posted by Issa Abdusemed  እንደሚታወቀው በአንድ ሃገር የኤኮኖሚ፣ የፖለቲካና የማህበራዊ ክንውኖች የቀን ተቀን ለውጥ ውስጥ የህብረተሰብ ተሳትፎ(አስተዋጾ) ጉልህ ሚና አለው፡፡ እንዲሁም በሂደትቱ ውስጥ የሚያጋጥሙ አገራዊ ጠቀሜታ ያላቸው ጉዳዮችም ይሁኑ ወይም በተቃራኒው የሚከሰት ተፈጥሯዊም ሆነ በመልካም አስተዳድር ችግር ምክንያት የሚፈጠሩ ችግሮች ከህብረተሰብ ጫንቃ ላይ አይወርድም… ይህ ስለሚታወቅ ሃላፊነት የሚሰማቸው፣ ለሃገርና ለሕዝብ ታማኝ የሆኑ፣ በሕዝብ ይሁንታ ስልጣን የያዙ መንግስታት ያላቸው ሃገሮች በየትኛውም ሃገራዊ እንቅስቃሴ ላይ ሕዝባቸውን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ በማድረግ በብሔራዊ ስሜት የታነፀ በሃገሩ ጉዳይ የማያመነታ ህብረተሰብ ይገነባሉ፡፡ የእንደኛ አይነቶቹ የሃገርና የሕዝብ ፍቅር የሌላቸው አምባገነን መሪዎች ግን እንኳን የሃገርህ ጉዳይ ያገባሀል ብለው ሊያሳትፉት ቀርቶ የሕዝብን የመናገርና ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ ተፈጥሮዊ መብቱን ገፈው ሃገሪቱን የቁም እስር ቤት አርገዋታል፡፡Image

ነፃነት፣አንድነት፣ፍትህ እና እኩልነት በወሬና በዲስኩር አይመጣም:: የመስዋዕቱ አይነት ይለያይ እንጂ አነሰም በዛም የነፃነት ትግል ወይ ሃብትን ወይም የህይወት መስዋዕትነት ይፈልጋል፡፡ ዶክተር ማርቲን ሉተር ኪንግ ጁንየር እንዳለው “ለውጥ በመንኮራኩር ተጭኖ የሚቀርብ ነገር አይደለም ፣ በማያቋርጥ ትግል እንጂ ፣ ወገባችንን ጠበቅ አድርገን ለነፃነታችን መጣር አለብን ”፥ ይህ ነው እውነቱ:: ይህንን ሁሉ በህዝብና በሃገር ላይ የሚደርሰውን ለከት ያጣ ጭቆና የምናይ እና የምንሰማ በተለይ በሰለጠነው አለም የምንኖር ወገኖች እኛ በሰው ሃገር የምናገኘውን የመናገር ፣የመሰብሰብ እና የመፃፍ ነፃነት ወገናችን በገዛ ሃገሩ ሲያጣ፣ ይህ ነው የማይባል ችግር ሲወርድበት ከወሬ ያለፈ በተግባር መልካም ውጤት የሚያመጣ ስራ ለመስራት ቆርጠን ልንነሳ ይገባል:: የህይወት መሰዋዕትነት ለሚከፈልበት የነፃነት ትግል ቢያንስ በገንዘብ በማገዝ አጋርነታችንን ማሳየት አለብን:: የወያኔን ተንኮል ችላ ካልን የወገኖቻችንን የመከራ ጊዜ እናራዝማለን ማለት ነው:: ቁጥር ስፍር የሌለው ህዝብ በውጪው አለም እየኖረ ስለምን የህዝባችን የመረጃ ምንጭ የሆኑትን ነፃ ሚድያዎች መስራት ያለባቸውን ያህል እንዲሰሩና ህዝባችን እየተራበ መጥገቡን፣ እየከሰረ ማትረፉን፣ እየተቸገረ መበልፀጉን ከሚነገረው የወያኔ ዲስኩር አውጥተን አማራጭና እውነተኛ መረጃ የሚያገኝበትን፣ ወያኔ የስልጣን ዘመኑን ለማራዘም በከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲው እያደረገ ያለውን ዘርን ከዘር ሃይማኖት ከሃይማኖት የማጋጨትና የመሳሰሉትን የወያኔን ሴራ ህዝቡ እንዲያውቅና በአንድነት ለመብቱና ለነፃነቱ እንዲነሳ በማድረግ የዜግነት ግዴታችንን መወጣት አለብን፡፡

የወያኔ ጁንታ 11% እድገት አሳይተናል እያለ በሌለ ተስፋ ላይ ተቀምጦ በሚኮፈስበት እና ሳተላይት አመጠቅን፣ አይሮፕላን ሰራን፥ እያለ ትምክህቱን በሚያሳይበት በአሁን ወቅን በሃገራችን መኖር ያልቻልን ኢትዮጵያውያን ድንበር አቋርጠን በተፈጥሮ የበለጸገች ሀገራችንን ጥለን ወደ ተለያዩ ሀገራት በስደት ተበትነን እንገኛለን:: የዘረኛው ስርዓት በነፃ አውጪ ስም ስልጣን ከያዘበት ጊዜ ጀምሮ እንዲሁም ከዛም በፊት የሚከተለው የተሳሳተ ሃገር የመገነጣጠሉንና ብሔራዊ ጥቅምን አሳልፎ የመስጠቱን እኩይ ተግባር መመልከት የተለመደና የቀን ከሌት ክንውናቸው መሆኑ በሃይል ስልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ የሚታይ እውነታ ነው፡፡

ከምስረታው ጀምሮ ይዞት የተነሳው የኢትዮጵያን ሉዋላዊነት የማፍረስና የመበተን አላማውን መተግበር የጀመረው በወቅቱ የነበረውን ሰራዊት በመውጋት ሃገራችን ያለ ባህር በር እንድትቀርና በኢትዮጵያዊነት የታነፀውን ዘመናዊ የወታደር ሀይል በትኖ በምትኩ የአንድ ብሄር የበላይነት የሚታይበት፣ ብሔራዊ ስሜት የሌለው፣ በህዝብ ላይ አንግሰው ያሻቸውን ሲገሉ፣ ያሻቸውን ሲያስሩ እነሆ አሁን ያለንበት ደርሰናል፡፡ በመሰረቱ ይህ እኩይ ስርዓት በኢትዮጵያዊነት ላይ ካለው የመረረ ጥላቻ የተነሳ አብረው የመሰረቱትንና በኢትዮጵያዊነት ላይ ፅኑ አቋም የነበራቸውን ባልንጀሮቻቸውን ሳይቀር እያስወገዱና እያባረሩ በምግባር የሚመቻቸውን በተለይ በህዝብና በሃገር ላይ የጠለቀ ጥላቻ ያላቸውን አስከትለው የጥፋት ዘመናቸውን ቀጥለውበታል፡፡ በተለይ የመንግስትነትን ስልጣን ከያዙ በኋላ ከስልጣን በተጨማሪ በገቢ እራሳቸውን ለማጠናከር ከኢትዮጵያ ህዝብ በዘረፉት ሃብትና ንብረት በትግራይ ህዝብ ስም ባቋቋሙት ‘ኢፈርት’ ሃገሪቱን ጫፍ እስከ ጫፍ በመቆጣጠር የንግዱን መስክ በበላይነት በመያዝ ገቢና ወጪው የማይታወቅ ትልቅ የሃብት ምንጭ በመፍጠር የአገሪቱን የትኛውንም የንግድ እንቅስቃሴ በበላይነት ይዘው ነግሰውበታል፡፡ በተለያየ መስክ ከሚፈፀመው የሰብዓዊ መብት ረገጣ በተጨማሪ የሀገርን ብሔራዊ ጥቅም አሳልፈው በመስጠት ወይም ገንዘብ የሚያስገኝላቸውን ሁሉ በመዝረፍና በማሸሽ፣ ምስኪኑ ህዝብ በዜግነቱ ሊያገኝ የሚገባውን ብቻ ሳይሆን በስሙ ተለምኖ የመጣውን ሁሉ በመንጠቅ ብዙሃን በርሃብ በሚሰቃይበት ሃገር ለአራት ለአምስት ትውልድ የሚበቃ ሀብት አሽሽተዋል፡፡

ከምርጫ 1997 ዓ.ም በፊት በተወሰነ መጠን እራሳቸው ላወጡት ህገ-መንግስት ተፈጥሯዊ ባህሪያቸው ቢያስቸግራቸውም ህጋዊ መስሎ ለመታየት የሚሞክሩበት ሁኔታዎች ይስተዋሉ ነበር፡፡ በዝያን ወቅት ጋዜጠኞች ምንም እንኳን ፍርድ ቤት መመላለስ የእለት ከእለት ስራቸው ቢሆንም ከአሁን በተሻለ የህትመት ውጤቶች በቁጥርም በይዘትም የተሻሉ ነበሩ፡፡ በሌላም በኩል ይህው እኩይ ስርዓት ህግን ከመሻሩ በፊት የፓርላማ ጀሌዎቹን ሰብስቦ ሊሽር ባስበው ህግ ላይ ሌላ ህግ ሲያወጣ ታይቷል፡፡ ከዚህ በፊት ህውሃት በአመለካከትም ይሁን በግል ጥላቻ የራሱን ሰዎች ሲበላ ከቻለ አንዱን በአንዱ ላይ አስነስቶ በማጫረስ አልያም በአደባባይ በደላቸውን እንዲናዘዙ በማስገደድ ከተጠያቂነት እራሱን ሲከላከል መቆየቱ አንድም እራሱን ላለማጋለጥ አልያም በሃገርና በህዝብ ላይ ለሚፈፅማቸው በደሎች ሰርዞም ደልዞም ህግዊ ለመምሰል ይጥራል፡፡

ከምርጫ 1997 በኋላ ያለው በፊት ከነበረው ጋር ማነፃፀር ይከብዳል፡፡ እጅግ ብዙ እርቀት ወደ ኋላ የመመለስ ያህል ነው ፥ምክንያቱም በዛን ወቅት በተፈጠረው በጣም ጠባብ አጋጣሚ ህዝቡ ለስርዓቱ ያለውን ጥላቻና ለውጥ ፈላጊነቱን እንዲሁም ወያኔዎች በተግባር የማያውቁትን ዴሞክራሲ ህዝቡ ሲዘምርላቸው፣ ፍፁም ሰላማዊ በሆነ መንገድ ከነሱ እንደሚሻል ሲያሳያቸው፣ በተቃራኒው ደግሞ ይበጁኛል የሃገሬን እና የእኔን ህልውና ይጠብቁልኛል፣ ብሩህ የነፃነት ጊዜ ያመጡልኛል ብሎ የሚላቸውን እንደራሴዎቹን ሲመርጥ ለአፍታ በዓይነ ህሊናችን እናስታውስ፡፡
ከዚህ በኋላ ያለችው ኢትዮጵያ የግል የህትመት ውጤቶች ሙሉ በሙሉ በማፈን በሀገራችው፥ በሞያቸው ይህ ነው የሚባል ለውጥ ማምጣት የሚችሉ ጋዜጠኞችን በማሰርና በማሳደድ፣ ለሃገራችን ክብርና ለህዝቧ ነፃነት የሚሟገቱ የሚታሰሩባት፣ የሚገደሉባት ወይም በሃገራቸው በነፃነት የመኖር መብት አጥተው የሚሰደዱባት አልያም የነሱ የሆነውን በሌሎች ተቀምተው የመከራ ቀንበር ከብዶ በግዞት የሚኖርባት ስትሆን ለኢምንት ባለ ጊዜዎች ግን የምድር ገነት ሆና ያሻቸውን የሚሆኑባት የግል ርስት አድርገዋታል፡፡
ለዚህ ሁሉ በሃገርና በህዝብ ላይ ለሚደርሰው እንግልትና መዋከብ ምንም እንኳን የመንግስትን እርካብ የተቆናጠጡት ’ገዢዎቻችን’ ከተፈጥሮ ባህሪያቸው አንፃር የፈለጉትንና ያሻቸውን ቢያደርጉም በየግዜው በህዝብ ላይ የሚያደረሱትን ሰቆቃ የየሰሞኑ መነጋገሪያ ከማደረግ በዘለለ ህዝብ እንደ ህዝብ በደል በቃኝ፣ ግፍ በቃኝ፣ መሰደድ በቃኝ፣ መታሰርና መገረፍ በቃኝ፣ ከሃብትና ከቀዬ መፈናቀል በቃኝ ብሎ ለለውጥ እንዲነሳ በህብረት ከመስራት ይልቅ የነሱን መበታተንና መሰነጣጠቅ አውርተን በድክመታቸው ሳንጠቀም መልሰው ተደራጅተው መብትና ክብራችንን ሲገፉንና ሲፃረሩን እናያለን፡፡ ሃገርና ህዝብን ከዚህ እኩይ ስርዓት መታደግን ለተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ብቻ ትተን በሰሞነኛ የወያኔ የጭካኔ ገድል ላይ ሻይ እየጠጣን ስናነሳና ስንጥል ከወሬ የዘለለ ተግባራዊ የትግል እንቅስቃሴ ውስጥ ሳንገባና የታደሉት ለሃገራቸውና ለህዝባቸው የሚከፍሉትን መስዋዕትነት የሚሰሩትን ታላቅ ስራ ስናፈርስና ስንክብ የዜግነት ግዴታችንን በአግባቡ ሳንወጣ ’ለገዢዎቻችን’ መሳሪያ ሆነን እንዳንቀር መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ በነፃነት በመኖር የምንቀድማቸው ሃገራት ሰልጥነው በዴሞክራሲያዊ ስርዓትና መልካም አሰተዳደር የህዝቦቻቸውን ሰብዓዊ መብት ለማስጠበቅ ደፋ ቀና በሚሉበት በዚህ ዘመን የኋሊት የሚጓዘው ከዘመኑ ጋር መዘመን ያቃተው ወያኔ ከብዙ ዘመናት በፊት በነበረው አስተሳሰብና የሃይል አገዛዝ ተሸብቦ ያላስነባው ህዝብ፣ ያልጣሰው ህግና ስርዓት፣ ያላፈረሰው አንድነት፣ያላዋረደው የህዝብ ስብእና፣ ያልገባበት የእምነት ተቋም፣ ያልበተነው የሞያ ማህበራት፥ ያልገደለው፣ ያላሰረውና ያላስለቀሰው የህብረተሰብ ክፍል የለም፡፡

*–ከላይ ወያኔ ከደደቢት እስከ ቤተ-መንግስት ጸረ-ኢህአዴግ ተብሎ የፈረጀውን አመለካከት ለመምታት የተጠቀመባቸው ስትራቴጅዎች በሙሉ ሁሉንም ተግባራዊ እያደረጋቸው ይገኛል፡፡ በሃገራችን ታሪክ ታይቶ እና ተከስቶ የማያውቅ የሽፍቶች አሸባሪ መንግስት በተለያየ ስልት ኢትዮጵያውያንን መከራቸውን እያሳየ ይገኛል:: ይህ ወንበዴ መንግስት ማፊያዊ ስልቶችን በመጠቀም የተለያዩ ሽብሮችን እየፈጸመ ነው:: መውደቂያው የደረሰው እና በቋፍ ላይ ያለው ይህ መንግስት ስለ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የሚያስቡ ሰዎችን የሚዋጋበት ስልቱ የህዝብ ንብረት እና ገንዘብ በመጠቀም ስልጣኑን ላለማጣት እየተራወጠ ይገኛል:: ይህንንም ለመዋጋት ድፍን ኢትዮጵያዊ ዘር ሃይማኖት ቀለም ወ.ዘ.ተ. ሳይለይ በአሁን ሰአት በጋራ ’ድምጻችን ይሰማ’ እያለ ለመብቱ እና ለነጻነቱ እየታገለ ነው:: በአሁኑ ወቅት አዛዥና ታዛዥ በውል በማይታወቅበት የወያኔ ስርዓት ዘመኑ እያከተመ መሆኑን ከሚሰራቸው ስራዎች መገንዘብ አይከብድም፡፡ ህግ ማሰከበር ያለበት አንድ መንግስት ላወጣው ህግ መገዛት የማይችልበት ደረጃ ከደረሰ ህልውናው አደጋ ውስጥ ለመሆኑ ማሳያ ነው፡፡ ለዚህ መብቱን በወያኔ የተነጠቀው ህዝብ የህገ-መንግስቱን አንቀፅ እያሳየ ’የህግ ያለህ’ ሲል መደመጡ፡ በግምት የሚመራን ስርዓት የመጨረሻው ጠርዝ ላይ መቆሙን አመላካች ነው፡፡ –*

ኢትዮጵያ፥ ሀሳብን በነፃነት ያለፍርሀት መግለፅ የማይቻልባት፤ የዜጎች የኑሮ ደረጃ ከዕለት ዕለት እየተባባስ የሚሄድባት፤ ዘማናዊ የመረጃ ግንኙነቶች (information technology) ሆን ተብለው የታገዱበት፤ የህዝቦቿን መከባበርና አንድነት በዘር ጥላቻና በሀይማኖት ለመከፋፈል አገዛዙ የሚጥርበት፤ ዜጎች አላግባብ የሚታሰሩባት፣ የሚገደሉባት፤ ዜጎች በከፍተኛ ሁኔታ የሚሰደዱባት፤ ነፃ፣ ፍትሐዊና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ የማይካሄድባት፤ ዜጎች ከመኖሪያቸውና ቀዬአቸው የሚፈናቀሉባት፤ ለሕግ ተገዢ ያልሆነ መንግሥት ያለባት፤ ዜጎች የገዢው ፓርቲ አባል ካልሆኑ በነፃነት ሠርተው መኖር የማይችሉባት፤ በተግባር ያልዋለ ህገ-መንግሥት ያላት፤ ነፃ ሚዲያ የሌለባት፤ ዜጎች ለሀብት ንብረታቸው ዋስትና የማያገኙባት፤ ህዝባዊ መንግሥት የሚናፍቅ ህዝብ ያለባት፤ በሀገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ተቋማት የገዢው ፓርቲ ፖለቲካ መጠቀሚያ የሆኑባት፤ ዜጎች በአስተሳሰብ እና በዕውቀት እየቀጨጩ፣ ቤቶች በቁመታቸው ማደጋቸው እንደዕድገት የሚቆጠርባት ሀገር ሆናለች።

እለት እለት እየተጠናከረ በመጣው አፈና ምክንያት ፌስቡክን እና ሌሎች ሶሽያል ሚድያዎች እንደመተንፈሻ እና መንግስትን ለመታገል እንደዋነኛ መደራጃ እያገለገለ እንደሚገኝ ግልፅ ነው። ታዲያ ሁሉንም ነገር ካላፈኑ እንቅልፍ የማይወስዳቸው ወያኔዎች የፌስቡክ ነገር ከቁጥጥራቸው እንደወጣ ስለተገነዘቡ ፌስቡክ የሚፈጠሩ ግሩፖችን፥ገፆችንና የግለሰብ ፕሮፋየሎችን እየተከታተሉ ከመዝጋት ባሻገር ፀረ-ፌስቡክ የሆነ ዘመቻ ከጀመሩ ውለው አድረዋል። እስከአሁን ፀረ-ፌስቡክ የሆኑ የፕሮፓጋንዳ ስራዎች በኢቲቪ፥ እና በተለያዩ ሚድያዎች ሲደሰኩሩ ሰንብተዋል።

በአሁኑ ወቅት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የሚጠይቀዉ አንድ ጥያቄ ነዉ። ይህም የአንድነትና ተባብሮ የመስራት ጥያቄ ነዉ። ይህንንም ጥያቄ ህብረተሰቡ በተገኘዉ መድረክ ላይ ሁሉ ሳያሰልስ እያነሳዉ ይገኛል። ከዚህ አኳያ ለዚህ ህዝባዊ ጥያቄ ሁሉም በጉዳዩ ያገባኛል የሚሉ ወገኖች ሁሉ ጊዜ ሳይሰጡ በመገናኘትና በዚህ ታላቅ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ እጅግ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥተዉ ሊወያዩበትና ሊመክሩበት አልፎም መፍትሄ ማስቀመጥና ይህንኑም ለማስፈጸም በጋራ መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።

ዘረኛው የወያኔ አስተዳደር በአገራችን ኢትዮጵያና ህዝቦችዋ ላይ የሚያደርሰውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ ነፃነት ገፈፋና መብት ረገጣን ለማጋለጥ፣ ለማስቆምና ሥርዓቱን አስወግዶ ሁሉን አቀፍ በሆነ መንግስት ለመተካት በትጥቅ እና በሰላማዊ ትግል እንደ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሽግግር ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር እና ሌሎችም የሚያካሂዱት ትግል እንደቀጠለ ነው። በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ህዝብ አርበኞች ግንባር በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በየግዜው በሚሰነዝረው ጥቃት የወያኔ መንግስት እንዳሳሰበው በየግዜው ከሚያስማው ሮሮ መረዳት ይቻላል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ብሔራዊ የሽግግር ምክር ቤት ይህንን ብልሹ ሥርዓት ለማስወገድና ህዝብ በመረጠው መንግስት ለመተካት በሚደረገው ትግል የበኩሉን አስተዋፆ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። በዚህም መሰረት በተለያዩ አጋጣሚዎች የተነሱ ተደጋጋሚና ወሳኝ ጥያቄዎች ላይ ማብራሪያና ማሻሻያዎችን አድርጓል። የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ምክር ቤት የወያኔን ጸረ-ኢትዮጵያ አገዛዝና የዘረኝነት ስርዓት አስወግዶ የኢትዮጵያ ህዝብ በነጻና ፍትሃዊ ምርጫ በመረጠው ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመተካት የሚታገል ህዝባዊ የፖለቲካ ተቋም እንጂ የሽግግር መንግስት አይደለም ። የሽግግር መንግሥት ስንል ደግሞ የወያኔ አገዛዝ ከተወገደ በኋላ የሚተካ ሁሉን አቀፍ የሆነ፥ በዲሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠ መንግስት እስኪቋቋም የሚያገለግል ጊዜያዊ አስተዳደር ነው።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ የሽግግር ም/ቤትም ከተነሳለት ህብረተሰቡን የማስተባበር አላማ በመነሳት ከተባባሪ አካላት ጋር በመሆን፤ ለህብረተሰቡ ጥያቄ ቀጥተኛ እና ቆራጥ ምላሽ ለማሰጠት፤ ያለዉን ስርአት በማስወገድ ሂደትና ስርአቱም ከተወገደ በኋላ ስለሚተካበት ሁኔታ፤ ሁሉም ባለድርሻ አካሎች አማራጮቻቸውን የሚያቀርቡበት “ትግሉም የጋራ ድሉም የጋራ” በሚል መርህ ዙርያ ታላቅ ሁሉን አቀፍ የምክክር ጉባኤ በሚቀጥለው ወር ጁላይ 2013 (እኤአ) በዋሽንግተን ዲሲ ላይ እየተሰናዳ ይገኛል። የኢትዮጵያን አንድነትና ሉዓላዊነት፥ የዜጎችን ሰብዓዊ መብት ለማስከበር ሁሉን አቀፍ ህዝባዊ የሽግግር መንግሥት እንዲቋቋም ቅድመ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ትልቅ ስራ ይጠብቀናል።

ይህ ከላይ ያነሳሁትና ተነግሮ የማያልቀው በህዝብ በሃገር ላይ የሚደርሰው በደልና ግፍ በወያኔ ተንኮል ብቻ ሳይሆን የኛም ግፍና በደልን የመሸከም አቅም ወይም እንደ ሰው መብታችንን የማስጠበቅ፣ ህልውናችንን ያለማስደፈር ወይም በውርደት መኖር በቃኝ ብለን ሃላፊነታችንን ሳንወጣ እንዲሁ ከድርጅት ድርጅት ስንላተም፣ ከፓርቲ ፓርቲ ስንከለስ በተዘዋዋሪ የወያኔ መሳሪያ ሆነን በህዝባችንና በሃገራችን ላይ የሚደርሰውን በደልና እንግልት ትኩረት ሰጥተን መንቀሳቀስ አለብን፡፡

ስለሆነም ኢትዮጵያንና ህዝቧን ለመታደግ በየትኛውም የትግል መስክ ተሳትፎ በማድረግ ለነፃነት፣ለፍትህ እና ለእኩነት በሚደረገው ትግል ውስጥ የየራሳችንን አሻራ ለማሳረፍ ለተግባራዊ ትግል እንትጋ፡፡

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!

Advertisements

Posted on June 29, 2013, in ETHIOPIA AMHARIC and tagged . Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: