ስደት ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን

ታክሎ ተሾመ
በየዓመቱ ከግንቦት 6 እስከ 20 2013 ዓ.ም ድረስ የስደተኞች ቀን ታስቦ እንደሚውል ይታወቃል። ስለሆነም የዚህች አጭር ጽሁፍ ዓላማ በሱዳን የስደተኞች ኑሮ ምን ይመስል እንደነበር አንዳንድ የኑሮ ትዝታዎችን ተመልሰን እንድናስታውስ ይረዳ ዘንድ ለመዳሰስ ነው…

suda-MMAP-md_61905628_sudan_meroe_pyramids_g
በወረሃ የካቲት 1966 ዓ.ም የፈነዳውን አብዮት ደርግ የፖለቲካ ፈሩን ብቸኛ አድርጐ ለመምራት ባለው ፍላጐት በለውጥ ሃዋሪያ አማካኝነት በአገሪቱ ለውጡን አስፋፍቶ ተማሪውና ሕዝቡ የሶሻሊዝምን ርዕዮት–አለም እንዲቀበል ዓላማውን ተግባራዊ ለማድረግ የተቻለውን ሁሉ አድርጓል።

ባንፃሩ አብዮቱ አሻፈረኝ ላለው ሕይወት መጥፊያ ከመሆኑም ሌላ አጋልጥ፤ ተጋለጥ በማለት በሕዝቡም ሆነ በወጣቱ ዘንድ መተማመን እንዳይኖር ተፈጠረ። በዚህ ወቅት ብዙ ተማሪዎች፤ የተወሰኑ ወታደሮችና ስቪሎች ሕይወታቸውን ለማዳን ሲሉ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ እየሄዱ ትጥቅ ትግል ጀመሩ። የጫካ ትግል የጀመሩት በሚንቀሳቀሱበት አካባቢ ነዋሪውን ሕዝብ ከጐናቸው ለማሰለፍ ከፍተኛ እንቅስቃሴ ያደረጉበት ወቅት ነበር።

መንግሥት የጫካውን ትግል ለማምከን አማጺያን አሉበት በሚባለው አካባቢ ፀጥታውን ለማስከበር ከፍተኛ ጦር ላከ። ደርግን የሚቃወሙ አርሶ አደሮች ሳይቀር እርሻውንና ቀዩውን በመልቀቅ ወደ ዋና ዋና ከተሞች የሄደበትም ጊዜ ታይቷል። በዚህ የተነሳ የገጠሩ ምርት እየቀነሰ የኑሮ ውድነት አሻቀበ። የኤርትራን መገንጠል የሚደግፉ ሰላም እንዲደፈርስ የሚፈልጉ የግርግሩን አጋጣሚ በመጠቀም የተገንጣዮች ትግል እንዲጠናከር በስውርም ሆነ በገሃድ እየደገፉ አማጺያን ከአጐራባች አገራት ጋር እየተገናኙ ኃይላቸውን አጠናከሩ።

በሰሜን ጐንደር የታጠቀውን የኢዲዩን ጦርና ሌሎችን የሚደግፉ አርሶ-አደሮች በብዛት ተቀላቀሉ። በዚህ ጊዜ ሕዝብ አገሩን እንዲከላከል በሚል መንግሥት የክተት አዋጅ አወጀ። ቢሆንም ሽምቅ ተዋጊዎች ሕዝቡን እየሰበሰቡ መንግሥት በግዳጅ ሊያዘምታችሁ ነው እያሉ መጠነ ሰፊ ቅስቀሳ አደረጉ። በክተት አዋጅ የዘመተው አርሶ-አድርም ሆነ ተማሪ ከመንግሥት ጋር ሆድና ጀርባ ሆነ። እንዲሁ የመደበኛ ጦሩ ቁጥር እየቀነሰና እየላላ ሽምቅ ተዋጊዎችን መመከት ስላልተቻለ በአገሪቱ ሰላም ደፈረሰ።

በዝናብ እጥረት ምክንያት በተወሰኑ ክፍላተ-ሀገራት ድርቅ ተከሰተ። ከጦርነቱ ባልተናነሰ ሁኔታ የምግብ እጥረት መኖሩን መንግሥት ሲገነዘብ በድርቅ የተጠቃውን አካባቢ ለም ወደ ሆነና ነዋሪ ባልበዛበት አካባቢ በሰፈራ መልክ አደራጅቶ ራሳቸውን በራሳቸው እንዲያስተዳድሩ ማስፈር ጀመረ። ነገር ግን መንግሥት ሰፈራውን እንደመፍትሄ ቢመለከተውም ሰፋሪው ለቤተለሰቡ መለያየትና ለተቃዋሚዎች የእርስ በርስ ግጭት ሰለባ ከመሆን አልዳነም።

በአገሪቱ በተከሰተው ድርቅ ምክንያት ችግሮች እየተባባሱ ሲመጡ ዓለም አቀፍ የእርዳታ ሰጭ ተቋማት በሱዳን በኩል እያደረጉ በሰሜኑ በጐንደርና በትግራይ በኩል እየተንቀሳቀሱ የምግብ እርዳታ ያደርጉ እንደነበር ይታወሳል። ይሁን እንጂ ሠራተኞች ተቀጥረው ሰፋሪውን በመርዳት ላይ እያሉ በሽምቅ ተዋጊዎችና በመንግሥት በኩል በሚደረጉ የተኩስ ልውውጦች አልፎ አልፎ ጥቃት ይደርስባቸው ነበር። ግድያና ዝርፊያ በዝቷል በማለት እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ተቸገሩ። ተገንጣይ ቡድኖች አጋጣሚውን በመጠቀም ደርግን ለዓለም ማኅበረሰብ ለማሳጣት በረሃብ የተጐዳውን ወገን ፎቶ እያነሱ የፕሮፓጋንዳ መጠቀሚያ አደረጉት። የአካባቢው ሕዝብም ከችግርና ከጦርነት ለማምለጥ ሲል ብዙ ሕዝብ ወደ ሱዳን ተሰደደ።

ከላይ ለመግቢያ ያህል ይህን ካልኩ ዘንዳ ኢትዮጵያዊ ሰደተኞች የሱዳን ኑሮ ምን ይመስል እንደነበር አንዳንድ ሁኔታዎችን ላንሳ። እንደሚታወቀው በአገሪቱ በከፍተኛ ደረጃ ረሃብም ሆነ ጦርነት የተካሄደበት አካባቢ በኤርትራ፤ በትግራይና በከፊል ጐንደር አካባቢ ነው። ከሌላው ክፍለ-ሀገር በተለየ መልኩ የስደተኛው ቁጥርም እያደገ ወደ ሱዳን የሚሰደደው በነዚህ ክፍላተ-ሀገራት ነበር።

እግሬ አውጭኝ ያለው ስደተኛ ሱዳን ለመድረስ አብዛኛው በእግሩና በከብት ጀርባ በመጓዝ ነበር። በዚህ ወቅት መንገድ ላይ በረሃብና በንዳድ በሽታ እየተጠቁ አንዳንዶች ካሰቡት ቦታ ሱዳን ሳይደርሱ ሕይወታቸው አልፏል። አንዳንዶችም የተለያዩ ችግሮችን ተቋቁመው መንገዱ ተሳክቶላቸው ለሱዳን ጠረፍ ጠባቂ እጃቸውን እየሰጡ የፖለቲካ ጥገኝነት ጠየቁ።

የሱዳን መንግሥት በእጃዙር የደርግን ውድቀት ይፈልግ ስለነበር ስደተኛውን እየተቀበለ በአምራኩባ፤ በገዳሪፍ፤ በደባዚን; በፖርት ሱዳን፤ በከሰላ፤ በተዋባ፤ በወዲ ሸሪፍ፤ ወዲከውሊ፤ ሶፋዋ ወዘተ ወደ ተባሉ ቦታዎች የስደተኛ መጠለያ ጣቢያዎች ተከፈቱ። በመሆኑም የሱዳን መንግሥት የስደተኛውን ጥያቄ እየተቀበለ የውጭ እርዳታ እንዲጐርፍ አደረገ። የተለያዩ የእርዳታ ሰጪ ድርጅቶች እየተዘዋወሩ የስደተኛውን መጠለያ እየጐበኙ ቢሮ ከፍተው ለስደተኛው እርዳታ ይሰጡ ነበር። በወቅቱ ይቀርብ የነበረው የእርዳታ ዓይነት ብርድ ልብስ፤ ዘይት፤ ዱቄት፤ ተምር፤ ስኳር ወዘተ ሲሆን የመጠለያው ዓይነት ደግሞ ሸራ ድንኳን ይሰጥ ነበር።

ስደተኛው ከተወለደበት አገር ተሰዶ ሱዳን ሲሰባሰብ የሃይማኖትም ሆነ የፖለቲካ ልዩነት ይኖራል የሚል ግምት ስላልነበረው መቀራረብ ጀምሮ ነበር። ነገር ግን የሱዳን መንግሥት የኤርትራንና የትግራይን ተቃዋሚዎች ይደግፍ ስለነበር በስደተኛው መካከል ልዩነት በመፍጠር ግለሰቦች እርዳታ የሚለግሱት በሃይማኖትና በፖለቲካ ሽፋን መሆኑ ቀስ በቀስ ግልጽ እየሆነ መጣ።

ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን በየቀኑ የሚጎርፈው የስደተኛው ቁጥር በመጨመሩ የሱዳን መንግሥትና የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ቅርጫፍ መስሪያ ቤት ስደተኛውን በሦስት ዓይነት ከፍለው ማየት ጀመሩ።

1. በፈቃደኝነት ወደ አገሩ መመለስ የሚፈልግ

2. ከሱዳን ተነስቶ ወደ ሦስተኛ አገር ሂዶ የሚኖር

3. እንደ አገሩ ዜጋ የሱዳን ዜግነት አግኝተው መኖር የሚችሉ መሆኑን ግልጽ አደረጉ። ይሁን እንጂ ወደ አገር መመለስ የሚለው በስደተኛው በኩል ተቀባይነት አላገኘም። የሱዳን ዜግነት አግኝቶ መኖር አገርን እንደመክዳት ያስቆጥራል በሚል የሱዳን የዜግነት ወረቀት ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበረም።

ከፍ ሲል ለመጥቀስ እንደሞከርኩት ሱዳን በስደተኛው ሥም ከሚላከው የእርዳታ ዓይነት ለራሷ ጥቅማጥቅም ለማግኘት ስትል በስደተኛው ላይ ለላ ያለ ቁጥጥር ታደርግ ነበር። ስደተኛው ከመጠለያ ጣቢያ በሚያገኘው እርዳታ ለተወሰነ ጊዜ መኖር ቢጀምርም አንዳንዶች የለት ገቢያቸውን ለማሳደግ ሲሉ የተለያየ ሥራ ይሰሩ ነበር። ለምሳሌ ያህል እርሻ፤ ትናንሽ ሸቀጣሸቀጦችን መሸጥ፤ መለወጥና ከሱዳኖች ምግብ ቤት ተቀጥረው እየሰሩ አንዳንዶች የገቢ ምንጫቸውን አሳደጉ። በተለይ በአምራኩባ የሚኖሩ ስደተኞች ቀስ በቀስ ትራክተር እየገዙ እስከማረስ የደረሱ እንደነበሩ ይታወቃል። እንዲሁ እድል ያጋጠማቸው አንዳንዶች ከሱዳን ሕዝብ ጋር ለመተሳሰር ሲሉ ተጋብተዋል።

እንደሚታወቀው ደርግ የሶሻሊዝምን ፍልስፍና ይከተል ስለነበር የአሜሪካን መንግሥትም ሆነ ምዕራብ አገሮች ደርግን ለመጣል ወደፊት ይጠቅሙናል የሚሏቸውን ለኤርትራና ለትግራይ ተቃዋሚዎች በኢትዮጵያ ሥም የሚገባውን እርዳት በቀጥታና በጃሩ እየሰጡ አጠናከሯቸው። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግሥት ደርግ ማለት ነው ከሶቭየት፤ ከምስራቅ ጀርመንና ከኩባ የማቴሪያ እርዳታ ያገኝ ስለነበር ተቃዋሚዎችን ለማጥፋት ከፍተኛ የሆነ የታጠቀ ጦር ወደ ሰሜን አዛወረ። ምንም እንኳን በአገሪቱ ውስጥ ረሃብና አለመረጋጋት ቢኖርም ደርግ አገሪቱን ለመምራት መቻሉን ለዓለም መንግሥታትም ይሁን ለተቃዋሚዎች አረጋግጧል።

የስደተኛው ኑሮ እንዲህ ባለበት ሁኔታ የሰሜን ሽምቅ ተዋጊዎች ከአረብ አገራት ጋር የጠበቀ ግንኙነት በመፍጠር ኤርትራ ተገንጥላ በአረብ እጅ እንድትወድቅ ከፍተኛ የማጠናከር ሥራ ሰርተዋል። አረብ አገር የሚኖሩ የኤርትራ ከፍተኛ ባለሃብት ሰዎች ሳይቀሩ ሻዕቢያንና ጀበሃን ለማጠናከር ከገንዘብ እስከ ዲፕሎማሲ የሚዘልቅ እርዳታ እያደረጉ ሽምቅ ተዋጊዎች ማንነታቸው እንዲታወቅ አስቻሏቸው።

በሱዳን መጠለያ ጣቢያ የሚኖሩ ኤርትራዊ ስደተኞች በከፊል የእስልምና አሃይማኖት ተከታይ በመሆናቸው የአረበኛ ቋንቋ ለመናገር ችግር አልነበራቸውም። በመሆኑም ከሌላው ክርስቲያናዊ ስደተኛ በተሻለ ሁኔታ ከሱዳን መንግሥትም ሆነ ከሕዝቡ ጋር ተግባብተው የመኖር እድል ገጥሟቸዋል። የሱዳን ፓስፖርት እየተሰጣቸው ከአረብ፤ አረብ አገር የመዘዋወር እድልም ነበራቸው። ባጠቃላይ ከየኤርትራ የመጡ እስልምና ተከታዮች በስደት በሚኖሩበት ጊዜ የሥራ እድል ስለሚያገኙ በግል ሥራ ላይ ተሰማርተው ብዙዎች ከባድ የጭነት መኪናዎችን እየገዙ ከብረው የኖሩበት ወቅት ተከስቷል።

ከዚህ በተጨማሪ ኤርትራዊ ስደተኞች በቋንቋ ከሱዳን ሕዝብ ጋር መግባባት ስለሚችሉ ከጐንደርም ሆነ ከሌላ ክፍለ ሀገር የመጡ ስደተኞችን ጉዳይ አስፈፃዊ ዋና ተጠሪ ነኝ በማለት አገልግሎት ይሰጡ ነበር። ለማስረጃ ያህል ፈላሾች በአካባቢው ጦርነትና ለረሃብ ተጋልጠዋል በሚል ፈላሾችን ከኢትዮጵያ ምድር ጠራርጐ ለማስወጣት የእስራኤል መንግሥት ከፍተኛ ትግል ማድረጉ ሃቅ ነው።

በወቅቱ አንዳንድ ኤርትራዊ ስደተኞች ከተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ቅርንጫፍ መስሪያ ቤት በአስተርጓሚነትና በሹፊርነት ተቀጥረው ስለነበር የፈላሾችን ጉዳይ እናስፈጽማለት እያሉ በመረጃነትና በድንኳን ተካይነት ያገለግሉ እንደነበር በወቅቱ የነበረው “ኦፕሬሽን ሞሰስ” የተባለው መጽሀፍ ይፋ አውጥቶት እንደነበር አይዘነጋም። ከጐንደርና ከሌላ ክፍለ ሀገራት የመጡ ስደተኞች ከትግራይና ከኤርትራ ስደተኞች ጋር አንድ ዓይነት እርዳታና ግልጋሎት እንደማይሰጥ በግልጽ ታይቶ አልፏል።

ነገር ግን የሱዳን መንግሥትም ሆነ የውጭ እርዳታ ሰጭ ድርጅቶች ለኤርትራዊ ስደተኞች የማዳላት ሥራ ቢሰሩም በፖለቲካ ጥገኝነት ይኖር የነበረው ስደተኛ በስደት ላይ የገጠመውን የኑሮ ውጣ ውረድ ለመቋቋም ያለፈ ትዝታውን እየተወ ሁሉም በተጠለለበት ጣቢያ በአንድነት እየኖረ ያለውን ተካፍሎ እየበላ፤ ተዋውሶ እየለበሰ በመተዛዘን ሕይወቱን አሳልፏል።

በተለያዩ የሱዳን መጠለያዎች የሚኖረው ስደተኛ አንድነቱን ለመጠበቅ በእቁብ፤ በእድር በኮሙኒቲ ማኅበር የተሰባሰበበት ጊዜም ነበር። በተገንጣዮች አማካኝነት ቀስ በቀስ የኤርትራና የትግራይ ስደተኞች ራሳቸውን ለማደራጀት ከፍተኛ የማደራጀት ሥራ ተርተዋል። ጠቅለል ባለ መልኩ ግን ስደተኛው በአንድነቱ እየተመካ ባለው የሙያ ችሎታና ጉልበት በፈቀደ ሁሉ ስርቶ ለማደር ያደረገው ጥረት ቀላል አልነበረም።

ስደተኛው በሱዳን የሚደርስበትን ግፍ እየተቋቋመ ወደ ሦስተኛው ዓለም የሚሄድበትን ሁኔታ የስደተኞች ጽህፈት ቤት እንዲያመቻችለት ከማመልከቻ እስከ ሠላማዊ ሰልፍ ድረሰ ተሟግቷል።

እንደሚታወቀው የሱዳን መንግሥትና ውሃ ሙላት አንድ እየሆኑ አንዳንዴ በስደተኞች ላይ የሚያደርገው እንግልት ቀላል አልነበረም። ፀረ ኢትዮጵያ አቋም ያላቸው ባለሥልጣናት ኢትዮጵያን ከመጥላታቸው አንፃር “አበሻና እባብ“ በአንድ ላይ ቢያጋጥምህ ቅድሚያ ሃበሻውን በለው ይሉ እንደነበር አስታውሳለሁ።

ነገር ግን አብዛኛው የሱዳን ሕዝብ ለስደተኛው የተለየ በጐ ፍቅር ነበረው። የሱዳን ሕዝብ ገርና የዋሃ ባይሆን ኑሮ የስደተኛው ኑሮ የከፋ ይሆን እንደነበር መገመት ይቻላል። በመሆኑም በስደተኛው ዘንድ የሱዳን ሕዝብ የተወደደ እንጂ የሚጠላ አልነበረም። ይህ ማለት ግን አጠቃላይ የሱዳን ሕዝብ ለስደተኛው የተመቸ ነበር ለማለት አያስደፍርም።

ኢትዮጵያዊ ስደተኛ በሱዳን ሲኖር ብዙ አጋጣሚዎችን አሳልፏል። የአገሩን ባሕል ጥሎ የተሰደደ ሰደተኛ የሱዳንን ባሕል ለመለማመድ አስቸጋሪ መሆኑ አልቀረም። ከሱዳኖች ጋር ለመግባባት የመጀመሪያው ችግር የአረበኛ ቋንቋ አለመቻል ነበር። እናም የሱዳን ሕዝብ የአለባበስ፤ ባህሉና እምነቱ ወዘተ የእስልምና እምነት ተከታይ በመሆኑ ከኢዮጵያዊያኑ ጋር ስለማይመሳሰል ለመግባባት የችግሩ መነሻ እንደነበር ይገመታል።

ኢትዮጵያዊያን ሥም ማውጣት ያውቃሉ እንደሚባለው አበበ፤ አለማየሁ ከበደ፤ አልማዝ፤ ብርቱካን ወዘተ የሚል መጠሪያ አለን። ሱዳኖች የእስልምና ሃይማኖት ተከታይ በመሆናቸው መሃመድ፤ አሊ፤ ጅብሪል፤ ምስጦፋ ወዘተ የሚል ሥም አላቸው። ሱዳኖች የአበሻን ሥም በቀላሉ ለመጥራት እየተቸገሩ ይሁን በንቀት ለምን አሊ አንልህም የሚሉም ሰዎች ነበሩ። በመሆኑም በእምነትና በባህል ልዩነት ምክንያት በስደተኛ ላይ ስድብ፤ አፈናና ድብደባ በየጊዜው ተከስቷል። ለዚህ ማስረጃ በሱዳን ገዳሪፍ ተዋባ ከሚባል መጠለያ ሁሌ አምባጓሮ ስለሚፈጠር በስደተኛውና በሱዳኖች መካከል በሚደረግ ግጭት ብዙ የሰው ሕይወት አልፏል።

በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች የተጠጉ ኢትዮጵያዊያን ከፍተኛ የሆነ ታሪክ ሰርተው ያለፉበት አጋጣሚ ብዙ ነው። ቀደም ብየ ለማሳየት እንደሞከርኩት ስደተኛው በሱዳን በሚኖርበት ጊዜ ኩሩ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ለማስመስከር ብዙ የኑር ውጣ ውረዶችን እየተጋፈጠ ከሱዳን ሕዝብ ጋር ተደባልቆ አብሮ በሰላም ከመኖር ደረጃ ላይ ደርሶ ነበር። በሱዳን የስደተኛው ታሪክ ዘርፈ ብዙ ነው። ኢትዮጵያዊ ስደተኛ በመጠለያ ጣቢው ይሁን በሌላ አጋጣሚ በሚያጋጥመው መድረክ ሁሉ ኢትዮጵያን በጥሩ ሥም ለማስጠራት ያለፈበት ጊዜ የለም ማለት ይቻላል። ስደተኛው የሱዳን ሕዝብ ከሚከተለው ባህል ጋር በመመሳሰል ከእስላሙ ከክርስቲያኑ ጋር አብሮ እየበላና እየጠጣ ኑሮውን በፍቅር አሳልፏል።

ኢትዮጵያና ሱዳን ጐረቤት አገር እንደመሆናቸው መጠን የሁለቱን ጐረቤት አገር ሕዝብ ባሕልና ቋንቋ በማሳወቅ፤ በማለማመድ በጐና አስደናቂ መሆኑን አሳይቶ አልፏል። አንዳንድ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ከሱዳን ጋር እየተጋቡ ልጆች ወልደው ለማሳደግና ለማስተማር የቻሉ አሉ። ስደተኛው በእምነቱ ጸንቶ ለመኖር የራሱን ቤተክርስቲያን መስርቶ ነበር። ለዚህ አምራኩባ ገብርኤል የሚባለውን ቤተክርስቲያን በዋናነት ዋቢ ማድረግ ይቻላል።

ስደተኛው ከተጠለለበት ጣቢያ ሆኖ ትምህርት ቤት በመክፈት የራሱን ቋንቋ ለማዳበር ችሏል። አንዳንድ ልጆች ለከፍተኛ ትምህርት የደረሱ ነበሩ። በወቅቱ የደርግን ሥርዓት ለመጣል ይደረግ በነበረው ጦርነት ሳይቀር መጠለያ ጣቢያቸውን እየተው አንዳንዶች ከሽምቅ ተዋጊዎች ጋር በመሰለፍ የሞት የሽረት ትግል አድርገዋል።

ከላይ ከተጠቀሰው በተፃረረ መልኩ ከ1991 ዓም ጀምሮ ለጋሽ ድርጅቶችና የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ጽህፈት ቤት ለስደተኛው ያደርጉለት የነበረውን ድጋፍ በመቀነስ አንዳንድ ጽህፈት ቤቶችን በመዝጋት ስደተኛው ወደ አገሩ እንዲመለስ ማግባባት ጀመሩ። የሱዳን መንግሥትም እንዲሁ ስደተኛውን ከአገሩ ለማስወጣት አንዳንድ የማስፈራሪያ ዘዴዎችን መጠቀም ጀመረ። ሻዕቢያና ሕወሀት የራሳቸውን ደጋፊ በስደተኛው መካከል አሰርገው በማስገባት የስደተኛው ማኅበራዊ ኑሮ የክፍፍል ኑሮ ሆነ። በጥገኝነት መኖር የአእምሮ ሰላም እየነሳ ጥርጣሬ፤ ፍራቻ የእርስ በርስ ጥላቻ ተከሰተ።

በሱዳን ኢትዮጵያዊ ስደተኞች የገጠማቸውን የኑሮ ውጣ ውረድ፤ የአእምሮና የመንፈስ ጭንቀት ከፍ ሲል በመጠኑ ለመዳሰ ሞክሬአለሁ። የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮምሽን ጽህፈት ቤት ወኪል ዋና ተግባሩ ከለጋሽ አገሮች የሚላከውን እርዳታ ለስደተኛው ማዳረስና ወደፊት ስደተኛውን የሚቀበል አገር ማፈላለግ አብይ ተግባሩ ነው።

በድርቅና በፖለቲካ ምክንያት አገሩን እየጣለ ወደ ሱዳን የፈለሰው ኢትዮጵያዊ ቁጥሩ ቀላል አልነበረም። በወቅቱ ብዙዎችን ያሳሰበው ወደ ሦስተኛው ዓለም ለመሄድ የጠያቂው ቁጥር ብዙ ስለነበር የትኛው አገር በቋሚነት ይቀበላል የሚለው ጥያቄ ቀላል አልነበረም። ይሁን እንጂ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኛች ኮሚሽን ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የጥገኝነት መስፈርት አሟልተዋል የሚላቸውን ግለሰቦች ወደ ሌላ አገር መላክ ጀመረ። በሌላ መልኩ ስደተኛው ወደ አገሩ መመለስ እንዳለበት መመሪያ አስተላለፈ። ይሁን እንጅ ስደተኛው ተሰብስቦ ለዋናው ጽህፈት ቤት አቤት የሚሉ ሰዎችን መረጠ። ወኪሎች ስደተኛው ወደ አገር ሊመለስ የማይችልበትን ምክንያት ዘርዝረው ጀኔቭ ለሚገኘው ለተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ጽህፈት ቤት፤ ለሰባዊ መብት አስጠባቂ ኮሚሽን፤ በውጭ ለሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የድረሱልን ደብዳቤ አስገቡ። ከዚህ ቀን ጀምሮ በደተኛውና በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኮሚሽን ጽህፈት መካከል ለሁለት ዓመት የዘለቀ ሙግት ተካሂዷል።

ስደተኛው የጀመረው ሙግት እንዲህ ቀላል አልነበረም። ቢሆንም ስደተኛው በሞራልና በጽናት በአንድነት በመቆም የእለት ጉርሱን እየቀነሰ የመረጣቸውን ወኪሎች እያበረታታ እልህ አስጨራሽ ትግል አድርጐ አልፏል። በዚህ ትግል ውስጥ የሱዳን ጠበቆችና ሕዝቡ ስደተኛውን ለመርዳት ተባብረዋል።

በመጨረሻም በሱዳን የሚገኙ ስደተኞች ወደ አገራቸው የማይመለሱበትን ምክንያት የሚያጣራ ቡድን በ2000 ተላከ። ከጀኔቭ የተላኩ፤ አንደኛ ዳንኤል ሆላንዳዊ ሁለተኛ ደቡብ አፍሪካዊት ቪክቶሪያ 3. ሙሳ እንደሚባሉ አስታውሳለሁ። እያንዳንዱ ስደተኛ ወደ አገር የማይመለስበትን ምክንያት ከአጣሪቡድኖች ፊት ለፊት እየቀረበ በማስረዳ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በርካታ ኢትዮጵያዊ ወደ ሦስተኛ አገር ሄዱ። ከዚህ ውስጥ አውስትራሊያ አገር የመምጣት እድል ያጋጠማቸው በርካቶች ናቸው። አንዱም እኔ ነኝ።

ለማጠቃለል ያህል፦ በሱዳን ኢትዮጵያዊ ስደተኞች ችግሩን መጋፈጥ ብቻ ሳይሆን አንድነታቸውንና የአገራቸውን ባሕል በመጠበቅ በደስታና በመከራ ያሳለፉ ኩሩ ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን አስመስክረዋል። በሱዳን የስደተኝነት ኑሮ እንዲህ በዚህች አጭር ጽሁፍ ማጠቃለል እንዳማይቻል ግልጽ ነው። ይሁን እንጂ በሕይወት የሚገኙ ሁሉ የዛሬውን ቀን ሲያከብሩ የጽናታቸውና የአድነታቸው ውጤት በመሆኑ ሊኮሩበትና ወደፊትም የአገራቸውን የቆየ የአብሮነትና የአልበገር ባይነት ባሕሪን በመላበስ በስደት የሚገኙ ልጆቻቸውን ማበረታታ ግድ እንደሚል አያጠያይቅም።

ስደት አብቅቶ ሁሉም ወደ አገሩ እንዲመለስ ቸርነቱ የማያልቅበት እግዜአብሄር ይጨመርበት

እግዚአብሄር አገራችን ይጠብቃት።
source ,,ECADF

Advertisements

Posted on June 25, 2013, in ETHIOPIA AMHARIC. Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: