የህዳሴውን ግድብ የተቃወሙት የሳውዲ ልዑል ከሃላፊነታቸው ተነሱ” የሪፖርተር አስቂኝ ዜና

የሳዑዲ የመከላከያ ሚኒስትር በኢትዮጵያ አቤቱታ ተነሱ?

የሪፖርተር አስቂኝ ዜና የሳምንቱ መዝናኛ ተደርጎ ተወስዷል። ዜናው የሚጀምረው “የህዳሴውን ግድብ የተቃወሙት የሳውዲ ልዑል ከሃላፊነታቸው ተነሱ” የሚል ነው.. የሳዑዲ አረቢያ  ምክትል የመከላከያ ሚኒስትር በቅርቡ በግብጽ ተደርጎ በነበረ የዓረብ አገሮች የውሃ ምክር ቤት ኮንፍረንስ በመገንባት ላይ ያለውን “የህዳሴ ግድብ” መቃወማቸውን በማስረጃነት ያሳየው ሪፖርተር ከዜናው ግርጌ ሚኒስትሩ ስለተነሱበት ምክንያት የሳዑዲ ፕሬስ ኤጀንሲ ያለው ነገር እንደሌለ አመልክቷል..

ሚኒስትሩ  በአገራቸው ፖለቲካ ውስጥ አወዛጋቢ ጉዳይ ማንሳታቸውን ፣ በዚህም ምክንያት  ከሃላፊነታቸው  መነሳታቸውን  የሚገልጹ ጠንካራ አስተያየቶች ከሳዑዲ እየወጡ ነው። ጉዳዩን  የሚከታተሉ ወገኖች የሚኒስትሩ መነሳት አገራቸው ውስጥ እያራመዱ ካለው ያልተለመደ እንቅስቃሴ ጋር ከመያያዙ ውጪ አባይ ግድብን አስመልክቶ ከተናገሩት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ለጎልጉል ተናግረዋል።

የህዳሴው ግድብ በማንኛውም ምክንያት የመፍረስ አደጋ ቢገጥመው ሊያጠራቅም የሚችለው 70 ቢሊዮን ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ ሱዳንን ሙሉ ለሙሉ ያጠፋል፡፡ ከዚህ አልፎም በግብፅ የአስዋን ግድብ ላይ ተጨማሪ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ነበር ምክትል የመከላከያ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡ በዚህ የኢትዮጵያ ግድብ በዋናነት ተጎጂ የምትሆነው ግብፅ መሆኗን፣ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ግብፅ ከዓባይ ውኃ ውጭ ሌላ አማራጭ የሌላት በመሆኑ ነው ብለው ነበር፡፡ በማከልም ኢትዮጵያ በዚህ ግድብ አማካይነት እያደረገችው ያለ እንቅስቃሴ ከኢኮኖሚያዊ ጥቅሙ ይልቅ ፖለቲካዊ ትንኮሳው ያመዝናል ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ዓላማ ፍፁም ፖለቲካዊ ሴራ መሆኑን በመግለጽ መናገራቸውን ሪፖርተር በዜናው መጨረሻ አስታውሷል። ኢትዮጵያም ባለስልጣኑ ለተናገሩት የሳዑዲ መንግስት ማብራሪያ እንዲሰጥበት መጠየቋ አይዘነጋም።

Posted on April 29, 2013, in ETHIOPIA ENGLISH and tagged , , , . Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a comment