የኢትዮጵያ ህዝብ በምርጫ ስም በሚደረጉ ድራማዎች መሰላቸቱን ገለፀ

ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ስርአት መገለጫ ቢሆንም ምርጫን ያካሄደ መንግስት ሁሉ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ገንብቷል ለማለት አያስችልም፡፡ በተለያዩ የአለም ክፍሎች የሚገኙ አምባገነን መንግስታት እንደሚያደርጉት ሁሉ ኢህአዴግም…. ስልጣን ከያዘበት ወቅት አንስቶ በህዝብ ይሁንታን ያላገኙ፣ በምርጫ ስም የተደረጉ ድራማዎችን አካሂዷል፤ እስከአሁን ግን ዴሞክራሲያዊ ስርአት አልገነባም፡፡

ለምርጫ የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን ሳያሟሉና ለተፎካካሪ ፓርቲዎች እኩል የመወዳደሪያ ሜዳ ሳይሰጡ “ነፃ ምርጫ” አካሄድን የሚሉት የኢህአዴግ ባለስልጣናትና ተላላኪያቸው የሆነው ምርጫ አስፈፃሚው ምርጫ ቦርድ ቆም ብለው ሊያስቡት የሚገባው አንድ ቁም ነገር አለ እሱም የኢትዮጵያ ህዝብ በምርጫ ስም የበሚደረጉ ድራማዎች መሰላቸቱን ነው፡፡

ኢህአዴግ በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርአት እንዲገነባና ኢትዮጵያውያን በነፃነት እንዲኖሩ እንደማይፈልግ ላለፉት 21 አመታት በተግባር አሳይቷል፡፡ ገዢው ፓርቲ በአምባገነናዊ እርምጃ ተፎካካሪዎቹን በማዳከም ብሎም በማጥፋት ጎልቶ ለመውጣት ችሏል፡፡ ለዚህ ያበቃው ዋንኛው ዘዴው የመንግስትነትና የፓርቲነትን ድንበር በማጥፋት ከህዝብ የሚሰበሰብን ግብርንና በብድር የሚገኘውን የመንግስት ሀብት ለፓርቲ ስራ ማዋሉ ነው፡፡ ከዚህም ጎን ለጎን የሀገሪቱ ህግ ከሚፈቅደው ውጪ በህገወጥ መንገድ ግዙፍ የንግድ ተቋማትን በማቋቋም በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ማንቀሳቀሱ ነው፡፡

ኢህአዴግ የመንግስትን መዋቅር ተጠቅሞ በግዳጅ አባላትን ከመመልመል ባለፈ የምርጫ ወቅት ሲደርስ ይሄንኑ የመንግስት መዋቅር ተጠቅሞ ህገወጥ ቅስቀሳ ያደርጋል፡፡ ዛሬ በተጀመረውና በመጪው ሳምንትም በሚደረገው የአካባቢና የከተማ አስተዳደሮች ምርጫም ኢህአዴግ የተለመደውን ድራማ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ የአሁኑ ድርጊቱ አስገራሚ እንዲሆን ያደረገው የተለመደው ህገወጥ ድርጊቱን ብቻውን እየተወዳደረም መድገሙ ነው፡፡ ለጋዜጣችን የደረሱ መረጃዎች እንደሚያረጋግጡት ኢህአዴግ በአሁኑ ምርጫም ህገወጥና አሳፋሪ በሆነ መንገድ በመንግስት መዋቅሮች በተፃፈ ደብዳቤ ከባለሀብቶችና መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች በግዳጅ ገንዘብ ሰብስቧል፣ የምርጫ ቅስቀሳ በማይፈቀድባቸው ቦታዎች(በትምህርት ቤቶችና በእምነት ተቋማት) ቅስቀሳ አካሂዷል፣ የመንግስት ንብረት በሆኑ ተሸከርካሪዎችና ቁሳቁሶች ቅስቀሳ አድርጓል፣ የመራጮች ምዝገባ ከተጠናቀቀ በኋላ በካድሬዎች አማካኝነት የምርጫ ካርድ አድሏል፡፡

እነዚህ ህገ ወጥ ተግባራት መፈፀማቸው ምርጫውንም ህገወጥ እንደሚያደርገው ግልፅ ነው፡፡ አብዛኞቹ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከላይ የተዘረዘሩት ህገወጥ ድርጊቶች እንደሚፈፀሙ አስቀድመው በመረዳታቸውና ለውድድር የሚያመቹ ሁኔታዎች ባለመኖራቸው ዛሬ በተጀመረውና በመጪው ሳምንትም በሚደረገው የአካባቢና የከተማ አስተዳደር ምርጫ ራሳቸውን አግልለዋል፡፡ ፓርቲዎቹ ከምርጫ እንዲወጡ ያስገደዳቸው መሰረታዊ ምክኒያት ኢህአዴግም ሆነ ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ ነፃ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ሜዳ አለማመቻቸታቸው ነው፡፡ በመሆኑም ኢህአዴግም ሆነ ብሔራዊው ምርጫ ቦርድ ከጥፋት ጉዟቸው በመመለስና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ያቀረቧቸውን ህጋዊ ጥያቄዎች በመመለስ ምርጫው እንዲደገም ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ይሄን ሳያደርጉ ከመቀጠሉ ግን ለገዢው ፓርቲም ሆነ ለጀሌዎቹ መዘዙ ከፋ እንደሚሆን አያጠራጥርም፡፡

Posted on April 15, 2013, in ETHIOPIA ENGLISH and tagged , , , , . Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: