቀን (ረቡዕና ቅዳሜ) ለተወሰነ ጊዜ እየታተመ ከተሰራጨ በኋላ፣ በሕትመት ዋጋ መናር ምክንያት በሳምንት አንድ ጊዜ (ቅዳሜ) በመታተምና በመሰራጨት ላለፉት አምስት ዓመታት የቆየው ኢትዮ ቻናል ጋዜጣና ለ15 ዓመታት የማስታወቂያ ሥራ ሲሠራ የቆየው ሳምሶን አድቨርታይዚንግ፣ ከትናንት ጀምሮ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲዘጉ መወሰኑን ባለቤቱ ጋዜጠኛ ሳምሶን ማሞ ለሪፖርተር ገለጸ፡፡ ድርጅቱን ለመዝጋት የወሰነበትን ምክንያት ተጠይቆ፣ የ2003 ዓ.ም. እና የ2004 ዓ.ም. የንግድ ፈቃድ አለመታደሱን ተከትሎ ‹‹ንግድ ፈቃድ ሳያድሱ በመሥራት ወንጀል›› ክስ ስለቀረበባቸውና የተጠቀሰባቸው የሕግ አንቀጽ እስከ 15 ዓመታት እንደሚያስቀጣ ስለተነገራቸው፣ ችግሩ መፍትሔ እስከሚያገኝ የወሰዱት ዕርምጃ መሆኑን ገልጿል፡፡

አቶ ሳምሶን እንደሚለው፣ ባለፈው ሳምንት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ከሜጋ ማተሚያ ቤት ገባ ብሎ በሚገኘው ቢሮው አድራሻ ንግድ ፈቃዳቸውን በአስቸኳይ እንዲያድሱ ሁለት ደብዳቤ በተከታታይ ይደርሳቸዋል፡፡ በዚህ ጊዜ አቶ ሳምሶን ‹‹በአጭር ጊዜ ማደስ አይቻልም፡፡ መዝጋት ከፈለጋችሁ መዝጋት ትችላላችሁ፤›› የሚል ምላሽ ይሰጣል፡፡

ሐምሌ 25 ቀን 2004 ዓ.ም. እሱ ለሥራ እንደወጣ፣ ከቢሮው ይደወልለትና ፖሊሶች እንደሚፈልጉት ሲገለጽለት ‹‹ይጠብቁኝ›› በማለት ወደ ቢሮው መሄዱን የገለፈው አቶ ሳምሶን፣ ቢሮው ሲደርስ ስድስት ፖሊሶችን ማግኘቱንና አብረዋቸው ወደ ቂርቆስ ፖሊስ መምሪያ መሄዱን ተናግሯል፡፡

‹‹ፈቃድ ባለማደስ ወንጀል ስለተከሰስክና ወንጀሉ እስከ 15 ዓመታት የሚያሳስር በመሆኑ ዋስትና አይፈቀድልህም፡፡ በቁጥጥር ሥር ውለሃል፤›› ተብሎ መታሰሩን አቶ ሳምሶን አስረድቷል፡፡ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር የዋሉትን ባለቤቱን ለመጠየቅ ፖሊስ ጣቢያ ሲሄድ ባለቤቱ ወ/ሮ ዘውድነሽ ታደሰም፣ ‹‹አንቺም አብረሽ ተከሰሻል›› በሚል ሁለቱም ታስረው ጣቢያ ማደራቸውን ተናግሯል፡፡

እንደ ነፍሰ ገዳይ አራት በአራት በሆነች ጠባብ ክፍል ውስጥ ከ24 እስረኞች ጋር ታስሮ ማደሩን የገለጸው አቶ ሳምሶን፣ ሐምሌ 26 ቀን 2004 ዓ.ም. ወደ ፍርድ ቤት ተወስዶ እስከ ምሽቱ 11፡00 ሰዓት ድረስ እዚያው መዋሉን አስታውቋል፡፡

በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የወረዳው ፍትሕ ጽሕፈት ቤት ንግድ ፈቃድ ሳያድሱ በመሥራት ወንጀል እስከ 15 ዓመታት የሚያሳስር የሕግ አንቀጽ ጠቅሶ ዋስትና እንዲከለከሉ ቢጥርም፣ ፍርድ ቤቱ ዋስትና እንደማያስከለክል በመግለጽና ከባድ ወንጀል መሆኑን በመጥቀስ፣ እያንዳንዳቸው የ100 ሺሕ ብር ዋስ አስይዘው እንዲለቀቁ ማዘዙን ገልጿል፡፡

ሰዓቱ መሽቶ ስለነበር የማስፈቻ ዋራንት ማስቆረጥ ስላልቻሉ፣ ገንዘብ የከፈሉበትን ደረሰኝ ብቻ ይዘው ፖሊስ ጣቢያ ሲሄዱ፣ በዚህ እንደማይፈቱ ተገልጾላቸው ወደ ማሰሪያ ክፍል ውስጥ እንዲገቡ መደረጋቸውን የገለጸው አቶ ሳምሶን፣ ቅዳሜና እሑድን እንዲታሰሩ የፈለጉና ጉዳዩን ያቀነባበሩ ቢኖሩም፣ የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ የሰማ የመንግሥት አካል እንዲፈቱ ትዕዛዝ በማስተላለፉ ሊፈቱ መቻላቸውን አስረድቷል፡፡

የተከሰሱት ንግድ ፈቃድ ባለማደስ ብቻ ከሆነ በርካታ ፍቃድ ያላሳደሱ ነጋዴዎች እንደሚገፋ የገለጸው አቶ ሳምሶን፣ ከበስተጀርባው ሌላ አቀነባባሪ አካል ይኖራል የሚል ግምት እንዳለው ተናግሯል፡፡

በዚህ ሁኔታ ለመቀጠል ስለማይቻል ሁለቱንም ድርጅቶች ለመዝጋትና ጉዳዩን ለመከታተል እንደሚፈልግ የገለጸው አቶ ሳምሶን፣ ከትናንትና ጀምሮ በሁለቱም ድርጅቶች ስም የሚንቀሳቀስ ሥራ አለመኖሩን አስታውቋል፡፡ ነሐሴ 17 ቀን 2004 ዓ.ም. ፍርድ ቤት እንደሚቀርቡም አስታውሷል፡፡

በዜድ ፕሬስ ፕሮሞሽን ኃላፊቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ሥር የሚታመው ኢትዮ ቻናል ጋዜጣ በባለቤቱ በወ/ሮ ዘውድነህሽ ታደሰና በራሱ ስም በጋራ የተቋቋመ ሲሆን፣ ላለፉት 15 ዓመታት በማስታወቂያና ፕሮሞሽን ሥራ ላይ የቆየው ሳምሶን አድቨርቲይዚንግ በራሱ ስም የተቋቋመ መሆኑን አስረድቷል፡፡

ምንጭ ሪፖርተር

About these ads

Posted on August 8, 2012, in ETHIOPIA AMHARIC. Bookmark the permalink. Leave a Comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: