ይድረስ ለወጣት ጃዋር መሐመድ

ሸንቃጣዉ ዘካሊፎርኒያ  በመጀመሪያና በተቀዳሚ ደረጃ በአል ጃዚራ ቴሌቪዥን የተካሄደዉን ዉይይት አንተ፣ መሐመድ አደሞና ፊዶ ኤባ ሆናችሁ በመካፈል የኦነግንና የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ ነዉ ብላችሁ የምታምኑበትን ነገር ሁሉ በመግለጻችሁ እጅግ በጣም አመሰግናለሁ…. ከእናንተ ባሁኑ ወቅት ያልጠበኩትን ሀሳቦች በመግለጻችሁ፤ በተለይም ከአንተ ከወጣቱ የተማረ አንደበት ይወጣል ብዬ ያልጠበኩትን ስሰማ በጣም ስላዘንኩ ይህንን ትንሽ መጣጥፍ ለመጫር ተገድጃለሁ። አንተ በተናገርከዉ ሀሳብ ጸንተህ የመቆየት መብት አለህ፤ ሆኖም ግን ሀሳብህ ኦሮሞ ባልሆኑ ኢትዮጵያዉያን ዘንድ ምን ያህል ዋጋ ሊያገኝ እንደሚችል መገመት አያዳግትም። ሁለቱ የአል ጃዚራ ወጣት ሴት ጋዜጠኞች እናንተን ለጥያቄ ሲጋብዟችሁ ስለኢትዮጵያ እምብዛም አያዉቁም ብላችሁ አስባችሁ ቀርባችሁ ከሆነ ተሳስታችሗል እላለሁ። ሴቶቹ ጋዜጠኞች ዲፕሎማሲያዊ በሆነ መንገድ በብዛት ሲጠይቋችሁ አንዳንዴም ደግሞ ወጋ እያደረጉ ነበር የጠየቁት።

ጠቅለል ባለ መንገድ ለመግለጽ እንዲቻል ሁላችሁም የሞከራችሁት የኦሮሞ ህዝብ ከማንኛዉም የኢትዮጵያ ህዝብ የበለጠ በደል፣ ብዝበዛ፣ ጭቆና፣ እስራት፣ እንግልት፣ስደትና የመሳሰሉት ነገሮች ደርሰዉበታል በማለት ነዉ። አልፋችሁም ደግሞ የኦሮሞ ህዝብ በባርነት እስከመሸጥ ድረስ ግፍ ተፈጽሞበታል ብላችሗል። ለመሆኑ ጂማ አባ ጂፋር እና ከባርያ ንግድ ሀባታም የሆኑት የቅርብ ኦሮሞ ወዳጆቻቸዉ እዳጣን ብሔረሰቦችንና ኦሮሞዎችን ጨምሮ በባርነት በመነገድ አይደለም ወይ ጠመንጃና ገንዘብ በብዛት ያካበቱት? በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ ኦሮሞዎች በግዛት ማሰፋፋት ተሳትፈዉ አያዉቁም ልትሉ ነዉ እንዴ? ለመሆኑ ኦሮሞዎች ጎንደር ድረስ የዘለቁት ግዛትና ገባሪ ፍለጋ ነዉ ወይስ ኢንቨስትመንት ለማስፋፋትና ዘመናዊ ቴክኖሎጂ ለማስተዋወቅ ነዉ? እየተዋወቅን።Jawar Mohammed, an Oromo elite and anti Ethiopia extremist

ጃዋር በተለይ አንደኛ ኢትዮጵያዊ ሁለተኛ ደግሞ ኦሮሞ ነህ ወይስ አንደኛ ኦሮሞ ሁለተኛ ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነህ ተብለህ ስትጠየቅ “አንደኛ ኦሮሞ ነኝ ሁለተኛ ኢትዮጵያዊ ነኝ” ብለህ ስትመልስ ከንተ አልጠበቅሁም ነበር። እንዲያዉም ኢትዮጵያዊነት በግዳጅ እንደተሰጠህ አድርገህ አፈረጥከዉ። ልክ የፈረንሳይ ቅኝ ገዢዎች በቅኝ የሚገዙዋቸዉን የአፍሪካ አገሮች ህዝቦችን ፈረንሳዉያን አድርገዉ እንደፈረጇቸዉ ሁሉ የአብሲኒያ ቅኝ ገዢዎች የኦሮሚያን አገር በወረሩበት ወቅት ኦሮሞዎችን እንደ ኢትዮጵያዉያን አድርገዉ እንደፈረጇቸዉ አድርገህ ደመደምክ። ኦሮሞዎች ጎንደር ዘልቀዉ የግዛት አስተዳደራቸዉ ተሳክቶላቸዉ ቢሆን ኖሮ ዛሬ ምድረ ጎንደር ሁሉ ኦሮሞ እንደሚሆን አልጠራጠርም ነበር። ሆኖም ግን የግዛት ማስፋፋቱ አለመሳካትና የሀይል ሚዛኑ ደግሞ ወደ ደቡብ ስላሽቆለቆለ የተለያዩ እዳጣን መንግስታት በጠመንጃ ሀይል ተሸንፈዉ ለማእከላዊዉ መንግስት መገበራቸዉ ለዘመናዊ አገር የሚያስፈልጉት ማእከላዊ የመንግስት መዋቅሮች ሊዘረጉ ችለዋል። ኦሮሚያ እንደ አንድ ራስዋን ችላ የነበረች አገር ወይም ብሔር ተቆጥሮና አቢሲኒያ ደግሞ ከሰሜን መጥታ ልክ እንደ እንግሊዞቹና እንደ ፈረንሳዮቹ ኦሮሚያን በቅኝ የገዛች ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ቅኝ ገዢ አገር ብትባል አግባብ ያለዉ ነገር ይሆናል ብዬ አምናለሁ። ሆኖም ግን ቅኝ ገዢ ለመባል መስፈርቶቹ መሟላት ያለባቸዉም ይመስለኛል።

ስምና ቋንቋን በተመለከተ የተናገራችሁት በጣም ተጋንኗል። የኦሮሞ ስም ያለዉ ኦሮምኛ ስለተናገረ እንደ ጠላት ይፈረጃል የሚለዉ በፍጹም ሊገባኝ አይችልም። የታወቁት የኢትዮጵያ ጀግኖች እንደ ባልቻ አባ ነፍሶ፣ ኮሎኔል አብዲሳ አጋ፣ ብ/ር ጄነራል ሙሉጌታ ቡሊ እንዲሁም የገንዘብ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ይልማ ደሬሳ ደረታቸዉን ነፍተዉ አማርኛና ኦሮምኛ የሚናገሩ አልነበረምን? ይህ ማለት ደግሞ ኦሮምኛ መናገር የሚያፍሩ አልነበሩም ማለት አይደለም። በወላይታም፣ በገዲኦም፣ በሲዳማም፣ በኮንሶም፣ በከንባታ፣ በሃዲያም እንዲሁም በብዙ እዳጣን ብሔረሰቦች መካከል የራስን ቋንቋ መናገር የሚታፈርበት ዘመንም ነበር። የደርግ መምጣት ግን ብዙዉን አስጥሏል። እኔ ራሴ ትምህርት ቤት ሳለሁ ኦሮሞዎችን በጸያፍ ቃል የጠሩ ተማሪዎች ትምክህተኛ ተብለዉ ግርፋት የደረሰበቸዉና ዘብጥያ የወረዱም እንደነበሩ በደምብ አዉቃለሁ። ኦሮሞዎች ብቻ አይደሉም እንዲህ ተብለዉ የተጠሩት፤ ሌሎችም ብሔረሰቦች አሉ። አማራና ትግሬ ብቻ አይደሉም ኦሮሞዎችን በጸያፍ ቃል ይጠሩ የነበሩት። ሌሎችም እዳጣን ብሔረሰቦች ኦሮሞዎችን በጸያፍ ቃል ይጠሩ እንደነር አሳምሬ ነዉ የማዉቀዉ። በደቡብ እትዮጵያ ተወልጄ ያደግሁና ኦሮምኛና ጋሞኛ ወይም ወላይትኛ እናገራለሁ። እስቲ ራሳችሁን ጠይቁ ወላይታዎችን ምን ብላችሁ ትጠሩ እንደነበር። ጠቅላይ ሚኒስትር ሀይለማሪያም ደሳለኝ ቢጠየቁ የየትኛዉ ብሔረሰብ ግለሰብ ወላይታዎችን በትክክል ወላይታዎች ብሎ ይጠራል ተብለዉ ቢጠየቁ በእኔ እምነት ጋሞዎች፣ በቅርብ ያሉ ኩሎ
ኮንታዎች እና በወላይታ አካባቢ ተወልደዉ ያደጉ መጤዎች ብቻ ናቸዉ እንደሚሉ አልጠራጠርም። እንዲህ አይነቱ ጸያፍ አጠራር በየአህጉሩና በየአገሩ አለ። እንዲህ ያለዉ ጸያፍ አጠራር በትምህርት የሚወገድ እንጂ በግዳጅ ወይም በጉልበት የሚጠፋ አይደለም።። በዚህ አይን ከሆነ ጉራጌዎች ምን ሊሉ ነዉ? ከጉራጌ የባሰ በኢትዮጵያ ዉስጥ ቀልድ የሚቀለድበት ተረት የሚተረትበት ብሔረሰብ አለ ወይ? ስንቱ ብሔረሰብ የጉራጌን ብሔረሰብ ይቅርታ ሊጠይቅ የሚገባ ይመስላችሗል? ይህ ሁሉ የትምክህት ዉርጅብኝ በጉራጌዎች ላይ ሲደርስ ጉራጌዎች ሰላማዊ ሰልፍ የወጡበት ወይም አመጽ የፈጠሩበት ወቅት ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። ሆኖም ግን ትምክህታዊ ቀልድና ንቀት ጉራጌዎችን ከኢትዮጵያዊነታቸዉ ፍንክች አላደረጋቸዉም። ጉራጌዎች ቀልድን እንደ ቀልድ አገርን እንደ አገር በመዉሰድ ለወያኔ ትምክህተኞች እንኳን አልተበገሩም። አገር አፍራሽና ዘረኛ የወያኔዎች ፕሮፓጋንዳ በጉራጌዎች ዘንድ እንደማፈሪያ ስለተቆጠረ ወያኔዎች ጉራጌ ነጋዴዎችንና ባለሀብቶችን በዘረፋ ቂም እንዲወጡ አስገድዷቸዋል። አናሳ ብሔረሰብ ሆነዉ እንኳን አቅምና ችሎታቸዉን በመገንዘብ የበሰለ ትእግስት፣ ብሔረሰባዊ ባህርይና ጠንካራ የሰራተኛነት ባህል ለኢትዮጵያ ህዝብ አስተምረዋል። እስቲ ይታሰብበት! ወያኔ አንዱን ብሔረሰብ ከሌላዉ ለመለያየት ከተጠቀመባቸዉ ዘዴዎች እንዲህ አይነቱን የህብረተሰብ ደካማ ጎን ከሚፈለገዉ በላይ አጉልቶ በማነብነብ አንዱ ብሔረሰብ በሌላዉ ላይ እንዲነሳና በጠላትነት እንዲፈርጀዉ አድርጓል። በጋራ ወያኔ/ኢህአዴግን ለመጣል በሚደረገዉ ትግል ላይ እንዲህ አይነቱ ደካማ የህብረተሰብ ጎን ብዙ ስንክሳርን ያስከትላል። ትልቁንና ዋናዉን ትግል ወደ ጎን በመተዉ
ህዝቦች በጥቃቅን ነገሮች ላይ አተኩረዉ እርስ በርስ ሲናቆሩ ማየት የወያኔዎች መሳለቂያ መሆን ነዉ። ይህን የመሰሉ የህብረተሰብ ደካማ ጎኖች የትግሉንም ወቅት ያራዝሙታል።

ለመሆኑ ኦነጎች አፄ ሀይለ ስላሴ ኦሮሞ እንደነበሩ ይገነዘባሉ ወይ? ተፈሪ መኮንን ወልዴ ጉዲሳ እንደነበር ስማቸዉ? እናታቸዉ ወ/ሮ አለምነሽ አሊ ጉራጌና ኦሮሞነት እንዳለባቸዉ ይረዳሉ? በዘር እንምጣ ከተባለ አፄ ሀይለ ስላሴ የመጨረሻዉ የኢትዮጵያ ኦሮሞ ንጉስ አይደሉምን? ትንሽ የአማራ ደም ጠብታ በዘራቸዉ ስለነበር በአማራና በኦርቶዶክስ ስም ለአርባ ሶስት አመታት ኢትየጵያን በፍጹማዊ ንጉስነት ገዝተዋል። በዚህ የንጉስነት ዘመን በብዙ ኦሮሞ ጀኔራሎችና መኳንቶች ተከበዉና ተወድሰዉ ኖረዋል። አፄ ሀይለ ስላሴ በሳል፣ ጮልና ዉስብስብ ያለ ዘመናዊ የአስተዳደር ዘዴ የነበራቸዉ ንጉስ ነበሩ። ለዚህ ነዉ እንዴ አፄ ሀይለ ስላሴ አማራ ሆነዉ የአማራን ምድር ያለሙት ልክ ወያኔዎች ትግራይን እንዳለሙት? ላለፉት ሀያ ሁለት አመታት ስንት አማራዎችና ሌሎች እዳጣን ብሔረሰቦች ሲጨፈጨፉ ኦነግ ምን ያህል ነዉ በዚህ ጉዳይ ተወያይቶ ወይም ይህን ጉዳይ በተመለከተ ለማጋለጥ የሞከረዉ? አፄ ሀይለ ስላሴ ለፈጸሙት ግፍ ሁሉም አማራ በጅምላ መወንጀል አለበት ወይ? አፄ ሀይለ ስላሴ በአማራዉ ህዝብ ላይ ግፍ አልፈጸሙም እንዴ? የአማራ ወይም የትግራይ ብሔረሰብ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለደረሰዉ ግፍ ብቸኛ ተጠያቂ ሊሆን ይገባዋል ወይ? ኦሮሞዎችስ በንጉሳዊ፣ በደርግና በወያኔ አገዛዞች የተጠያቂነት ድርሻ አይገባቸዉም ወይ? ኦህዴድ ማን ነዉና? ወያኔዎች ያለ ኦህዴድ እገዛና ድጋፍ ኦሮሞዎችን አሳድዶ መግደል፣ ማሰርና ማንገላታት ይችሉ ነበር ወይ? ኦነግስ ቢሆን በሽግግር መንግስቱ ተካፍሎ አልነበረምን? በደርግ ጊዜስ
ቢሆን ስንቱ ኦሮሞ ነዉ በቀይ ሽብር የተካፈለዉ? አናዉቅምና ነዉ እንዴ? ኦሮሞዎችም ተጠያቂዎች ናቸዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለተደረገዉ ሁሉ። ማንም ከሃላፊነት የሚድን የለም። ሁሉም እንደየድርሻዉ ተጠያቂነት አለበት። ሆኖም ግን አንድን ብሔረሰብ እንደተጠያቂና ሌላዉን ብሔረሰብ ደግሞ ተጠያቂ እንማይሆንና ተበዳይ ብቻ እንደሆነ አድርጎ ማቅረብ ለችግሩ መፍትሄ አይሆንም። የዛሬ አንድ መቶ አመት ለተፈጸመዉ ነገር ዛሬ ትክክለኛና ፍትሀዊ መፍትሄ እንደመፈለግ ፈንታ ያንን ነገር እየደጋገሙ ማንሳቱና ከሚገባዉ በላይ አጋንኖ በየጊዜዉ ማቅረቡና የመወያያ ነጥብ ማድረጉ የሚያሰተዛዝብ ነገር ይመስለኛል።

ወጣት ጃዋር ሲራጅ ሆይ! ባንተ እድሜ ክልል ያሉት ወጣት ኢዮጵያዉያን እንዳንተ ካለ ሰታንፎርድ ዩኒቨርስቲ ከተማረ ወጣት ኢትዮጵያዊ ብዙ ምሁራዊ አስተሳሰብና ተስፋ ይጠብቃሉ። ለረጅም ጊዜ በትግል ላይ ከቆዩ ኦሮሞዎች የሰነዘርካቸዉ ሀሳቦች ቢሰነዘሩ ኖሮ ምንም አልነበር። ሆኖም ግን ወጣቱ ትዉልድ በተራማጅ አሰተሳሰብ በቀላሉ የሚማረክ፣ ዘመናዊ አስተሳሰብን የሚወድ፣ ለአገሩ ደሙን ለማፍሰስ በቀላሉ የሚሰለፋና የህዝቦችን መዋሃድና መቀላቀል የሚፈልግ የህብረተሰብ አካል ነዉ። ለወጣቱ ትዉልድ ሊሰጥ የሚገባዉ ትምህርት በጣም ጥንቃቄ ሊደረግለት ይገባዋል። ወያኔዎች በጎሳ ፖለቲካ የወጣት ትግራዉያንን አእምሮ አደንዝዘዉ በጉልበት መርተዉና መስዋእት አድርገዉ ነዉ እዚህ ደረጃ የደረሱት። ኢህአፓ ወጣቱን በመምራት በቀይ ሽብር ወቅት ለብዙ ወጣቶች እልቂት ምክንያት ሁኗል። ሻቢያም እንዲሁ። ኦነግም ቢሆነ ለወጣት ኦሮሞዎች እልቂት ከተጠያቂነት አይድንም። የብሔረሰብ ወይም የጎሳ ፖለቲካ ከብሔራዊ ወይም ከአገራዊ ፖለቲካ ጋር የሚቃቃርና የማይጣጣም ከሆነ ሀገራዊ መፍትሄ በቀላሉ ይገኛል ብዬ አላምንም። የኦሮሞነት ጥያቄ ብቻዉን መፍትሔ ይሆናል ብዬ አላምንም። ምክንያቱም ከኤርትራ መገንጠል ብዙ የምንማረዉ ነገር አለና። ኦሮሞዎች የራስን እድል በራስ የመወሰን መብት አግኝተዉ በተሻለ አስተዳደር ስር የኦሮሞ መስተዳደር ቢመሰረት እንኳ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር እስካልተቋቋመ ድረስ የጉልቻ መቀያየር ነዉ የሚሆነዉ። ቅኝ ገዢዎች ከአፍሪካ ከወጡ በሗላ
በምትካቸዉ የገቡት የአፍሪካ ብሔረተኛ መሪዎች ህዝቦቻቸዉን ከብዝበዛና ከጭቆና አላላቀቁም። መንግስቱ ሄዶ መለስና ኢሳያስ መጥተዉ ምን መሰረታዊ ለዉጥ አመጡ? ሁላችንም ያየነዉና የምናየዉ አይደለም ወይ? ኦሮሞዎች በተፈጥሮ ዲሞክራሲያዉያን ሆነዉ አልተፈጠሩም ወይም አማራዎች ወይም ትግሬዎች አምባገነን ሆነዉ አልተፈጠሩም። ሁሉም ንጹሀን ሆነዉ ነዉ የተፈጠሩት። ሰይጣንነቱን ወይም ጻድቃንነቱን እዚህ ምድር ላይ ነዉ የተማሩት። ሀገራዊ ዲሞክራሲያዊ ባህርይ የሌለዉ የፖለቲካ ፈለግ “አለባብሰዉ ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” የሚባለዉን ተረት ያሰታዉሰናል። የኢትዮጵያን አጀንዳ ካላስቀደምን የኦሮሞን አጀንዳ ማስቀደም ብሔራዊ ትግሉን ይጎዳል። የኢትዮጵያን አጀንዳ ስናስቀድም የኦሮሞም አጀንዳ በአግባቡ እንዲካተት በማድረግ ብሔራዊ ትግሉን ማጠናከር ይቻላል። አማራዉ፣ ትግሬዉ፣ ወላይታዉ፣ ጉራጌዉ፣ ሲዳማዉ፣ ግዲኦዉና ሌላዉ ብሔረሰብ በኢትዮጵያ አጀንዳ ዙሪያ እንጂ ሊሰባሰብ የሚችለዉ መጀመሪያ የኦነግ አጀንዳ ይገባደድና የኢትዮጵያ አጀነዳ ይከተላል ቢሉት እምቢ ለሀገሬ ነዉ የሚለዉ። ምክንያቱም አብረን እንነሳለን ወይም አብረን እንወድቃለንና።

በመጨረሻም “ድር ቢያብር አንበሳን ያስር” የሚባለዉን ተረት ላስታዉስህ ስወድ ወጣት ጃዋር መሐመድ ከላይ የጠቀስኳቸዉን ሀሳቦች ሚዛን ዉስጥ በማስገባት ለማለት የፈለግሁትን ትረዳለህ ብዬ እገምታለሁ። ኢትዮጵያ ላንተም ለእኔም አኩል ነች። “የእናት ሆድ ዝንጉርጉር” እንደሚባለዉ ሁሉ ሰዉ ሰራሽ በሆነ ምግባረ ብልሹ አስተዳደር ምክንያት በጎሳ ተለያይተን ሊኖረን የሚገባንን አንድነትና ሀይል አጥተናል ሊኖረን ሲገባ። አንድነትና ሀይል ማግኘት አቅቶን ሳይሆን ከልብ ካለመደማመጣችን የተነሳ ነዉ ብዬ አምናለሁ። ስለሆነም ለሁላችንም በጋራ የሚበጅ የአስተዳደር ስርአት ለመመስረት ከልብ ተደማምጠንና ተቻችለን ትግሉን በጋራ አካሂደን ከፋፋይና ዘረኛ ወያኔዎችን አስወግደን ሀራችን ኢትዮጵያን የፍቅር፣ የሰላምና የዲሞክራሲ አገር እንድትሆን ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናድርግ። ለምን ብትለኝ “ሞኝ የእለቱን ብልህ ግን የአመቱን” እንዲሉ።

shenqatawu@yahoo.com

 

Advertisements

Posted on July 9, 2013, in ETHIOPIA AMHARIC and tagged , . Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: