“አቶ መለስ አንድ ነገር ቢሆን ኢህአዴግ ችግር ይገጥመዋል” – ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የቀድሞው ፕሬዚዳንት

(ሰንደቅ ጋዜጣ)የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዚደንት እና በአሁኑ ወቅት የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ አሁን በሥራ ላይ ያለውን ሕገመንግሥት ካረቀቁት ምሁራን መካከል አንጋፋው መሆናቸው ይታወቃል። ከጠ/ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ መታመም በኋላ እየተነሱ ባሉ ሕገመንግሥታዊ ጥያቄዎችና ተያያዥ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ ፍሬው አበበ በቢሮአቸው ተገኝቶ አነጋግሯቸዋል።

ሰንደቅ፡- ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ መታመማቸው ከተነገረ በኋላ ከዚህ በፊት እምብዛም የማይሰሙ ሕገ-መንግሥታዊ
ጥያቄዎች እየተነሱ መወያያ እየሆኑ ነው። ከእነዚህ ጉዳዮች አንዱ ሕገመንግሥቱ ጠ/ሚኒስትሩ በማይኖሩ ጊዜ ማን
ይተካቸዋል ለሚለው ግልጽ ምላሽ የለውም የሚለው ጉዳይ አንዱ ነው። ይህን ጉዳይ እንዴት ነው የተመለከቱት?
ዶ/ር ነጋሶ፡- ሕገመንግሥቱ ያለበት ክፍተት ከጠ/ሚኒስትሩ ጋር በተያያዘ ብቻ አይደለም። ሌሎችም በርካታ ጉዳዮች
መኖራቸውን በሂደት እያየን የመጣንበት ሁኔታ አለ። የዚህ ዓይነት ችግሮች ከዚህ በፊትም ተከስቷል። በወቅቱ ኅብረተሰቡ
በደንብ አላወቀውም፣ አልተወያየበትም እንጂ ክፍተቶች በደንብ አሉ። አንዳንዶቹን ለምሳሌ ያህል ልጥቀስልህ። አንዱና
ዋንኛው የሕገመንግሥት ጥያቄ በሚነሳበት ጊዜ፣ ጉዳዩን በማየት ረገድ ያለው ክፍተት ነው። ያኔ ሕገመንግሥቱን
በምናረቅበትና በምናፀድቅበት ጊዜ ያላየነው ነው። ይኸውም የሕገመንግሥት ጥያቄ በሚነሳበት ጊዜ ጉዳዩ የሕዝብ ጉዳይ
ነውና እንዴት ለዳኞች እንሰጣለን ብለን ነበር ያየነው። ሕገመንግሥታዊ ጥያቄዎች የሚያስነሱ ጉዳዮች ሲኖሩ ለመጀመሪያ
ደረጃ ፍ/ቤት ይቀርቡና ወደ ሕገመንግሥት አጣሪ ጉባዔ ይላካሉ። ጉባዔው አጣርቶ የውሣኔ ኅሳቡን ለፌዴሬሽን ም/ቤት
ያቀርባል። ፌዴሬሽን ም/ቤት የመጨረሻ ውሣኔ ይሰጣል። ጥያቄው የብሔር ብሔረሰብ ወኪሎች በሙሉ ፌዴሬሽን ም/
ቤት ውስጥ አሉ ወይ? በሙሉ ተወክለዋል ወይ? ሲወከሉስ እንዴት ነው? የሚለው ነው። አሁን እየሆነ ያለው ያለ ሕዝብ
ውክልና ከክልል ም/ቤቶች የመጡ ሰዎች ፌዴሬሽን ም/ቤት ይገባሉ። የክልል ም/ቤቶች ደግሞ የገዢው ፓርቲ አባላት
ናቸው። ስለዚህ ሕገመንግሥታዊ አተረጓጐም ላይ ሲመጣ መጨረሻ የሚጠበቀው የኢህአዴግ መልካም ፈቃድ ነው ማለት

ነው።
ሰንደቅ፡- ሕገመንግሥታዊ ፍርድ ቤት ቢኖር የተሻለ ነበር?

ዶ/ር ነጋሶ፡- አዎ!… ያላደረግነው ጉዳይ ይህንን ነው። በየትኛው አገር ሕገመንግሥታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ልዩ እና ነፃ
የሆኑ ፍ/ቤቶች ይደራጃሉ። ሕዝቡ እነዚህን ጉዳዮች ለማየት መቻሉ ጥሩ ነው። ከዚህ በፊትም ከሕገመንግሥቱ አንፃር
ግንዛቤ ያላገኙ ክፍተቶች ነበሩ። እነዚህን ክፍተቶች ማየት መጀመሩ ጥሩ ነው። በ1994 ዓ.ም ፕሬዚዳንቱን በተመለከተ
አንድ ሕግ ወጥቷል። በሕገመንግሥት የተፃፈው ፕሬዝዳንቱ የሚመረጠው ከተወካዮች ም/ቤት ከሆነ የያዘውን ወንበር
ይለቃል የሚል ብቻ ነው። ፕሬዚዳንቱ ከውጪም፣ ከም/ቤቱ ሊመረጥ ይችላል። ከም/ቤቱ ከሆነ ወንበሩን ይለቃል
ይላል። ፕሬዚዳንቱ ስድስት ዓመት ካገለገለ በኋላ ምን ይሆናል የሚለውን ሕገመንግሥቱ አይመልስም። ሰውየው
ወደፓርቲው ይመለሳል ወይስ ሌላ ፓርቲ ይቀላቀላል ወይስ የራሱን ፓርቲ ይመሰርታል ወይስ ፖለቲካ ትቶ አርፎ
ይቀመጣል የሚለውን አይመልስም። እና ይሄም ትልቅ ክፍተት ነው።
ሰንደቅ፡- ጠ/ሚኒስትሩን በተመለከተስ?
ዶ/ር ነጋሶ፡- ጠ/ሚኒስትሩ በተመለከተ ሕገመንግሥቱ የሚለው ጠ/ሚኒስትሩ በሌለበት ጊዜ ምክትሉ ተክተው ይሰራሉ
ነው።
ሰንደቅ፡- “ተክቶ ይሰራል” ማለት ምን ማለት ነው? መቼና እንዴት ነው የሚተካው?
ዶ/ር ነጋሶ፡- ይህን በተመለከተ ክፍተት አለው። ምክትሉ የሚተካው ጠ/ሚኒስትሩ ምን በሚሆንበት ጊዜ ነው። ጠ/
ሚኒስትሩ ሰው ናቸውና ሊሞቱ ይችላሉ ወይም ደግሞ ታመው ለረጅም ጊዜ ከሥራ ሊገለሉ ይችላሉ። በዚህን ጊዜ ምክትሉ
ተክቶ ለመሥራቱ በሕገመንግሥቱ በግልፅ የተቀመጠ ነገር የለም።
ሰንደቅ፡- ምክትል ጠ/ሚኒስትሩን ማንነው የሚመርጣቸው?
ዶ/ር ነጋሶ፡- ይህንንም በተመለከተ በሕገመንግሥቱ በግልፅ የተቀመጠ ነገር አላገኘሁም። ጠ/ሚኒስትሩ በፓርላማ የሕዝብ
ተመራጮች ነው የተመረጠው። ሕገመንግሥቱ ስለምክትል ጠ/ሚኒስትሩ አመራረጥ በግልፅ የደነገገው ነገር የለም። ለምን
ያህል ጊዜ ተክቶ እንደሚሰራም ግልፅ አይደለም። ጠ/ሚኒስትሩ በሕይወት ከሌሉ መተካታቸው የታወቀ ነገር ነው።
በሕይወት ካሉ ግን ለምን ያህል ጊዜ ነው ሊተካቸው የሚችለው የሚለው በግልፅ አልተቀመጠም።
ሰንደቅ፡- በቅርቡ አቶ በረከት ስምኦን በሰጡት ይፋዊ መግለጫ ጠ/ሚኒስትሩ ረዘም ያለ የሐኪም ፈቃድ ላይ
መሆናቸውና፣ አሁንም አገሪቷን የሚመሩት እሳቸው መሆናቸውን ተናግረዋል። ይሄን ከሕገመንግሥቱ አኳያ እንዴት
ያዩታል? ሕገመንግስቱ ጠ/ሚኒስትር በሌሉ ጊዜ ምክትሉ ተክቶ ይሰራል ነው የሚለው፤
ዶ/ር ነጋሶ፡- ረዥም ጊዜ እረፍት ወስዷል ሲባል ለምን ያህል ጊዜ ነው? በግልፅ አይታወቅም። ጠ/ሚኒስትሩን ያቀረበው
ገዢው ፓርቲ ነው። ገዢው ፓርቲ ኃላፊነት ተሰምቶት ጠ/ሚኒሰትሩ እስኪድኑ ድረስ ምክትሉ ተክተው እንዲሰሩ
ሊያደርጉ ይችላሉ። በም/ቤቱ ያልተመረጠ ምክትል ጠ/ሚኒስትር፤ ጠ/ሚኒስትሩን ለረጅም ጊዜ ተክቶ የሚሰራበት ሁኔታ
ከተፈጠረ ለእኔ ኢ-ሕገመንግሥታዊ ነው። ሕገመንግሥቱ ላይ ያለው ትልቁ ክፍተት ጠ/ሚኒስትሩ በማይኖር ጊዜ ምክትሉ
ለምንያህል ጊዜ፣ በምን ዓይነት ሁኔታ ይተካዋል የሚለው ምላሽ የሰጠ አለመሆኑ ነው። ዋናው ግን መታወቅ ያለበት ግን
በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ያልተመረጠ ምክትል ጠ/ሚኒስትር አገሪቱን ለረዥም ጊዜ ሊመራ አይችልም።
ሰንደቅ፡- እንደነዚህ ዓይነት ጥያቄዎች ሕገመንግሥታዊ ማሻሻያ እንዲመጣ የሚያስችሉ በቂ ምክንያቶች ናቸው ብለው
ያምናሉ?
ዶ/ር ነጋሶ፡- አዎ!… ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች አሉ። አንዱ አሁን እየተነሳ ያለው የጠ/ሚኒስትሩ ጉዳይ ነው።
ሌላው የሕገመንግሥታዊ ፍርድ ቤት ያለመኖር ጉዳይ፣ ነፃ የሆነ ዐቃቤ ሕግ ያለመኖር ጉዳዮች ናቸው። (በአሁን ሰዓት
ዐቃቤ ሕግ መ/ቤት በፍትህ ሚኒስትር ሥር ነው ያለው። ይሄ ተቀይሮ ራሱን የቻለ ነፃና ገለልተኛ የሆነ ዐቃቤ ሕግ
እንዲደራጅ ሕገመንግሥቱ መፍቀድ አለበት።) አንቀፅ 39 የሚመለከቱና ሌሎችም አንቀጾች መሻሻል አለባቸው። ይሄ
ሕገመንግሥት መፅሐፍ ቅዱስ (ዶግማ) አይደለም። በየጊዜው ታይቶ መሻሻል መቻል አለበት። ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ ለ17
ዓመታት ሰርተንበታል። በየወቅቱ ታይቶ መሻሻል ያስፈልጋል። ሕገመንግሥቱ ሳይሻሻል ሕግ ማውጣት ተገቢ አይደለም።

በአሁኑ ሰዓት ችግር የሆነው ሕገመንግሥቱ ሳይሻሻል ኢህአዴግ ብዙ እያጠፋቸው ያሉ ነገሮች የመኖራቸው ጉዳይ ነው።
ከጥፋት ለመዳን ሕገመንግሥቱን ማሻሻል ያስፈልጋል።
ሕገመንግሥቱን በተመለከተ አሁን መደረግ ያለበት የሚሻሻሉ ነገሮች ተዘርዝረው ቀርበው፣ ሕዝብ በየደረጃው ውይይት
አድርጎባቸው ተቀባይነት ያገኙት መሻሻል አለባቸው።
ሰንደቅ፡- ሕገመንግሥቱን በተመለከተ የሚነሱ ቅሬታዎች ሕጉ በሚረቅበት ወቅት የተነሱበት ሁኔታ ነበር? ለምሳሌ
ሕገመንግሥቱ ለጠ/ሚኒስትሩ ምንም ዓይነት የሥልጣን ገደብ አላስቀመጠም፤
ዶ/ር ነጋሶ፡- አንዳንድ ነገሮች በወቅቱ ተነስተዋል። በወቅቱ የነበረው አስተሳሰብ ፓርቲው ከፈለገ ጠ/ሚኒስትሩ ለምን
ዘላለም አያቆየውም የሚል ዓይነት ነበር። ምክንያቱም ጠ/ሚኒስትሩን ለሹመት የሚያቀርበው ገዢው ፓርቲ ነውና።
ሰንደቅ፡- ከጠ/ሚኒስትር መለስ ሕመም ጋር በተያያዘ ኢህአዴግ በውስጡ የመከፋፈል ችግር ሊፈጠር ይችላል የሚሉ
ዘገባዎች በማኅበራዊ ድረገጾች በስፋት ይዘገባሉ። እርስዎስ ከኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች ጋር በቅርበት እንደመሥራትዎ
ይህን ሥጋት ይጋራሉ?
ዶ/ር ነጋሶ፡- ሊመጣም፣ ላይመጣም ይችላል። እኔ እንደሚመስለኝ ጠ/ሚኒስትሩ በሌሉ ጊዜ ተክተው የሚሰሩት ምክትል
ጠ/ሚኒስትሩ ናቸው። ምክትል ጠ/ሚኒስትሩ ሲሾሙ ብቃት አላቸው ተብለው ነው። ያንጊዜ አምነውበት ምክትል ጠ/
ሚኒስትር አድርገው ያስቀመጡትን ሰው ዛሬ ተነስተው አይችልም ብለው ችግር ሊፈጥሩ የሚችሉ አይመስለኝም። እኔ
እስከማውቀው ድረስ ድርጅታዊ ጉባዔ ጠርተው፣ ተወያይተውበት መወሰን አለባቸው። ከዚህ ውጪ ግን በቀላሉ ቡድን
ተፈጥሮ ችግር ሊፈጠር ይችላል ብዬ አላስብም።
ሰንደቅ፡- እየተንፀባረቀ ያለው፤ ጠ/ሚኒስትሩ ከበድ ያለ ነገር ቢገጥማቸው አራቱም የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች
የራሳቸውን ሰው የማስቀመጥ ሽኩቻ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ የሚል ሥጋት ነው፤
ዶ/ር ነጋሶ፡- አቶ መለስ በሕይወት የማይኖሩበት ሁኔታ ከተፈጠረ ወይም ደግሞ ለረዥም ጊዜ ታምመው ከሥራ የመራቅ
ሁኔታ ከተፈጠረ ኢህአዴግ ትልቅ ችግር ይገጥመዋል ብዬ እገምታለሁ።
ሰንደቅ፡- ምን ዓይነት ችግር?
ዶ/ር ነጋሶ፡- አቶ መለስ ከማውቃቸው የኢህአዴግ አባላት ብቃቱም ችሎታውም አለው። ይህን ችሎታውን ለትክክለኛ
ዓላማ ተጠቅሞበታል ወይስ አልተጠቀመበትም የሚለው ጥያቄ እንዳለ ሆኖ ማለቴ ነው። እሱን ለመተካት ይቸገራሉ።
ሰንደቅ፡- ተተኪ አመራር የማፍራቱ ኃላፊነት የጠ/ሚኒስትሩ አልነበረም?
ዶ/ር ነጋሶ፡- በአንድ ሰው ላይ የሚያርፍ ኃላፊነት አይደለም። አንድ የፖለቲካ ድርጅት ሰዎችን ይመለምላል፣ ይገነባል።
ከሴትም ከወንድም ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች። ከመለመልክና ከገነባህ በኋላ በልምድ የሚመጣ ነው፤ ተተኪነት።
ይህንን ለማድረግ የጠ/ሚኒስትሩ ኃላፊነት አይመስለኝም፤ የፓርቲው ጉዳይ ነው።
ሰንደቅ፡- ኢህአዴግ ራሱ ተተኪ አላፈራም ማለት ይቻላል?
ዶ/ር ነጋሶ፡- ከእነሱ ጋር ከተለያየሁ 10 ዓመታት አልፎኛል። በዚህ ጊዜ ውስጥ አፍርተው ሊሆን ይችላል። ሥራ ላይ
በነበርኩበት ወቅት የማውቃቸው እነተወልደ፣ እነስዬ፣ እነገብሩ ሌሎችም ጠንካራ ሰዎች ነበሩ። እነዚህ ጠንካራ ሰዎች
ሕዝቡ በሚያውቀው ምክንያት በአሁኑ ወቅት ከኢህአዴግ ጋር አይደሉም።
ሰንደቅ፡- ከጠ/ሚኒስትሩ ሕመም ጋር ተያይዞ የተፈጠረው የፖለቲካ ድባብ መልካም ገፅታ እንዲይዝ፣ መረጋጋት
እንዲመጣ አንድነት ፓርቲ በቀጣይ ምን መደረግ አለበት የሚል ምክር ይለግሳል?

ዶ/ር ነጋሶ፡- በአገራችን ላይ ብዙ ችግሮች አሉ። አንዱ የዚህ የኑሮ ውድነት ጉዳይ አለ። በቅርቡ የፓርላማው አፈጉባዔ አቶ
አባዱላ ገመዳ ስህተት መሥራታቸውን ያመኑት የሊዝ ጉዳይ አለ። በፀረ-ሽብር ሕጉ መሠረት በሠላማዊ መንገድ
የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅት አመራሮችና ጋዜጠኞችን የመክሰሱና የማንገላታቱ ጉዳይ፣ በነፃው ፕሬስ ላይ ያለው አፈና
አለ። እነዚህና መስል ጉዳዮች ስታይ ከፍተኛ ችግሮች መኖራቸውን ትገነዘባለህ። ኢህአዴግ አገሪቱን መምራት ያልቻለበት
ሁኔታ ነው የሚታየኝ። በቀጣይ ኢህአዴግ ማድረግ ያለበት የሚመስለኝ፤ ወይ አልቻልኩም ብሎ ሌላ ምርጫ እንዲካሄድ
ማድረግ፣ ወይም ሌሎችንም በሚያሳትፍ መንገድ አንድ መድረክ እንዲመሠረት መጣር ነው። በተለይ ከጠ/ሚኒስትሩ
መታመም ጋር ተያይዞ በሚታይበት ጊዜ (ይህን በግሌ ነው የምናገረው) ስሰማ የነበረው ሁሉ ጥሩ አይደለም። አንድ ሰው
ሲታመም መጥፎ ነገር አትመኝለትም። እሳቸው ታመዋል ሲባል መጥፎ አስተያየት ስትሰማ የሰዎች ጥላቻ የቱን ያህል
የከበደ መሆኑን ትገነዘባለህ። ከዚህ አኳያ ኢህአዴግም ራሱን የሚያይበት፣ ጠ/ሚኒስትሩም (በጤና እንዲመለሱ
እመኝላቸዋለሁ) ከተመለሱ የከዚህ በፊቱን የአመራር አቅጣጫቸውን መቀየር አለባቸው። ይበልጥ ግልፅ መሆን፣ ይበልጥ
ዴሞክራት መሆን፣ እኔ ብቻ የሚል አካሄድ እንደማያዋጣ መረዳት አለባቸው። በአሁኑ ወቀት ያሉትን ብዙ ችግሮች
ለመፍታት በራቸውን ክፍት ሊያደርጉ ይገባል።

Posted on August 1, 2012, in ETHIOPIA AMHARIC. Bookmark the permalink. 1 Comment.

  1. 'Tornet kefetaw werie yefetaw'

    Hello Mr Article Onwer – When Negasso was a President, the blind opposition used to call him a ‘condom’. How come now he is now labelled a well-known and well educated draftsmen of the Ethiopian constituion?

    My fellow Ethipians say ‘tornet kefetaw werie yefetaw’. Either that the strategy of the opposition or it is just a collecdtion of backward people ……..

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: