መለስ ዜናዊ መስቀል መሳለሙን በተመለከተ

 On Thursday, January 19, 2012 11:36 PM.

ከግርማ ካሳ

ካፒታል ኢትዮጵያ የተሰኘዉ፣ አዲስ አበባ ዉስጥ የሚታተመዉ የእንግሊዘኛ ጋዜጣ «መንግስትና ቤተ ክርስቲያን» በሚል ርእስ ስር አንድ ዘገባ በድህረ ገጹ ላይ አዉጥቶ ነበር። ከዘገባዉ ጋር ተካቶ በድህረ ገጹ አንድ የተለጠፈ ፣ ቀልቤን የሳበ፣ ፎቶግራፍ አየሁ። የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ፣ ከአቡነ ጳዉሎስ እጅ፣ ወርቃማ መስቀልን ሲሳለሙ የሚያሳይ ፎቶግራፍ ነበር።

ጽሑፉን ሳላነብ ፎቶግራፉ ላይ አይኖቼ ተተክለዉ በዉስጤ የተለያዩ ሃሳቦች ይመላለሱ ጀመር። ደስ ይለኝና ትንሽ ቆይቼ ከመቅስፈት ደስታዬ ወደ ሃዘን ይለወጣል። «አይደለም … ይህ ትልቅ ነገር ነዉ» እላለሁ። መልሼ ደግሞ «አይ ዋጋ የለዉ ሲያስመስሉ ነዉ» እያልኩ በቃ፣ ወደ ቀኝ ወደ ግራ በሃሳብ መላወስ ጀመርኩ።

«መስቀል» መስቀል የሆነዉ፣ ጌታችን መድሃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ የሰዉ ልጆችን ለማዳን ከሁለት ሺህ አመታት በፊት በመስቀል ላይ በመሰቀሉ ነዉ። «ሙሴ በምድረ በዳ እባብን እንደሰቀለ በርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረዉ እንጂ እንዳይጠፋ የሰዉ ልጅም(ኢየሱስ ክርስቶስ) ሊሰቀል ይገባዋል» ይላል ዩሐ 3፡15። ዮሐንስ 3፡ 16 ደግሞ «በርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረዉ እንጂ እንዳይጠፉ እግዚአብሄር (አብ) አንድያ ልጁን(ወልድ ወይንም ኢየሱስ ክርስቶስ) እስኪሰጥ ድረስ አለምን እንዲሁ ወዷልና» ይላል። መድሃኔአለም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሞተዉ እኛን ለማዳን ነዉ። እኛን ያዳነንም ስለሚወደን ነዉ። በመሆኑም መስቀል የፍቅር ምልክት ነዉ።

መስቀል ሁለት እንጨቶችን የያዘ ነዉ። አንደኛዉ ከላይ ወደ ታች የቆመዉ ሲሆን፣ ሁለተኛዉ ደግም ከቀኝ ወደ ግራ ወደ ጎን የተዘረጋው ነዉ። ከላይ ወደታች የሆነዉ እንጨት የሚያሳየዉ ሰዉንና እግዚአብሄርን የሚያገኛኝ መንገድ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተዘረጋ ነዉ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ ጋር አስታርቆናል። መስቀል የሚያሳየዉ አንዱና ትልቁ ቁም ነገር ይሄ ነዉ።

ነገር ግን መድሃኔዓለም በመስቀል ላይ በከፈለዉ መስዋእትነት፣ ሰዉና እግዚአብሄርን ብቻ አይደለም ያስታረቀዉ። ሰዉንም ከሰዉ ጋር ነዉ ለማስታረቅ የመጣዉ። ከቀኝ ወደ ግራ የተዘረጋዉ እንጨት የሚያሳየዉ ወንድምን ከወንድም የማስታረቅን ሂደት ነዉ። በመሆኑም መስቀል የእርቅ ምልክት ነዉ።

ሰዎች አብረን በምንኖርበት ጊዜ ስህተቶች እንሰራለን። በወንድሞቻችን ጉዳት ሊደርስብን ይችላል። እኛም አዉቀንም ሆነ ሳናውቅም ጉዳት ልናደርስ እንችላለን። ለብዙ አመታት ትዳር መስርተዉ ፣ ልጆች ወልደዉ የኖሩ ባልና ሚስቶች በትንሽ ነገር ፣ የአመታት መልካም ኑሯቸዉን ረስተዉ ፣ እንደ ጠላት የሚተያዩ አሉ። ትላንት በአንድ ድርጅት አብረዉ የታገሉ፣ የጥንቱ መልካም ነገር ተርስቷቸው አሁን፣ የሃሳብ ልዩነቶች በመካከላቸው ስለተፈጠረ እንደ ጠላት የሚተያዩ አሉ። በተለይ በኛ ኢትዮጵያውያን መካከል መቻቻል፣ ይቅር መባባል ብዙ አልተለመደም። ብዙ ጊዜ በጣም ቂመኞች፣ ነክሰን ነገሮችን የምንይዝ፣ ግትሮች ነን። ነገር ግን መስቀል የተለየ መልእክት ነዉ ያለዉ።

በመስቀል ላይ ፣ መድሃኔ አለም ኢየሱስ ክርስቶስ የሰቀሉትን፣ በጦር የወጉትን ፣ የገደሉትን አልረገማቸዉም። አልተበቀላቸዉም። «የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸዉ» ነበር ያለዉ። መስቀል ይቅር የመባባልና ምህረት የመደራረግ ምልክት ነዉ።

http://googleads.g.doubleclick.net/pagead/ads?client=ca-pub-9296450337345570&output=html&h=60&slotname=3787492135&w=468&lmt=1327056577&ea=0&flash=11.1.102.55&url=http%3A%2F%2Fwww.ethiosun.com%2F2012%2F%25e1%2588%2598%25e1%2588%2588%25e1%2588%25b5-%25e1%258b%259c%25e1%258a%2593%25e1%258b%258a-%25e1%2588%2598%25e1%2588%25b5%25e1%2589%2580%25e1%2588%258d-%25e1%2588%2598%25e1%2588%25b3%25e1%2588%2588%25e1%2588%2599%25e1%258a%2595-%25e1%2589%25a0%25e1%2589%25b0%25e1%2588%2598%25e1%2588%2588%25e1%258a%25a8%25e1%2589%25b0-2%2F&dt=1327056577459&shv=r20120111&jsv=r20110914&saldr=1&prev_slotnames=5715135218%2C3787492135&correlator=1327056577309&frm=20&adk=1144698336&ga_vid=1927721146.1321387387&ga_sid=1327056577&ga_hid=214308613&ga_fc=1&u_tz=60&u_his=3&u_java=1&u_h=768&u_w=1366&u_ah=728&u_aw=1366&u_cd=32&u_nplug=0&u_nmime=0&dff=arial&dfs=13&adx=200&ady=1263&biw=1345&bih=584&eid=44901218&ref=http%3A%2F%2Fwww.ethiosun.com%2Fcategory%2Famharic%2F&fu=0&ifi=3&dtd=147

«ይህንን የፍቅር፣ የወንድማማችነት፣ የይቅርታ፣ ምህረት የመደራረግ ምልክት የሆነዉን መስቀል፣ አቡነ ጳዉሎስ በእጃቸው ይዘዉ ሲያሳልሙ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ደግሞ ጎንበስ ብለዉ ሲሳለሙ ፣ ለፍቅር ለሰላም፣ ለይቅርታ ፣ ለእርቅ ልቦናቸዉን መክፈታቸዉን ይሆን ?» የሚል ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል። ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት በሚል ነዉ እንግዲህ በሃሳብ ማእበል ዉስጥ በመዘፈቅ ነገሮችን ማውጣትና ማውረድ የጀመርኩት።

አቡነ ጳውሎስ የኢትዮጵያ «ፓትሪያርክ» ከሆኑበት ጊዜ ጀመሮ በጥንታዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ መከፋፋል ተፈጥሯል። ክርስቶስን እናገለግላለን የሚሉ ጳጳሳት፣ በእጃቸዉ ይዘዉ የሚያሳልሙትን የመስቀል አላማ፣ ተግራባዊ ከማድረግ ይልቅ፣ ሲወጋገዙ ነዉ የምናየዉ። አቡነ ጳዉሎስ በእጃቸው መስቀል ይዘዋል እንጂ፣ በልባቸዉ የጥላቻ፣ የክፋት፣ የትእቢት ምልክት የሆነዉ የእባብ ምስል የተሳለ ነዉ የሚመስለዉ። ይህ ባይሆንማ ኖሮ፣ ለመስቀል ቢገዙማ ኖሮ ከነአቡነ መርቆርዮስ ጋር ይስማሙ ነበር። በቦሌ ናቡከደነጾር እንዳደረገዉ፣ የርሳቸዉን ወርቃማ ሃዉልት አያቆሙም ነበር። «የሚያስታርቁ ብጹዓን ናቸዉ፤ የእግዚአብሄር ልጆች ይባላሉና» ተብሎ እንደተጻፋ፣ እርሳቸዉ እራሳቸው ከወንድሞቻቸው ታርቀዉ፣ ሌሎች በአገራችን ያሉ ቀዉሶች ይፈቱ ዘንድ የማስታረቅ ሥራ በሰሩ ነበር።

እንግዲህ አቡነ ጵወሎስ ንስሐ ይግቡ እላለሁ። መስቀልን በእጅ መያዝ ብቻ ሳይሆን በልባቸዉም ሊስሉት ይገባል እላለሁ። እግዚአብሄር የሚምር የሚራራ አምላክ ነዉ። የጌታ የምህረት በር አሁንም የተከፈተች ናት። ነገር ግን እግዚአብሄር በምህረቱ አይዘበትበትም። ከቀድሞ ሕጋዊ ፓትሪያርክ ጋር ያላቸዉን ልዩነቶች ቁጭ ብለዉ በቅንነትና በትህትና ካልፈቱ፣ ለመስቀሉ፣ ለእርቅ በራቸዉን ከዘጉ፣ የሚጸልዩት፣ የሚያስቀድሱትና የሚያደርጉትን ማናቸዉም አይነት መንፋሳዊ/ሃያማኖታዊ ተግባራት በሙሉ፣ በእግዚአብሄር ዘንድ ጸያፍ ሆነዉ ነዉ የሚታዩት። ተቀባይነት አይኖራቸዉም። «እሺ ብትሉ ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላችሁ፤ እምቢ ብትሉ ግን ሰይፍ ይበላቹሃል» ተብሎ እንደተጻፈው በርግጥ እኝህ አባት ካልታዘዙ፣ ሰይፍ ይበላቸዋል። አወዳደቃቸዉም እጅግ በጣም የከፋ ይሆናል።

ወደ ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ስመጣ፣ የምለዉ ይሄን ነዉ። ለመስቀል መጎንበሳቸው አስደስቶኛል። እንደ አብዛኛዎቹ የስድሳዎቹ ፖለቲከኞች፣ ማርክሲስት፣ ሌኒኒስት ፣ እግዚአብሄርን የማያምኑ ነበር የሚመስሉኝ።

እንግዲህ እርሳቸዉም ጋር መስቀል፣ በዉጭ ብቻ ሳይሆን በተግባር በልባቸዉ እንዲሳል ያስፈልጋል።

መስቀል የፍቅር እንጂ የጭካኔ ምልክት አይደለም። ሰላማዊ ኢትዮጵያዉያንን «ሽብርተኞች ናቸዉ» እያሉ ማሰርዎትን ያቁሙ። ከሰላም ዉጭ ሌላ ነገር የማያወቁትን ፣ እንደ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ጋዜጠኛ ርዮት አለሙ፣ አቶ አንዱዋለም አራጌ፣ አቶ በቀለ ገርባ የመሳሰሉ ወንድምዎቾትንና እህትዎቾትን ይፍቱ። መቀጣት፣ መታረም፣ ለሕብረተሰቡ ጥቅም ሲባል በቁጥጥር ስር መዋል ካላባቸው፣ ነፍሰ ገዳዮችና ወንጀለኞች በስተቀር፣ በአራቱም ማእዘናት ባሉ እሥር ቤቶች የታሰሩ እስረኞችን ይፍቱ » ስል እማጸናቸዋለሁ። ይህ አይነቱ የጭካኔ ድርጊት የበለጠ ጥላቻን፣ መቃቃረን የሚያመጣ እንጂ የሚገነባና የሚጠቅም አይደለም።

መስቀል የእርቅ የመቻቻል ምልክት ነዉ። በአገራችን የዘር ልዩነቶች በዝተዋል። ፖለቲካዉ ከሯል። የፍርሃት ደመና ሕዝቡን ከቦታል። ሁሉም ችግሩና ብሶቱን በዉስጥ አምቆ ይዟል። በየመስሪያ ቤቱ፣ በየቢሮው ጉቦ ካልተሰጠ ጉዳይ አይፈጸምም። አገር ቤት የሚመረቱ እህሎች ወደ አረብ አገር በመላክ ጥቂቶች ሲከብሩ አብዛኛዉ ሕዝብ፣ በቀን ሶስቴ ሳይሆን በቀን አንዴ ብቻ ነዉ የሚመገበዉ። ለሕዝቡ የተረፈው ቁምራ ብቻ ነዉ። (“ቁ” ለቁርስ ፣ “ም” ለምሳ እና “ራ” ለራት በአንድ ላይ ሆኖ በቀን አንዴ መመገብ))

ሁላችንም ትልቅ የአስተሳሰብና የአመለካከት አብዮት ያስፈልገናል። ይሄም የሚጀምረዉ ከአቶ መለስ ዜናዊ ነዉ። ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር (የተቃዋሚ ፓርቲዎች ስል እንደ አንድነት ፓርቲ ያሉ ዋና ፓርቲዎችን ማለቴ ነዉ) በጋራ ጉዳዮች ላይ ስምምነትና ዉይይቶች መጀመር አለበት። ከፍቷቸው ነፍጥ ያነሱ ቡድኖችን፣ ነፍጥ አነሱ ብሎ እነርሱን ሽብርተኞች ማለትን አቁመዉ፣ ነፍጥ እንዲያነሱ ላደረጋቸው ጉዳዮች ምላሽ በመስጠት ወደ ጠረቤዛ ዉይይት እንዲመጡ ማድረግ እና ብሄራዊ እርቅ እንዲኖር የድርሻቸዉን መወጣት ይጠበቅባቸዋል።

እንደዉም እዉነትን እንነጋገር ከተባለ ፣ ለእርቅ እንቅፋት የሆኑት እራሳቸው አቶ መለስ ዜናዊ ናቸዉና፣ ለራሳቸዉ ሲሉ ይህንን የእርቅ ጉዳይ ሊያስቡበት ይገባል ባይ ነኝ። አቶ መለስ ከፈለጉ በአጭር ጊዜ ዉስጥ ለትዉልድ የሚተርፍ፣ ታሪካዊ ብሄራዊ እርቅ ማምጣት ይችላሉ። እንግዲህ የተሳለሙት መስቀል ማለት ይሄ ነዉ። እርቅ ማለት ነዉ።

እርግጥ ነዉ «እርቅ ፣ እርቅ እያሉ ማውራት ቀላል ነዉ። በተግባር ለእርቅ መስራት ግን ቀላል እንዳልሆነ አውቃለሁ። የትም ቦታ መገንባት፣ ሰዉን ወደ አንድነት ማምጣት፣ ሰዉን ማስማማት በጣም ከባድ ነዉ። ማፍረስ፣ ማጣላት፣ ማቃቃር፣ ማለያየት ደግሞ በተቃራኒዉ ዘርፍ፣ እጅግ በጣም ቀላል ነዉ። ቀላሉን ሳይሆን ከባዱን ማድረግ ነዉ እንግዲህ መሪን መሪ የሚያሰኘዉ።

የፈርኦን ልብ እንደደነደነ አቶ መለስ ዜናዊ ልባቸዉን አደንድነዉ ለዝንተ አለም የሚገዙ ከመሰላቸው፣ የምናቀርብላቸዉን የሰላምና የእርቅ ጥሪዎችን አጣጥለዉ የሚመለከቱት ከሆነ፣ የማዝነዉ ለርሳቸው ነዉ። አሁን ባሉበት ሁኔታ መቀጠል እንደማይችሉ በእርግጠኝነት ልነግራቸው እወዳለሁ። ወደዱም ጠሉም፣ ከስልጣናቸው ይነሳሉ። ጥያቄዉ በሰላም በፍቅር ልጆቻቸዉንና የልጅ ልጆቻቸዉን በሚያኮራ መልኩ ነዉ የሚነሱት፣ ወይንስ በሌላ አይነት እንደ ጋዳፊ አይነት እጣ ደርሷቸው ነዉ የሚነሱት የሚል ነዉ።

ከአቶ መለስና ከአቡነ ጳዎሎስ ትኩረቴን ላዙርና ወደ ተቀረነዉ ልምጣ። ስለ እነርሱ ተናገርን፤ እኛስ የት ነዉ ያለነዉ ? እኛስ ከምር ለእርቅ፣ ለሰላም፣ ለፍቅር፣ ለይቅር መባባል፣ ለመቻቻል ዝግጁዎች ነን ወይ? የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት እፈልጋልሁ።

«አዎ ነን» የምንል ከሆነ ታዲያ የመቻቻል፣ የመከባበር ፖለቲካዉ ወዴት ነዉ ያለዉ ? ዜጎች የተለየ ሃሳብና አስተያየት ስላቀረቡ እገዳ፣ ስድብ የሚደርስባቸው ለምንድን ነው ? ዜጎች የፈለገ አመለካከት ቢኖራቸዉ፣ ከቻልን የተሳሳቱ ከመሰለን፣ ሃሳባቸዉን በሃሳቦችን በሰለጠነ መንገድ እንዲለዉጡ ማድረግ፣ ካልቻልን ደግሞ በልዩነቶቻችን ተከባብረን ወደፊት መራመድ ለምን ያቅተናል ?

አትላንታ በተደረገዉ በኢትዮጵያዉያን እግር ኳስ ዉድድር ወቅት፣ በክብር እንግድነት ንግግር ያደረገችዉ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ አንድ የተናገረችዉ ታላቅ አባባል ነበር። ስላሰሯት፣ ከስድስት ወራት በላይ በጨለማ ቤት ዉስጥ ስላስቀመጧትና ግፍ ስለፈጸሙባት ፣ ስለአቶ መለስና ጓዶቻቸዉ ስትናገር ወንድሞቿ እንደነበሩ ነዉ በግልጽ የተናገረቸዉ። «ወንድሜ ስመ ጥፉ፣ ግብረ ጥፉ ሊሆን ይችላል።፡ነገር ግን ምንም ማድረግ አልችለም ወንድሜ ነዉ » ነበር ያላችው።

እርግጥ ነዉ ይከብዳል። ግን ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ይቅር ማለት ፣ አለመጥላት፣ ከቻለች እኛ ለመዉደድ፣ ለማፍቀር ሙከራ ማድረጉ እንዴት ሊከብደን ይችላል ? እንግዲህ በአገራችን ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ፣ በወንድማማችነትና በፍቅር ላይ የተመሰረተ፣ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓአት ለመገንባት የሚደረገዉ ትግል፣ መጀመር ያለበት ከእያንዳንዳችን ነዉ።

ለሁላችንም እግዚአብሄር ልቦና ይስጠን !

Posted on January 20, 2012, in ETHIOPIA AMHARIC. Bookmark the permalink. 2 Comments.

  1. wushetam

Leave a Reply to germicael Cancel reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: