አደባባይ ወጥተህ አልቅስ የተባለ ሕዝብና ልክየለሽ ውርደቱ

Ethiopians hold up candles and a poster of their late Prime Minister

ሞትም ዲሞክራት ሆኖ ክፉና ደግ ሳይመርጥ በፈቀደው ሰዐት ያሻውን ይዞ ይሄዳል። አንዳንዶች ሰው አዋርዶ ማሰገድ ይለምዱና ሞትም የሚሰግድላቸው ይመስላቸዋል። በዚህ ምድር የሚኖሩት ለቅጽበት መሆኑን ልብ ያላሉ ልባቸው በዕብሪት የተሞላም እነሆ የስለላ ድርጅቶች መረጃ፣ የመከላከያ ሃይል ትጥቅ ወይም የዘረፉት ገንዘብ መጠን በጊዜው ከሚጠለሉበት አናሳ የሬሳ ሣጥን አልነጠላቸውም። የሀገራችን ሰው ‘ የክፉምየደጉምአንድነውመንገዱ ….. እንደመወርወርያተንጋለውሲሄዱ’ ብሎ ገጥሞ ነበር። አዎን ጥይት በማይበሳው መኪና ተሸሽገው ፣ ጥይት እንደ ውሀ የሚረጭ መሳርያ ወደ ሕዝቡ ተደግኖ በአጀብ የሚሸኙት ሰው እንደ ሻንጣ በገመድ በታሰረ ሳጥን ከብለል እያሉ ሲጫኑና ሲወርዱ ማየት እውነትም እንደ ሸማኔ መወርወርያ ተንጋሎ መሄድ ያሰኛል። በመጨረሻው ሽኝታቸው የተከናነቡት ጨርቅም የኢትዮጵያ ባንዲራ ሆኖ ተገኘ። በሶ የቁዋጠሩበት ጨርቅ እሳቸውን እንደበሶ ቁዋጥሮ ሲሸኛቸው “አልነገርኩህም ወይ ከላይ ተሰቅዬባንዲራ በደም ነው የሚቆየው ብዬ……” የሚላቸው ይመስል ይኸው ከበላያቸው ላይ አርፎ ተመለከትነው። አንሱልኝ የሚሉበት አቅም ግን አልነበራቸውም። ስንቶቻችን ይህንን አስተውለን ይሆን? ስንቶቻችን መኖርና መሞት የቅጽበት ብልጭታና ጭልምታ እንደሆነ ልብ ብለን ይሆን?

አዎን ልፍስፍሱንም፣ አገሩን እያሳረደ ቅንጣቢ የሚጠብቀውን ሆድ አደሩንም ይቺው ትንሽ ሳጥን ነች በስተመጨረሻ የምትሸኘው። ሰው የሚያስብና የሚማር እንሥሳ ነው ይባላል። ሆኖም ስለ ጥፋት ብቻ የሚያስብ ሰው ምናለበት ሳር የሚግጥ እንሥሳ ቢሆን ኖሮ ያስብላል። ሞት ለተወሰኑቱ የተመረጠ አይደለምና ማንኛችንስ ከዚያ እንቀራለን? በሚል ደግ ሰርቶ ለማለፍ፣ ይቅር ብሎ ይቅርታም ጠይቆ ለተሻለ ሀሳብ ለመሸነፍ እንዳይሞክር አንዳች የሰውን ልጅ ጭንቅላት የሚያነሆልል ስሜት አለ። እሱም ስግብግብነት፣ እብሪትና ክፋት ነው። ለነጻነት ታገልኩ ያለ ነብስ እንደምን ሆኖ ነው ለአንድ ሰው እንዲለቀስ ቆመጥ ይዞ፣ ጠመንጃ ደግኖ ደረት የሚያስመታው ብለን ስንጠይቅ አስለቃሾቹ በመለስ ሞት አሳበው የአንድ አገር ሕዝብን አንገት ማስደፋት፣ ቅስም መስበርና ዳግም ቀና እንዳይል ለማድረግ ያቀዱት ይመስላል። ይህንን ሕዝብ እንደ ሰርከስ እንስሳ አደባባይ አውጥቶ ማስለቀስ የተቆጣ እለት ቦጫጭቆ እንደሚጥል አንበሳና ነብር ጋር የመቀለድ ያህል መሆኑን ማን በነገራቸው? ይህ በሰንሰለት የታሰረ አንበሳ፣ ነብርና ዝሆን ሰንሰለቱን አይበጥስም ብሎ ማሰብ ትናንት ከትናንት ወዲያ የሆነውን ታሪክ መለስ ብሎ ያለመመልከት ነው። ይህንን ግፍ ለማን ነው እንደሚያቆዩት ግልጽ ነው። እነዚህ የወያኔ ቁንጮዎች መሮጫቸውን ያውቃሉ መሮጫ የሌላቸው ነገን የሚያዩበትን ሆድ ስላስጨፈናቸው የቀን ጎዶሎ ምነው በቀረብኝ እንዳያሰኛቸው ማሳሰብ አስፈላጊ ነው።

እናም እኒህ ሰው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ለአፍሪካም ብቻ ሳይሆን ለአለም የሚተርፉ ተብሎ የተነገረላቸው ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ደረት እንዲመታ፣ ታማሚው ከሆስፒታል በምርኩዙ፣ በረንዳ አዳሪው ከየታዛው ተሰብስቦ እሳቸው ባይኖሩ ኦክሲጅን እንኩዋን ወደ ሳንባችን አይሄድም ነበር። እያሉ እንዲያለቅሱ ሲደረግ የሚደንቅ ነው። ይህንን ሕዝብ አጥብቀው ይጠሉታልና ሊያስጎነብሱት ሊያሰግዱት ከወራሪ ጠላት ያላነሰ ግፍ እየፈጸሙበት ምን ያህል ገፍተው መሄድ እንደሚችሉ እየለኩበት ነው። የዚህ ክፋት መሀንዲሶች አደባባይ አውጥተን አስለቀስናቸው። ደረት እያስመታን በግዳቸው እንዲያነቡ አደረግናቸው።አሁን በአንድ ነገር እርግጠኞች ነን የሚሉ ይመስላል። “ኑ ትሰቀላላችሁ” ብንላቸው “ገመድ ከኛ ነው ከመንግስት?” እንዲሉ አድርገናቸዋል። የሚል የንቀትና የጥላቻ ስሜት!! የአንድ መንደር ዱርዬዎች እብሪት! የጫካ ስነልቦና!! ጣርያ የነካ ጥላቻ ነው። ብዙዎቻችን ጊዜ የምናጠፋው ለቅሶው የምር ነው ወይስ ተገደው የሚለው ጥያቄ ላይ ነው። አንዳንዶቻችንም ያለቀሱትን ታዋቂ ሰዎች እያሳነስን ነው። ጉዳዩ ከዚያ በላይ ነው። ያነሰቺው ኢትዮጵያ ነች የተዋረደቺው አገራችን ነች። አገራችን ስንል ውርደትና ሽንፈትን በእንባችን እንድንቀበለው የተደረግን ሁላችንም ነን። በውስጥም በውጭም ያለን ኢትዮጵያውያን ነን የተዋረድነው። መቀበል የሚገባን መራር እውነት ቢኖር ይኸው ነው። አስተባባሪዎቹ አቀነባባሪዎቹ ዋንኛ አልቃሾቹ ባለሀገር እኛ ነን ገዢዎቻችሁ እኛ ነን የሚሉቱ በግልጽ ከፊት ለፊት ተሰይመዋል።

ሁልጊዜ በደልን አጉልተን ስንናገር ለበዳዮችም የተመቸናቸው እኛው ነን አንልም። ኢትዮጵያን ታህል የሰለጠነች አገር ከጫካ በወጡ ወሮበሎች ይህን ያህል ዘመን ከተገዛችና ሕዝቡም ይህን ያህል ከተዋረደ ችግሩ የጠላት ትልቅነት ሳይሆን መሸነፍን በጸጋ የተቀበልን ወይም እኛን እስካልነኩን ብለን እስኪነኩን የምንጠብቅ ብዙ በመሆናችን ነው። በባለስልጣን እየታከክን ጥቅም የምንፈልግ ልፍስፍሶችና መንገድ ጠቁዋሚዎች ስለበዛን ነው ብለን ደፍረን መናገር አለብን። ተልዕኮአቸው ለስልጣን እንጂ ለነጻነት፣ ለእኩልነትና ዲሞክራሲ ያልሆነ በሕዝብ ስም ለራሳቸው ሰምና ዝና የሚተጉ የፖለቲካ መሪዎች ወይም ድርጅቶች ብዙ ስለሆኑ እንጂ የጋራ ቁዋንቁዋና የትግል ስትራቴጂ ለመንደፍ ሃያ አመት መገዛት አስፈላጊ ስለሆነ አይደለም በማለት እውነቱን ልንናገር ይገባል። እንደ ሕዝብም የምናስበውንና የምንፈልገውን የማንናገር ተመልካቾች ስለበዛን ነው ብለን የራሳችንን ድክመት አደባባይ ልናወጣ ይገባል። ታዛቢ እንጂ ተሳታፊ ባለመሆናችን ነው። አይደለም የምንል ከሆነ የሆነውን እውነት መናገር መቻል አለብን። ከዚህ በላይ ውርደት የለም። እንደ ሰርከስ እንሥሳ ከመቆጠር በላይ መገዛት የለም።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ችግር አሁን አንድ አይነት መሆኑን በአደባባይ ለቅሶ ተመልክተናል። ለዚህ 90 ውጤት አልባ የፖለቲካ ድርጅት አስፈላጊ ነው? ከዚህ ሁሉ ብጥስጣሽ ጋር ተኪዶስ የት ሊደረስ? የጠገበ ጅብ ሸኝቶ የተራበውን ለመተካት ወይስ እውነትም ለነጻነት? እንደምንመለከተው ሁሉም መሪ ሁሉም አስተባባሪ ሁሉም ስብሰባ ጠሪ ከሆነ ምናልባት የሚያዋጣው ለጉልበተኛው ሰግዶ ማደር ሊሆን ነው ማለት ነው? መንግስት የሕዝቡ ነጸብራቅ ነው ይባላል። እናም ለኢትዮጵያ ሕዝብ የሚመጥነው ወያኔ ነው ማለት ነው? እየገረፈ የሚያስለቅሰው እያስለቀሰ የሚገርፈው? አይደለም ከተባለ መንገዱ ምን ይሁን? ምንሰ መቼ ይሰራ? 85 ሚሊየን ሕዝብ ተጎትቶ ሲያለቅስ ትንተና እያቀረብን እንደወትሮው አሳፋሪን ነገር ባንድ ሰሞን ወሬ እንሸኘው?

ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች ሕዝቡ በቂ መረጃ አያገኝም የሚሉ ናቸው። ለሕዝቡ እውነተኛና ሚዛናዊ መረጃ ለማድረስ እያንዳንዱ የፖለቲካ ድርጅት ራድዮ ወይም ሌላ የመገናኛ መንገድ ይጠቀማል። በጋራ የመስራትና በመጀመርያ ሀገርን ማዳን የሁሉም እምነት ከሆነ፣ ነጻ መገናኛ ብዙሀን ለሁሉም አማካይ አቀራራቢ ወይም ‘common denominator’ ነው። ቢያንስ ጠንክሮ የወጣውንና በጥሩ ባለሙያዎች የተያዘውን ኢሳትን ድጋፍ በመስጠት በበቂ ሀይል አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር አልነበረምን? ስንት የሲቪክና የፖለቲካ ድርጅቶች ናቸው የኢሳት ደጋፊዎች? ምን ያህሉ ናቸው አስፈላጊነቱን አምነው ተፈላጊውን ድጋፍ የሰጡ? ብለን ስንጠይቅ መልሳችንን ከውጤታችን መረዳት ይቻላል። እንዲያውም አንዳንዶች ኢሳትን ራሱን ለማጥፋት ሲታገሉ ነው የምንመለከተው። ለጋራ ሀገር መሸጋገርያ የሚሆን የጋራ ሥራ መስራት የማይችሉት ወደፊትስ ምን ጥቅም ይኖራቸዋል? ብሎ መጠየቅ ጊዜው አሁን ይመስላል።

የአቅማቸውን የሚያደርጉትን ሁሉ ማድነቅና ማመስገን ተገቢ ነው። አነስተኛ ሕዝባዊ ትብብርና ድጋፍ እያገኙ ሌት ተቀን የሚማስኑ ወገኖች ድካማቸው ቀላል አይደለም። የዚያኑ ያህል ደግሞ የሚያሳዝነው እናውቅለታለን የሚሉቱ የፖለቲካ ጠበብቶች፣ የድርጅት መሪዎች አሁንም ገና የጋራ አገር ለማዳን የጋራ ቋንቋ የላቸውም። አንድ የሆነን ሕዝብ በትነው ያስበሉታል፣ በድርጅት ከፋፍለው ያስቀጠቅጡታል። የጋራ የሆነ ጠላትን በተበጣጠሰና አቅመ ቢስ ትግል አሸናፊ ሆነው ለመውጣት ጥሎ ማለፍ ውድድር ላይ ናቸው። በዚህ መንገድ እርስ በርስ ይጣጣሉ እንደሆን እንጂ ወያኔን መጣል እንደምን ይቻላቸዋል? ለወያኔም የሰላም እንቅልፍ የሰጠው የሌላው መጠላለፍ ነው። ሃያ አመት ሙሉ የትግል ንድፍ ለማውጣት ከአንድ አዳራሽ ወደ ሌላኛው መሄድ አይበቃም?

እንደ እንሥሳ ተነድቶ አልቅስ መባሉ የወያኔን እብሪት ንቀትና ጥላቻን እንጂ ለመለስ ዜናዊ ክብር ሲባል የሚያደርጉት እንዳልሆነ ከራሳቸው ሁኔታ መረዳት ይቻላል። ምክንያቱም ሙያቸው ነውና ለነርሱ መግደልና መሞት ይህን ያህል የተለየ ነገር አይደለም። የያዙትም የሙታኖችን ስም ነውና። ተዋርደን ተዋርደን እዚህ ደረጃ ከደረስን ግን ማልቀስ ለኛው ነው። ምናልባትም ሰዉ ለራሱ ውርደት ይሆናል እያለቀሰ ያለው። ማስፍታት ያልቻልናቸው የፖለቲካ እስረኞቻችን፣ ጋዜጠኞችና የሰብዓዊ መብት ተማጋቾች መታሰር ሳያንሳቸው እስርቤት ጊቢ ውስጥ ለመለስ እንዲያለቅሱ ሲደረጉ ማሰብ ህሊና አያቆስልም የሚል ማን ነው? ምን ያህል ግድየለሽ ብንሆን ነው ይህ ውርደት የማያስቆጣን። በደርግ ጊዜ ተገደን ሰልፍ ወጣን ያልን ሰዎች ከሀያ አመት በሁዋላ ተገደን እናልቅስ? ፈርተን እንዝፈን? ከዚህ ውርደት ለመውጣት የሚያስችለን የህሊና ጽናትም ሆነ የእውቀት/የገንዘብ አቅም የለንም?

የወያኔ ቁንጮ ባለመኖሩ ከሚሰማ ምቾት ይልቅ የኢትዮጵያውያን መዋረድ ሊያመን ይገባል። የ ኢትዮጵያ ሕዝብ በተመደበለት ሰዓት እየወጣ የሀገሩን ሀብት ወደ አንድ ጎጥ ጨምሮ በጠራራ ጸሀይ ልጆቹን የፈጀበትን ሰው አክብሮ ለቅሶ እንዲወጣ ማድረጋቸው ሊያመን ይገባል። ከዚህ ውርደት ለመውጣት ከግል ምኞት፣ እኔነትና ትልቅነት በላይ የሀገር ሕልውና ልቆ ሊገኝ ይገባዋል። ለዚህ መነሳት የማይችሉትን ማጀብ ማቆምም ጊዜው አሁን ነው። ሁሉ ወደ ጠላት በቻ ሳይሆን አንዳንዴ ወደራሳችንም መልከት በማድረግ መሻሻልን ማድረግ አለብን። በሃያ አመት ውስጥ አንድ ወጥ ትግል ማድረግ ካልተቻለ ለሌላ ሃያ አመት ውርደት መዘጋጀት አለብን ማለት ነው። ምርጫችን ግን አይሆንም ብሄራዊ ውርደት ይበቃናል።

ብሄራዊ ውርደት በቃ ብለን እንነሳ!!

Posted on August 28, 2012, in ETHIOPIA AMHARIC. Bookmark the permalink. 2 Comments.

  1. Shameful……….werie bicha, Meles le Ethiopia hizb Serto aberkto enji diaspora kuch bilo yehone yalhone sitsif noro almotem…….weregna hula

    • From Geleltegnaw on አደባባይ ወጥተህ አልቅስ የተባለ ሕዝብና ልክየለሽ ውርደቱ # [Pending]
      Shameful……….werie bicha, Meles le Ethiopia hizb Serto aberkto enji diaspora kuch bilo yehone yalhone sitsif noro almotem…….weregna hula
      kkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkkk anferdem yewyana abalate mesmat mayet yetsanchew endehonu enakalen bakhe werga nger nhe tebke becha>?>>

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: