ፀረ ሙስና ኮሚሽን ወደ ግሉ ዘርፍ ጎራ ሊል ነው. የፖለቲካ ድርጅቶችና የሃይማኖት ተቋማት ተዘለዋል

የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የግሉ ዘርፍ ውስጥ ያሉ ሕዝባዊ ድርጅቶች በሙስና ሊጠይቁ የሚችሉበትን የሕግ ረቂቅ አዘጋጀ፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶችና ቤተ ዕምነቶች በሕዝባዊ ተቋማት ምድብ ውስጥ ቢገኙም በእነዚህ ተቋማቶች ላይ ክንዱን ለማሳረፍ ዓይን አፋር ሆኗል..

ሕዝባዊ ድርጅቶች ተብለው በኮሚሽኑ የተዘረዘሩት መካከል የአክሲዮን ኩባንያዎች፣ የሙያና የብዙኀን ማኅበራት፣ ዩኒየኖችን ጨምሮ መሠረታዊ የኅብረት ሥራ ማኅበራትና የልማት ማኅበራት፣ ሃይማኖታዊ ተቋማት፣ የፖለቲካ ድርጅቶችና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

ከእነዚህ በተጨማሪም በቁጠባ ወይም በመድን ዋስትና አረቦን መልክ የተሰበሰበ ሀብት የሚያስተዳድሩ ተቋማት፣ ለሕዝባዊ አገልግሎት እንዲውል ታስቦ የተሰበሰበ ሀብት የሚያስተዳድሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማኅበራት በሕዝባዊ ድርጅት ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል፡፡ ነገር ግን የፀረ ሙስና ኮሚሽን ከተዘረዘሩት ሕዝባዊ ተቋማት ውስጥ የሃይማኖት ድርጅቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ አለም አቀፍ ድርጅቶች፣ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ማለትም ዕድሮችንና ዕቁቦችን በሙስና ከመጠየቅ እንደሚቆጠብ አስታውቆ፣ በሌሎች ተቋማት ግን ሕጉ በሚኒስትሮች ምክር ቤትና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደፀደቀ ምርመራውን ማካሄድ እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡

ኮሚሽኑ ባለፈው ሐሙስ የሙስና ወንጀሎችን እንደገና ለመደንገግ ባዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ላይ ከተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ከተወከሉ የሕግ ባለሙያዎች ጋር በግዮን ሆቴል መክሯል፡፡ ኮሚሽኑ ወደ ግሉ ዘርፍ በመምጣት በተለይ ሕዝባዊ ድርጅቶች ላይ አተኩሮ ለመሥራት ማሰቡ ተቀባይነት ቢያገኝም፣ ሃይማኖታዊ ተቋማትንና የፖለቲካ ድርጅቶችን አልመረምርም ማለቱ አግባብ አለመሆኑ ከተሰብሳቢዎች ተገልጾለታል፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽን በሃይማኖት ተቋማትና በፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ የሙስና ምርመራ ከማድረግ ወይም ከዚህ ረቂቅ አዋጅ ውጭ ያደረገበትን ምክንያት አብራርቷል፡፡

ኮሚሽኑ እንዳለው፣ በመርህ ደረጃ መንግሥትን ጨምሮ ከሕዝብ የተሰበሰበና ለሕዝብ ጥቅም ታስቦ የተሰበሰበ ሀብት የሚያስተዳድሩ አካላት፣ ተገቢ ጥቅም ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ጥቅም ለማስገኘት ሲጠቀሙበት በሙስና መጠየቅ እንደሚኖርባቸው ገልጿል፡፡ ነገር ግን ኮሚሽኑ በእነዚህ ተቋማት ላይ ይህንን መርህ ተግባራዊ ማድረግ ያልፈለገበትን ምክንያት ሲያስረዳ፣ የሃይማኖት ድርጅቶች ገቢ አሰባሰብ በእምነት ላይ የተመሠረተ እንጂ ለቁጥጥር አመቺ አሠራር የማይከተል ከመሆኑም በላይ፣ አንድ ሰው የዕምነት ግዴታውን ለመወጣት ገንዘብ የሰጠው የኅብረተሰብ ክፍል ስለሀብቱ አጠቃቀም ጥያቄ የማያነሳ በመሆኑ ነው ይላል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎችን ተጠያቂ ለማድረግ ያለውን አስቸጋሪ ሁኔታ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ሲገልጽም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገቢና ወጪ በድርጅቱ ከፍተኛ ካድሬዎች የሚከናወን በመሆኑ፣ ማስረጃና ምስክር ለማግኘት አስቸጋሪ በመሆኑ ነው በማለት ያስረዳል፡፡ ‹‹የሃይማኖት ተቋማትና የፖለቲካ ድርጅቶች ምርመራ ሲካሄድባቸው አንዳንድ አባላትና የፓርቲ አመራሮች መንግሥት በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ እየገባ ነው፡፡ ሊያጠቃን ስለፈለገ ነው በማለት ሊፈጥሩት የሚችሉት መደናገር፣ በሰላማችንና በልማታችን ሊኖረው የሚችለው አሉታዊ ውጤት ቀላል አይደለም፤›› ሲል ምርመራውን በእነዚህ ሁለት ተቋማት ላይ የማያደርግበትን ምክንያት ገልጿል፡፡

ከኢትዮጵያ ሕግ ባለሙያዎች ማኅበር የተወከሉት አቶ ተስፋዬ ደረሰ የኮሚሽኑን መከራከርያ አይቀበሉትም፡፡ በምክክር መድረኩ ላይ አቶ ተስፋዬ፣ ኮሚሽኑ የሃይማኖት ተቋማትና የፖለቲካ ፓርቲዎች በዚህ አዋጅ እንዳይካተቱ ያቀረበው መከራከርያ ሚዛን እንዳልደፋ ገልጸዋል፡፡ ሁለቱም ተቋማት እንዳይካተቱ የተቀመጠው ከሰላምና ፀጥታ ጋር፣ እንዲሁም ማስረጃ ከማግኘት አንፃር አስቸጋሪ ነው የሚለው ነጥብ እንዳላረካቸው አቶ ተስፋዬ ገልጸው፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች በተለይም ገዥው ፓርቲ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያንቀሳቀስ በመሆኑ በረቂቅ ሕጉ ሊካተት ይገባል፡፡ ማስረጃ በማግኘት በኩልም ፀረ ሙስና ኮሚሽን የራሱን ብቃት ማሳደግ እንጂ ተቋማቱን በሕጉ አለማካተት መፍትሔ ነው ብለው እንደማያምኑ አስረድተዋል፡፡

በአክሲዮን ሽያጭ እየተቋቋሙ ያሉ በተለይም ከባንኮችና ከኢንሹራንስ ኩባንያዎች ወጣ ያሉ አክሲዮን ኩባንያዎች ከአባላቶቻቸው በየጊዜው ቅሬታ እየቀረበባቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ባንኮችና ኢንሹራንሶች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ጠበቅ ያለ ቁጥጥር የሚያካሂድባቸው በመሆኑ ብዙም ቅሬታ እየተደመጠባቸው አይደለም፡፡ ነገር ግን ከሦስት ዓመታት ወዲህ የልማት ሥራዎችን፣ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ለማቋቋም እየተቋቋሙ የሚገኙ አክሲዮን ኩባንያዎች ላይ ግን ቀላል የማይባል ቅሬታ ከባለአክሲዮኖች እየተሰማ ይገኛል፡፡

ከእነዚህ በተጨማሪም የሙያና ብዙኀን ማኅበራትና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ላይም አልፎ አልፎ ቅሬታ መቅረቡ አልቀረም፡፡ ምንም እንኳ በቤተ እምነቶችና በፖለቲካ ድርጅቶች አካባቢ ያለው ሙስና ይፋ ባይወጣም ውስጥ ውስጡን የሚብሰለሰሉ ምዕመናንና ፖለቲከኞች እንዳሉ ይነገራል፡፡  የፀረ ሙስና ኮሚሽን ያረቀቀው ሕግ ከፀደቀ በእነዚህ ተቋማት ላይ ዕርምጃ ይወስዳል ተብሎ ሲጠበቅ፣ በቤተ እምነት ተቋማትና በፖለቲካ ድርጅቶች ልዩ ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ ለጊዜው ዝምታ መምረጡ ያልተዋጠላቸው አሉ፡፡ ኮሚሽኑ እንደገለጸው በቀጥታ በዕምነት ተቋሙ ላይ ዕርምጃ ከመውሰድ ይልቅ የዕምነት ተቋማት የሚያቋቁሟቸውን የልማት ድርጅቶች እንደሚመረምር አስታውቋል፡፡

በዚህ ረቂቅ አዋጅ ላይ ከፍተኛ ተሳትፎ የነበራቸውና በረቂቅ አዋጁ ላይ ለመምከር ለተሰበሰቡት ባለሙያዎች ማብራሪያ የሰጡት የሕግ ባለሙያው አቶ ኃይሉ በርሄ፣ የፀረ ሙስና ኮሚሽን የተመዘበረ የመንግሥት ሀብት እንደሚያስመልሰው ሁሉ የተመዘበረን የግሉ ዘርፍ ሀብት እንደሚያስመልስ አስረድተዋል፡፡

Advertisements

Posted on June 9, 2013, in ETHIOPIA AMHARIC. Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: