ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ አይሲሲን በዘረኝነት ከሰሱ

ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ከአፍሪካ ጋር አንድ ዓይነት ቋንቋ ማውራት ተስኖታል፡፡

50ኛ ዓመቱን በቅርቡ ያከበረው የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የመሪዎች ጉባዔ መጠናቀቅን አስመልክተው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አይሲሲን በዘረኝነት የከሰሱ ሲሆን፣…. ፍርድ ቤቱ ተጠያቂነትን ለማረጋገጥና ከወንጀል ድርጊት ተጠያቂነት የሚያመልጡን ለመያዝ የተቋቋመ ቢሆንም፣ አፍሪካውያኑን ማደን ብቸኛ ሥራው መሆኑን ኅብረቱ እንደሚቃወም ገልጸዋል፡፡ የኅብረቱን ተቃውሞ ለተመድ ለማቅረብም መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል፡፡

አይሲሲ እስካሁን የጥፋተኝነት ውሳኔ ያሳለፈው በኮንጎው ቶማስ ሉባንጋ ላይ ብቻ ሲሆን፣ ክስ የቀረበባቸው 30 ተጠርጣሪዎችና በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው ያሉ 12 ግለሰቦች የተገኙት ከኡጋንዳ፣ ከኮንጎ፣ ከመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ከሱዳን፣ ከኬንያ፣ ከጊኒ፣ ከኮትዲቯርና ከሊቢያ ነው፡፡ ኅብረቱ የተካረረ አተካሮ ውስጥ ከአይሲሲ ጋር እንዲገባ ያደረገው ፍርድ ቤቱ ትኩረቱን ከአፍሪካ አኅጉር ያላነሳ በመሆኑ ነው፡፡

አይሲሲ በ2001 ዓ.ም. በሱዳኑ ፕሬዚዳንት አል በሽር ላይ የእስር ትዕዛዝ በመቁረጡ የተነሳ ትልቅ ውዝግብ ተነስቶ ነበር፡፡ በሥልጣን ላይ ያለን ፕሬዚዳንት በመክሰሱ ፍርድ ቤቱ በሱዳን ያለውን የሰላም ሒደት እንዳያበላሽ ሥጋት እንዳደረበት በወቅቱ ኅብረቱ አስታውቆ ነበር፡፡

በ1999 ዓ.ም. የኬንያ ጠቅላላ ምርጫን ተከትሎ በተከሰተው ብጥብጥ እጃቸው አለበት የተባሉ ከፍተኛ የኬንያ ባለሥልጣናትን ጉዳይ ለመመርመር የአይሲሲ ዋና ዓቃቤ ሕግ የነበሩት ሉዊዝ ሞሪኖ አካምፖ ከፍርድ ቤቱ ፈቃድ በመጠየቃቸው፣ በ2002 ዓ.ም. ፍርድ ቤቱ ፈቃድ በመስጠቱ ምርመራ ጀምረዋል፡፡

በኬንያው ምርጫ የምዋይ ኪባኪ አሸናፊነት ከተገለጸ በኋላ በኪባኪ ብሔር በኪኩዩና በዋነኛው ተቃዋሚ በራይላ ኦዲንጋ ብሔር በሉዎ ብሔር መካከል ከፍተኛ ብጥብጥ የተከተለ ሲሆን፣ ይህን ለመመርመር የቀረበው የዋና ዓቃቤ ሕጉ ጥያቄ በራሱ ተነሳሽነት የተመረመረ የመጀመሪያው ጉዳይ ነበር፡፡

በሚያዝያ 2005 ዓ.ም. የኬንያ አራተኛው ፕሬዚዳንት በመሆን ቃለ መሃላ የፈጸሙት ኡሁሩ ኬንያታና ምክትላቸው ዊሊያም ሩቶ በሰኔ ወር መጨረሻ ላይ በኔዘርላንድ ዘ ሄግ በሚገኘው አይሲሲ እንዲቀርቡ ቀነ ቀጠሮ ተይዞላቸዋል፡፡ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝና ሌሎች የአፍሪካ መሪዎችን ያበሳጨውም ይኼው ጉዳይ ነው፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ኅብረቱን በመወከል አይሲሲ በኬንያ ፕሬዚዳንት ላይ የጀመረውን ክስ እንዲያቋርጥ ጥሪ ሲያቀርቡ፣ በሕዝብ ይሁንታ የተመረጠን መሪ ከስድስት ዓመት በፊት ብጥብጥ አስነስተሃል ብሎ ተጠያቂ ማድረግ ከአፍሪካዊ የፍትሕ እምነት ጋር የሚቃረን መሆኑን በመጠቆም፣ የአፍሪካ ኅብረት የአኅጉሩን ክብርና ሉዓላዊነት ለመጠበቅ እንደሚሠራና ጉዳዩን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) እንደሚያቀርብም አስታውቀዋል፡፡

የአፍሪካ ኅብረት የወቅቱ ሊቀመንበር የፍርድ ቤቱን ዓላማ እንደማይቃወሙ ገልጸው በዘር ማጥፋት፣ በጦር ወንጀል፣ በሰብዓዊነት ላይ በሚቃጣ ወንጀል የተሳተፉ ሰዎች ተጠያቂ እንዲሆኑ አፍሪካ ኅብረት ድጋፍ የሚሰጥ ቢሆንም፣ በሁለት የተለያዩ መስፈርቶች መሥራቱን ከቀጠለ ግን ኅብረቱ ከፍርድ ቤቱ ጋር በምንም መንገድ ተባብሮ የማይሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ከአራት ዓመት በፊት በተመሳሳይ ምክንያት በሱዳን ፕሬዚዳንት አል በሽር ላይ የተከፈተው ክስ እንዲቋረጥ ኅብረቱ ጠይቆ የነበረ ሲሆን፣ የኬንያው ለየት የሚለው ኬንያ የፍርድ ቤቱ አባል ከመሆኗም ባሻገር ጉዳዩን ለፍርድ ቤቱ የመራው ራሱ የኬንያ መንግሥት መሆኑ ነው፡፡

አይሲሲ እንዲቋቋም ከአፍሪካ ኅብረት አባል አገሮች ከ30 በላይ አገሮች ድጋፍ የሰጡት ቢሆንም፣ ባለፉት 11 ዓመታት ዓይኖቹን ከአፍሪካ ውጪ አላሳርፍ ያለው አይሲሲ በተራው በአፍሪካውያኑ ዓይንህ ለአፈር እየተባለ ይገኛል፡፡ 70 በመቶ የሚሆነውን ሕዝብ የሚወክሉ አገሮች የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት የሆኑትን አሜሪካ፣ ቻይናና ሩሲያን ጨምሮ የፍርድ ቤቱ አባላት አይደሉም፡፡

የሰላምና የፍትሕ ክርክር

አፍሪካውያን ከፍርድ ቤቱ ጋር እንዳይስማሙ ካደረጋቸው ምክንያቶች መካከል ለሰላምና ለፍትሕ ሊሰጥ በሚገባው ትኩረት ላይ ያላቸው የአመለካከት ልዩነት ዋነኛው ነው፡፡ አፍሪካውያኑ ፍትሕ ሁልጊዜም ከሰላም መቅደም የለበትም የሚል ክርክር የሚያቀርቡ ሲሆን፣ የአይሲሲ ዋነኛ መርህ ፍትሕን በምንም ነገር ላይ ማንገስ ነው፡፡ አንዳንድ አፍሪካውያን እንዲያውም የፍትሕ ምንነት ለአፍሪካና ለምዕራባውያን አንድ ዓይነት ትርጉም እንደሌለው በመጠቆም፣ ባህላዊ ሕጎችና ማኅበራዊ እሴቶች ከምዕራባውያን የእስርና የበቀል መፍትሔ ይልቅ ለይቅርታና ለሰላም ትኩረት እንደሚሰጡ ይከራከራሉ፡፡

በምዕራባዊያን የፍትሕ ሞዴል የተቀረፀው አይሲሲን 36 የአፍሪካ አገሮች በአባልነት ከታቀፉበት በኋላ ስለአመለካከት ልዩነት ማውራታቸው ሰበብ ፍለጋ እንደሆነ የሚተቹ በርካቶች ናቸው፡፡ የዓለም አቀፍ የወንጀል ሕግ ኤክስፐርት የሆኑት ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም በጉዳዩ ላይ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ ‹‹ቅጣቱ እኮ ሊዘለልም ይችላል፡፡ ማኅበረሰቡም ይቅርታ ሊያደርግለት ይችላል፡፡ ዋናው ቅጣቱ ሳይሆን ተጠያቂነቱ ነው፡፡ በአካባቢው እርቅና ሰላም እንዲወርድ ከተፈለገ ቅጣቱን መዝለል ወይም በይቅርታ ማለፍ ይቻላል፡፡ ተጠያቂነት ግን በምንም ዓይነት መንገድ መዝለል አይገባም፡፡ … ፍትሕ ሁሉን አቀፍ የሆነ መብት ነው፡፡ አፍሪካ የተለየ ፍትሕ የለውም፡፡ የሰው ልጅ ፍላጎት ተመሳሳይ ነው፤›› ብለዋል፡፡

አፍሪካ ላይ ማነጣጠር

ፍርድ ቤቱ እስካሁን ሥራው በአፍሪካ የተወሰነው በዕቅድ እንዳልሆነ ይገልጻል፡፡ የጉዳዮቹ ክብደት፣ የማስረጃ መገኘትና የአገሮቹ ጉዳዮችን ለፍርድ ቤቱ የመምራት ውሳኔ አፍሪካዊ ተኮር ለመሆን አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ገልጾ፣ ፍርድ ቤቱ ሥራውን እየሠራ ያለው በሕግ በመመራት ብቻ መሆኑን ይጠቁማል፡፡

በሌላ በኩል በሌሎች አካባቢዎች ይበልጥ አሰቃቂ ወንጀሎች እየተፈጸሙ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ ትኩረቱን አፍሪካ ላይ ያደረገው በምዕራባውያን የፖለቲካ ስሌት እየተመራ መሆኑን በመጥቀስ ፍርድ ቤቱ የፍትሐዊነት ችግር እንዳለበት የሚከራከሩ በርካቶች ናቸው፡፡ ኡጋንዳዊው የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ የመንግሥት አስተዳደር ፕሮፌሰር ማህሙድ ማምዳኒ ፍርድ ቤቱ በአሜሪካ ብሔራዊ ፍላጎት እንጂ በፍትሕ መርሆዎች ዙሪያ እንደማይሠራ በስፋት ጽፈዋል፡፡

ዶ/ር ያዕቆብ ኃይለ ማርያም ፍርድ ቤቱ በሌሎች ቦታዎች ይበልጥ ሊሠራ ቢገባም፣ በአፍሪካ ላይ አነጣጥሯል ብለው እንደማያምኑ ይገልጻሉ፡፡ ‹‹በሌላ አካባቢ የማይከሰቱ አሰቃቂ ወንጀሎች በአፍሪካ አኅጉር በጣም የተለመዱ ናቸው፤›› ይላሉ ዶ/ር ያዕቆብ፡፡ የደኅንነት ተንታኝ የሆኑት ዶ/ር ሰለሞን አየለ በበኩላቸው፣ አይሲሲ አፍሪካ ላይ ያነጣጠረ ሥራ መሥራቱ እውነትነት እንዳለው ጠቁመው ፍርድ ቤቱ ሌሎች አካባቢ የሚከሰቱ ወንጀሎች ላይ ምንም ነገር አለመሥራቱ አሳሳቢ ቢሆንም፣ በአፍሪካ ከባድ የአይሲሲ ጣልቃ ገብነትን የሚጋብዙ ጥሰቶች ስለመከናወናቸው ግን ይቀበላሉ፡፡ የኬንያ ተወላጅ የሆኑት አሜሪካዊው የቡፋሎ የሕግ ትምህርት ቤት ዲን የሆኑት ማክዋ ሙቱዋ ደግሞ፣ ፍርድ ቤቱ ሌሎች አካባቢዎች አልሠራም በማለት የአፍሪካ መንግሥታት ለአይሲሲ ያለባቸውን ግዴታ ላለመወጣት ምክንያት እየፈጠሩ እንደሆነ ይከሳሉ፡፡

ብዙ አፍሪካውያን ግን በኢራቅ፣ በአፍጋኒስታን፣ በጋዛ፣ በሶሪያ፣ በየመን፣ በባህሬንና በመሳሰሉ ቦታዎች የተከሰቱትን አሰቃቂ ወንጀሎች ለማየት ምንም ዓይነት ጥረት ያላደረገው አይሲሲ፣ የዓለም አቀፍ ፖለቲካ ሰለባ በመሆኑ አቅም አልባና ደሃ የአፍሪካ አገሮች ላይ ስለመዝመቱ እንደሚስማሙ የተለያዩ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡

የአይሲሲ ደጋፊዎችና ምዕራባውያን ሚዲያዎች እንዲሁም የአፍሪካ መንግሥታት ተቃዋሚዎች ግን የአፍሪካን የውስጥ ችግር ለመሸፋፈን መንግሥታቱና ኅብረታቸው ከአይሲሲ ጋር አተካሮ ውስጥ መግባታቸውን ያስረዳሉ፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምን ትችት ተከትሎ ‹‹ዘ ኢኮኖሚስት›› መጽሔት ባወጣው ጽሑፍ ‹‹ለምሳሌ ፍርድ ቤቱ አፍሪካ ላይ ያነጣጠረው አኅጉሩ ከመጠን ያለፈ መጠነ ሰፊ የእርስ በርስ ጦርነት ስላስተናገደና የሕግ ሥርዓቱም በአጠቃላይ መሠረት አልባ ስለሆነ ነው፤›› ሲል አስፍሯል፡፡

አንዳንድ አፍሪካዊ ምሁራን ደግሞ ሁለቱ ተቋማት ተቀራርበው በመሥራት አሁን ያለውን የቅያሜ ስሜት መለወጥ እንዳለባቸው የሚመክሩ ሲሆን፣ እግረ መንገዳቸውንም አፍሪካ የውስጥ ጉዳይዋን በግልጽነት ማየት እንዳለባት ይመክራሉ፡፡ ደቡብ አፍሪካዊው ማክስ ዱ ፕሌሲስ ‹‹The International Criminal Court that Africa Wants›› በተሰኘ ሥራቸው በአፍሪካ ያሉ የወንጀል ተጠቂዎች ቁጥር ከየትኛውም ዓለም ካለው የበለጠ በመሆኑ፣ ፍርድ ቤቱ ከመንግሥታቱ የበለጠ ለዜጎች እንደሚያስፈልግ ይጠቁማሉ፡፡

ብሔራዊ የፍትሕ ሥርዓቶች

አይሲሲ ጉዳዮችን ከመውሰዱ በፊት ብሔራዊ የሕግ ሥርዓቶች በቅድሚያ መፍትሔ የመስጠት መብታቸውን እንዲያሟጥጡ ያበረታታል፡፡ ብሔራዊ የሕግ ሥርዓቶች ጉዳዮችን ለማየት ፈቃደኛ ካልሆኑና አቅም ከሌላቸው ግን ፍርድ ቤቱ ለጉዳዮቹ መፍትሔ የመስጠት ሥልጣን ይኖረዋል፡፡

የአፍሪካ አገሮች ብሔራዊ የፍትሕ ሥርዓት ብቃትና ከፖለቲካ የፀዳ ነፃ ውሳኔ የመወሰን ጉዳይ ግን በርካታ ጥያቄ ይቀርብበታል፡፡ የኬንያ መንግሥት ለምሳሌ ጉዳዩን ለአይሲሲ የመራው አቅም እንደሌለው በመግለጽ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የአፍሪካ ኅብረት ኬንያ መልሳ ጉዳዩን በብሔራዊ የፍትሕ ሥርዓቷ እንድታይ ዕድል እንዲሰጣት ጠይቋል፡፡ የብጥብጡ ሰለባዎች የሆኑ 150 ሰዎችን የወከለው ኬንያዊው ጠበቃ ዊልፍሬድ ንዴሪቱ ለቢቢሲ እንደገለጸው፣ ኬንያ ጉዳዩን እንድትዳኝ ዕድል ቢሰጣት የምስክሮቹ ደኅንነት አደጋ ውሰጥ እንሚወድቅና የኬንያ ፍርድ ቤትም ውስብስብ የሆኑ ዓለም አቀፍ የወንጀል ጉዳዮችን ለማዬት ብቃቱ እንደሌለው ገልጿል፡፡

ጉዳዮችን ለአይሲሲ ማስተላለፍ

አይሲሲ ጉዳዮችን እንዲመረምርና እንዲከስ ጥቆማ የመስጠት ወይም የመምራት መብት ለአገሮች (አባል ለሆኑ ወይም ላልሆኑ)፣ ለግለሰቦችና ለድርጅቶች የተሰጠ ነው፡፡ የተመድ የፀጥታው ምክር ቤትም የራሱ ሚና አለው፡፡

ፍርድ ቤቱ ከእነዚህ ሁሉ አማራጮች መረጃ ወይም ጥቆማ የማግኛ መንገዶች ውጪ በራሱ ተነሳሽነት ጉዳዮችን የማየት ሥልጣን አለው፡፡ ይሁን እንጂ ከአገሮች በተለይም ከአባል አገሮች ጉዳዮች ከተመሩለት ቅድሚያ ሰጥቶ ይሠራል፡፡

የአይሲሲ የቀድሞው ዋና ዓቃቤ ሕግ ሉዊዝ ሞሪኖ አካምፖ በአፍሪካ ላይ ትኩረት ለምን እንደሚያደርጉ ሲጠየቁ ‹‹በአብዛኛው ጉዳዮቹ በአፍሪካ መንግሥታት የተመሩ ስለሆነ ነው፤›› የሚል ምላሽ ይሰጡ ነበር፡፡ በእርግጥም ኬንያ፣ ኡጋንዳና ኮንጎ ጉዳዮቻቸውን ወደ አይሲሲ መርተዋል፡፡ ዶ/ር ሰለሞን አየለ አይሲሲ በአሁኑ ወቅት እያያቸው ካለው 18 ጉዳዮች ውስጥ 12 ያህሉ ጉዳዮች በመንግሥታቱ በራሳቸው የተመሩ መሆናቸውን አስታውሰው፣ ፍርድ ቤቱ በአፍሪካ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ራሳቸው አፍሪካውያኑ አስተዋጽኦ እንዳደረጉ ያስረዳሉ፡፡

ነገር ግን ይህ ጉዳዮችን ወደ አይሲሲ የመምራት ውሳኔ በአፍሪካ መንግሥታት በነፃነትና በሙሉ ፍላጎት የተሰጠ አለመሆኑን የአፍሪካ መሪዎችና ምሁራን ይጠቁማሉ፡፡ በኬንያ፣ በኮንጎና በኡጋንዳ ጉዳዮች ወደ ፍርድ ቤቱ እንዲመሩ ራሱ አይሲሲና ምዕራባውያን የውትወታ ሥራ በመሥራትና በሌሎች ጫና በሚያሳድሩ ሁኔታዎች መገፋፋታቸው ተዘግቧል፡፡ የኬንያና የኡጋንዳ መንግሥታት በኋላ ላይ በጉዳዮቹ መመራት ላይ ያሳዩት የሐሳብ ለውጥም ከዚህ አንፃር መታየት እንዳለበት የሚጠቁሙ በርካቶች ናቸው፡፡ ለምሳሌ የኡጋንዳው መሪ ዩዌሪ ሙሴቬኒ አይሲሲ ምዕራባውያን በአፍሪካ የፈለጉትን መሪ ለመጫን ያልፈለጉትን መሪ ለማውረድ መሣሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል በቅርቡ ተናግረዋል፡፡

‹‹ፓክታ ሱንት ሰርቫንዳ››

‹‹ፓክታ ሱንት ሰርቫንዳ›› የላቲን ሐረግ ሲሆን ትርጉሙም ‹‹ቃል ከገባህ ፈጽመው›› እንደማለት ነው፡፡ በሌላ አባባል ስምምነት ከፈጸምክ ትገደዳለህ እንደማለት ነው፡፡ ይህ የዓለም አቀፍ ሕግ መርህ ለአይሲሲ የሚሠራ አይመስልም፡፡

ለአይሲሲ ሥራ ቀጥተኛ ሚና ያለው የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባላት መካከል አሜሪካ፣ ቻይናና ሩሲያ የአይሲሲ አባል አይደሉም፡፡ የሚገርመው ግን እነሱ በማያምኑበት ፍርድ ቤት ሌሎች አገሮችን አባል ባይሆኑም እንኳን የማስገደድ ሥልጣን ያላቸው መሆኑ ነው፡፡ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ያልፈረመ አገር አስገዳጅ ተፈጻሚነትን የሚያስወግድ ቢሆንም፣ የሮም ስምምነት ያልፈረሙ አገሮች ግን ለምሳሌ ሱዳን በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ይተላለፍባቸዋል፡፡

በተለይ ደግሞ የአሜሪካ አቋም በጣም ግራ የሚያጋባ ነው፡፡ በአንድ በኩል ፍርድ ቤቱ የአወቃቀርና የሥልጣን ወሰኑ ላይ ችግር አለበት በማለት ትቃወማለች፡፡ በዚህም የተነሳ አባል ካለመሆኗም በላይ ሕግ በማውጣትና ከየአገሮቹ ጋር ዜጎቿን ለአይሲሲ አሳልፈው እንዳይሰጡ የሁለትዮሽ ስምምነት በመፈራረም ራሷን ታርቃለች፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለአይሲሲ የገንዘብና ሌሎች ትብብሮችን ታደርጋለች፡፡ ተጠርጣሪዎችን አሳዳ በመያዝ ሁሉ ትተባበራለች፡፡ ከዚያም በፀጥታው ምክር ቤት አባልነቷ እንዳ ሱዳን ያሉ ጉዳዮችን ለአይሲሲ ትመራለች፡፡

የአፍሪካ አይሲሲ

በወንጀል ኃላፊነት ያለባቸውን ለመጠየቅ አይሲሲ አስፈላጊ እንደሆነ በመርህ ደረጃ ሁሉም ይቀበላሉ፡፡ በተለይ ለወንጀል ተጠቂዎች ተቋሙ አስፈላጊ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ነገር ግን እስካሁን የአይሲሲ የ11 ዓመታት የአፈጻጸም ብቃት ተቋሙ በዓለም አቀፍ ፖለቲካ የተጠቃ መሆኑን ያረጋገጠ ነው፡፡ በርካታ አባላት ያሉዋት አፍሪካ ተቋሙን ለማስተካከል ልትሠራ እንደምትችል ግምቶች አሉ፡፡

ይሁንና ባለፈው ዓመት የፀደቀው የአፍሪካ የፍትሕና የሰብዓዊ መብቶች ፍርድ ቤት ማሻሻያ ፕሮቶኮል አይሲሲ የሚያያቸውን ከባድ ዓለም አቀፍ የወንጀል ድርጊቶች የአፍሪካው ፍርድ ቤት እንዲያያቸው ውሳኔ ላይ መደረሱና የወንጀል ችሎቱን በታንዛኒያ አሩሻ አቋቁሞ የሰው ኃይል መቅጠሩ፣ ከአዲሷ አፍሪካዊት ዋና ዓቃቤ ሕግ ጋር ለመሥራት ይበልጥ እንደሚቸገር አመላካች ነው፡፡ ሁለቱም ፍርድ ቤቶች ተመሳሳይ ሥልጣን መያዛቸውም የሚያሳየው የአይሲሲና የአፍሪካ ስምምነት የአጭር ጊዜ ፕሮጀክት አለመሆኑን ነው፡፡

Advertisements

Posted on June 17, 2013, in ETHIOPIA AMHARIC. Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: