መስከረም ሁለት – ኢትዮጵያ ትቅደም! (ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ)

‹‹እንኳን ከ፲፱፻፷፮ ዓ.ም ወደ ፲፱፻፷፯ ዓ.ም አዲሱ ዓመት ከሰላማዊ የአስተዳደር ለውጥ ጋር በደህና ያሸጋገራችሁ፤ ይህ ያለምንም ደም መፋሰስ የተጀመረው ‹ኢትዮጵያ ትቅደም› ዓላማ መሰላል ሆኖ የመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ኑሮ የሚቀራረብበት፣ አንድነታችንን የሚያጠናክርበት ዘመን እንዲሆን እንመኛለን,,, ‹ኢትዮጵያ ትቅደም!› መጪው ዘመን የሰላም የለውጥ ጊዜ ይሁንልን፡፡›› (አዲስ ዘመን ጋዜጣ መስከረም 3 ቀን 1967 ዓ.ም)

እነሆም ይህ ክስተት ከሶስት ቀን በኋላ ሰላሳ ዘጠነኛ ዓመቱን ይደፍናል፤ በዚህ የመፅሄታችን ልዩ ዕትምም ታሪኩን መዘከርና ባለውለታዎቹን ማመስገን ወደድኩ፡፡

ቅድመ-አብዮት

በ1953 ዓ.ም ‹የነዋይ ልጆች› ያስተባበሩት መፈንቅለ መንግስት በርካታ መኳንንትንና ሹማምንትን የህይወት መስዋዕትነት አስከፍሎ ቢከሽፍም፣ በጥንታዊቷ ‹የባላባቶች› ኢትዮጵያ በአጭር ጊዜ ውስጥ የነፃነት ጎህ መቅደዱ አይቀሬ መሆኑን አመላክቶ ነበር ያለፈው፡፡ የአቤ ጉበኛ ‹‹አልወለድም›› እና የጄነራል አብይ አበበ ‹‹አውቀን እንታረም›› መፅሀፍት፤ አምባሳደር ብርሀኑ ድንቄ ለንጉሱ የላኩት ረጅም ደብዳቤ እና ሀዲስ አለማየሁ ‹‹የገለፅኩበት ቋንቋ ትንሽ ወፈር ያሉ መሆናቸው ይሰማኛል›› በሚል ሀረግ በመፈንቅለ መንግስቱ ማግስት ለአፄው ያቀረቡት ማስታወሻ በገደምዳሜ ይህንኑ አመላካች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ ጊዜው ደርሶ ትንግርቱ ሲፈፀም፣ ታሪክ የተጎረደውንም መቀጥል የሚችልበት አጋጣሚ እንዳለ ያሳየበት ክስተትም ነበር፤ ይኸውም ተማሪዎቹ የለውጥ ንቅናቄውን ፈትለው የገመዱት በመፈንቅለ መንግስቱ ሙከራ የባለስልጣናት ደም የፈሰሰበት ‹ልዑል መኮንን ቤተ-መንግስት›ን ገደ-ቢስ (ክፉ ምልኪ) አድርገው የወሰዱት ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ ሠፈራቸውን ወደ ‹ኢዮቤልዩ ቤተ-መንግስት› ቀይረው፣ ‹ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ› (የዛሬው አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ) ይሆን ዘንድ በፈቀዱት ያው ግቢ መሆኑ ነው፡፡

በእነጄነራል መንግስቱ ነዋይ ጉልበቱ የተፈተነው የዘውድ አስተዳደር፣ ከአስራ አራት ዓመት የተማሪዎች ጠንካራ ትግል በኋላ በወርሀ የካቲት (1966 ዓ.ም) የዘመኑ ዘጋቢዎች ‹ማምለጡ አዳጋች ነው› ያሉት ድንገቴ አጣብቂኝ ተፈጠረበት፤ ነገሩ እንዲህ ነው፡- በአረቦችና እስራኤል ጦርነት የተነሳ የስዊዝ ካናል መዘጋት ባመጣው የአለም አቀፍ የነዳጅ ዋጋ ንረት የካቲት 6 በነዳጅ ላይ የአስር ሳንቲም ማሻሻያ መደረጉን ተከትሎ፣ የካቲት 11 የታክሲ ሹፌሮች ጭማሪውን፣ መምህራን አዲሱን ‹ሴክተር ሪቪው› የትምህርት ፖሊሲ በመቃወም የስራ ማቆም አድማ መቱ፤ የካቲት 13 ተማሪዎችና የመንግስት ሰራተኞች ለተቃውሞ ሰልፍ አደባባይ ወጡ፤ ሁኔታዎች መባባሳቸውን ያስተዋለው የአፄው መንግስት የካቲት 16 ነዳጅ ላይ የጨመራትን አስር ሳንቲም ማንሳቱን በይፋ ቢያሳውቅም፣ ተቃውሞውን ሊያስታግስለት አልቻለም፤ በዚሁ ዕለት በተለያዩ ካምፖች የሠፈሩ የሠራዊቱ አባላት የንቅናቄው ደጋፊ መሆናቸውን ከመግለፅ ባሻገር ‹‹አቆርቋዥ›› ሲሉ የወነጀሏቸውን የጦር አዛዦች በቁጥጥር ስር አዋሉ፤ ንጉሱም የካቲት 19 መፍትሄ ይሆናል በሚል ስልት የጠቅላይ ሚንስትር አክሊሉ ሀብተወልድን ካብኔ አፍርሰው በእንዳልካቸው መኮንን የሚመራ አዲስ ካቢኔ አቋቋሙ፤ ይሁንና የንቅናቄው አራማጆች ‹ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም!› ብለው ትግሉን አቀጣጠሉ፡፡ ሠራዊቱም ከአዛዦቹ በተጨማሪ የሲቪል ባለስልጣናትን ማሰሩን ሳያቋርጥ ከባድ ክረምት የተሸከመው ወርሀ ሰኔ ደረሰ፡፡

አፄው ለመጀመሪያ ጊዜ ለህዝብ ጥያቄ ተንበርክከው ሹም-ሽር ማድረጋቸው የአብዮቱን ወደ መጨረሻው ምዕራፍ መዳረስ በማብሰሩ፣ የኢትዮጵያ ወታደር በዩኒቨርስቲና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደጃፎች የሚደረጉ የተቃውሞ ሰልፎችን ለመበተን ይወድረው የነበረውን አፈ-ሙዝ ወደ ዙፋኑና ባለሟሎቻቸው አዞረው፡፡ ሰኔ 21 ቀን 1966 ዓ.ም ከጦር ሠራዊት፣ ከክቡር ዘበኛ፣ ከብሄራዊ ጦር፣ ከፖሊስ አባላት የተወከሉ መለዮ ለባሾች ‹የጦር ኃይሎች፣ የፖሊስ ሠራዊትና የብሔራዊ ጦር አስተባባሪ› በሚል ስያሜ (ሐምሌ 1/1967 ዓ.ም ‹ደርግ› በሚል መቀየሩን ልብ ይሏል) በአራተኛ ክፍለ ጦር ግቢ ተሰባስበው ሲያበቁ ኮሚቴ አቋቋሙ፡፡ ዕለቱንም ሻለቃ መንግስቱ ኃ/ማርያም ሊቀ-መንበር፣ ሻለቃ አጥናፉ አባተ ምክትል ተደርገው ተመረጡ፡፡ በወቅቱ የሆነውንም ገስጥ ተጫኔ (ዘነበ ፈለቀ) ‹‹ነበር››  በሚል ርዕስ ባሳተመው ቅፅ አንድ መፅሀፉ እንዲህ ገልፆታል፡-

‹‹ሰኔ 20 ቀን 1966 ዓ.ም ሻለቃ አድማሴ ዘለቀ፣ ንቡረ ዕድ ድሜጥሮስና አቶ አበበ ወንድሜነህ የተባሉ የፓርላማ አባላት ወደ አራተኛ ክፍለ ጦር ጠቅላይ መምሪያ ሄደው በምድር ጦር መሐንዲስ ትምህርት ቤት (ጎፋ ሠፈር) ውስጥ በጥበቃ ሥር የሚገኙ ባለስልጣኖች እንዲለቀቁ በአማላጅነት ጠየቁ፡፡ ጦሩ በዚህ ድርጊታቸው በቁጣ ገንፍሎ እነርሱንም በቁጥጥር ሥር አዋላቸው፡፡ ይህ ቁጣው ሻለቃ መንግስቱ ኃ/ማርያም ወልዴ የሚባሉ፣ አጭር፣ ኮሳሳና ቁጡ ሰው ወደ ሥልጣን ያመጣል ብሎ ያሰበ አልነበረም፡፡›› (ገፅ 8)

የኢትዮጵያ ወታደር በዚህ መልኩ አብዮቱን መቀላቀሉ ስህተት ነው ብዬ አላስብም፡፡ በየትኛውም ሀገር ለስኬት የበቃ የአብዮት ታሪክ ንባብ እንደሚያትተው ህዝብ የመንግስት ለውጥ ፈልጎ አደባባይ በመውጣት ጫና ፈጥሮ ስርዓቱን ያዳክማል እንጂ፣ የቤተ-መንግስት አጥር ሰብሮ ወንበር አይይዝም፤ በቅርቡ በቱኒዚያና በግብፅ (ሆስኒ ሙባረክን ለማስወገድ) የታየውም የሠራዊቱ ጣልቃ-ገብ መግፍኤ ይኸው ነው፡፡ ሻለቃ መንግስቱና ጓደኞቹም ያደረጉት ተመሳሳዩን ነው፡፡ በዚህ አይነት የህዝብ አመፅ ወቅት ‹በእምቢተኝነት› ሥልጣን የሙጢኝ ያለ መሪን ለሕዝብ ፍላጎት የማስገዛትና ሀገር የማረጋጋት ኃይል ያለው በሠራዊቱ መዳፍ ብቻ እንደሆነ መረሳት የለበትም፡፡ በተቀረ ደርጎች በስልጣን ነጠቃም ሆነ በጭፍጨፋ የሚከሰሱት ከለውጡ በኋላ ያ ሁሉ መስዋዕት የተከፈለበትን የ‹‹ህዝባዊ መንግስት›› ጥያቄ አሳክተው ወደ ጦር ሠፈራቸው ከመመለስ ይልቅ በጥያቄው ላይ አምፀው በፈፀሙት ውንብድና ነው፡፡ በዚህ ፅሁፍ ‹‹መስከረም ሁለት››ን ለመዘከር የተገደድኩበት ምክንያት ብዬ የምጠቅሳቸው ሀገራዊ ጉዳዮች በሙሉ ለፍሬ በማብቃቱ የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው ደርጉ ሳይሆን የተማሪው ትግል መሆኑን ግን በቅድሚያ አስታውሳለሁ፡፡

ደርግ

መንግስቱ ኃ/ማርያም የደርጉ ሊቀ-መንበር ሆኖ ከተመረጠ በኋላ ግድግዳው ላይ በተሰቀለው ሰሌዳ ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› የሚል መፈክር መፃፉ ዛሬም ደርጉንና ተቺዎቹን እንዳወዛገበ ነው፡፡ የውዝግቡ መንስኤ መንግስቱ የፃፈውን ሀረግ ተከትሎ የደርግ አባላት ‹‹ሀገሪቱን የምንመራው ‹ኢትዮጵያ ትቅደም!› በሚል የፖለቲካ ፍልስፍና ነው›› በማለታቸውና ከዚህ ቀደም እንዲህ አይነት ፍልስፍና ባለመኖሩ ‹ከየት አመጣችሁት?›፣ ‹ምን ማለትስ ነው?› ለሚሉ ጥያቄዎች መልስ መስጠት አለመቻል ነበር፡፡ መንግስቱ ኃ/ማርያም አለመግባባቱ የተፈጠረበትን አጋጣሚ ‹‹ትግላችን›› በሚል ርዕስ ባሳተመው መጽሀፉ እንዲህ ሲል ገልፆታል፡-

‹‹በተፈጥሮው እጅግ ችኩል የሆነው የማስታወቂያ ኮሚቴ ሊቀ-መንበር …ደርግ በተቋቋመበት ቀን የደርጉ አባላት የእኔን አስተዋጽኦ በጠየቁኝ መሰረት ያሉኝን ሃሳቦች ሳቀርብ የመጀመሪያው የደርጉ የፖለቲካ ወይም የትግል መፈክርን ‹ኢትዮጵያ ትቅደም› እንዲሆን ማሳሰቤ ይታወሳል፡፡ ጉባኤው መፈክሩን በይሁንታ እንዳፀደቀው ሻለቃ አስራት ከስብሰባው አዳራሽ ሹልክ ብሎ በመውጣት የሀገር ውስጥና የውጭ ጋዜጠኞችን በመሰብሰብ ‹የደርጉ የፖለቲካ ፍልስፍና ኢትዮጵያ ትቅደም ይባላል› በማለቱ እስከ ዛሬ በተራማጅ ምሁራን ዘንድ ሲያስተቸን ይኖራል፡፡›› (ገፅ 153-154)

ይሁንና በወቅቱ የነበሩ የመንግስት ሚዲያዎች በ‹ኢትዮጵያ ትቅደም› ዓላማ መሰረት እያሉ የሚዘረዝሯቸው የፖለቲካ ሃሳቦች እንደነበሩ ይታወሳል፡፡ ደርጉ ወደ ጅምላ ጭፍጨፋው ሲንደረደር ያስተላለፈው ማስጠንቀቂያ ‹‹የኢትዮጵያ ትቅደምን ዓላማን በመቃወም፣ የሥራ ማቆም አድማ፣ የተቃውሞ ሰልፍ የሚያደርግ… ጥብቅ እርምጃ ይወሰድበታል!›› የሚል እንደነበረም ይታወሳል፡፡

የሆነ ሆኖ ይህ ዕለት (ይህ ፅሁፍ) አብዮቱ ጎርምቶ የሠራዊቱን ጣልቃ መግባት ባሻበት በዛች ቀውጢ ወቅት ቆራጦቹ ሻለቃ መንግስቱና ጓዶቹ የነበራቸውን አበርክቶ ማመስገንና መዘከር በመሆኑ ወቀሳውን እዚሁ ገተን (ሁነቱን ‹ዝግምተኛ መፈንቅለ መንግስት› ነበር የሚለውን ሙግት ሳንዘነጋ) ወደዚያው አንለፍ፡፡

ደርግ፣ የጦር ካምፑን ወደ አብዮት ካምፕ ቀይሮ በወርቃማ ቀለም ያስከተበውን ታሪክ በሁለት ከፍለን ከመደብነው፡- የመጀመሪያው የዘውድ ስርዓቱን ለመለወጥ ከሰኔ 20/1966 ዓ.ም አንስቶ፣ መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም ድረስ ባሉት ሰባ ጭንቅ ያማጡ ቀናት ውስጥ የሚወድቀው ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ከለውጡ በኋላ የተወሰዱ ታላላቅ እርምጃዎችን የሚያካትት ይሆናል፡፡

                                                                                                                         አብዮቱ-ያችን ሰዓት!

ደርግ በይፋ ከተቋቋመ ከሁለት ቀናት በኋላ የታሪኩ ‹ምዕራፍ አንድ› ደረጃ በደረጃ እንዲህ ይጀምራል፡- ለፖለቲካ እስረኞች ምህረት አደረገ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አክሊሉ ሀብተወልድ አብዮቱን ለመቀልበስ ያቋቋሙትን ‹ብሔራዊ የፀጥታ ኮሚሽን› አፍርሶ፣ በእርሳቸው ትዕዛዝ ‹አመፀኛ› ተብለው የታሰሩ የሠራዊቱ አባላትን በነፃ ለቀቀ፤ ሜ/ጄነራል አማን ሚካኤል አንዶምን በሌፍተናንት ጄነራል ማዕረግ  የጦር ኃይሎች ኤታማዦር አድርጎ አስሾመ፤ ባለስልጣናቱ ለግል መጠቀሚያ የወሰዱትን ሁሉንም አይነት የመንግስት ንብረት እንዲመልሱ በብዙሀን መገናኛ አዘዘ፤ የጠ/ሚኒስትር እንዳልካቸው መኮንን ካቤኔን አፍርሶ፣ ልጅ ሚካኤል እምሩን ተካ፤ የዙፋን ችሎት፣ የዘውድ ምክር ቤትና የፍርድ አጣሪ ጉባኤን አፈረሰ፤ አፄው የደህንነት፣ የጦርና የሲቪል ባለስልጣኖቻቸውን እና መላ ሀገሪቷን በዘመናዊ መንገድ አዋቅረው የሚሰልሉበትን ‹‹የንጉሰ ነገስት ልዩ ኤታማዦር›› የተሰኘ ተቋም በመከላከያ ሚኒስቴር ስር እንዲጠቃለል ወሰነ፤ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ለደርግ ሳያሳውቁ ገንዘብ እንዳያንቀሳቅሱ ከለከለ፤ በቀዳማዊ ኃ/ስላሴ የግል ይዞታ ስር የነበሩት የብሔራዊ ልማት አክሲዮን፣ የአንበሳ አውቶብስ ድርጅት እና የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካን ባለቤትነት ወደ መንግስት አዞረ፤ የመሳፍንትና ባለስልጣናት ልጆች በመንግስት ገንዘብ ወደ ውጭ ሀገር ሄደው መማራቸውን አገደ…

በዚህ መልኩ በዝግታ የተጓዘውን አብዮት የመሩት የደርግ አባላት ለመጨረሻው ውሳኔ ጳጉሜ 4/1966 ዓ.ም ተሰበሰቡ፤ ሙሉውን ቀንም በአጀንዳው ላይ ሲከራከሩና ሲመክሩ ውለው፣ ጀንበር ስታዘቀዝቅ በለመዱት አሰራር ወደ ድምፅ መስጠቱ አመሩ፣ በውጤቱም ከ1909 ዓ.ም እስከ 1923 ዓ.ም በ‹አልጋ ወራሽ›ነት፤ ከ1923 ዓ.ም እስከ እዚህች ዕለት ደግሞ በ‹ንጉሰ- ነገስት› ማዕረግ በሀገሪቱ ላይ የፈጣሪን ያህል የተከበሩትን ቀዳማዊ አፄ ኃ/ስላሴ ከዙፋናቸው እንዲወርዱ በአብላጫ ድምፅ ወሰኑ፡፡

ከውሳኔው በኋላ እንቅፋት እንዳይኖርና ህዝቡን በስነ-ልቦና ለማዘጋጀት በማሰብ የተንዛዛውን የንጉሱን 80ኛ ዓመት የልደት በዓል አከባበርን፣ በወሎና በትግራይ ከተከሰተው አስከፊ ረሀብ ጋር እያነፃፀረ የሚተርክ አሰቃቂ ፊልም በቴሌቪዥን አስተላለፉ፤ ፊልሙ እንደተጠናቀቀም ቀዝቃዛው የክረምት ምሽት ያቆረፈዳቸው የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ስሜት በፈነቀላቸው ነዋሪዎች ተቃውሞ ተጥለቀለቁ፤ በማግስቱም (በአዲሱ ዓመት) ይኸው ትዕይንት ቀጥሎ ዋለ፤ በዕለቱ የሆነውን ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ከላይ በጠቀስኩት መፅሀፉ እንዲህ ገልጾታል፡-

‹‹መስከረም 1 ቀን 1967 ዓ.ም በጉልታዊ ሥርዓተ-ማህበር የሚመራው ፈላጭ ቆራጭ፣ መለኮታዊ የዘውድ አገዛዝ ተገረሰሰ›› (ገፅ 492) 

መስከረም 3/1967 ዓ.ም የታተመው ‹‹አዲስ ዘመን›› ጋዜጣ ደግሞ ‹‹ትናንት ጠዋት›› በሚል ርዕስ ባስነበበው ዘገባ፡-

‹‹ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ ከሥልጣን መውረዳቸው በጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር መታወጁን የአዲስ አበባ ኗሪ ትናንት ጧት በአንድ ሰዓት ተኩል ላይ በኢትዮጵያ ሬዲዮ ሲሰማ፣ ምንም አይነት መደናገጥና መሸበር ሳያደርስ እንደተለመደው ወደ ሥራ መስኮቹ ሲሰማራ ታይቷል፤ …የለውጡን ሁኔታ ለመከታተል በብዛት ወደ አደባባዮች እና ዋና መንገዶች የወጣው ሕዝብ ወደ ሥራውና ቤቱ እንዲሄድ ወታደሮች በኩምቢቮክስ ባገን መኪና ውስጥ ሆነው በድምፅ ማጉያ ‹ስለተባበራችሁን ከልብ እናመሰግናለን፤ ሆኖም የእናንተ እዚህ መሰብሰብ አስፈላጊ መስሎ ስላላገኘነው ወደየሥራችሁ እንድትሄዱ እንጠይቃለን› በማለት እየተዘዋወረ አሳስቧል፡፡›› ሲል ነበር በሕዝቡ ዘንድ የነበረውን ድባብ የገለፀው፡፡

እነሆም እዚህ ድረስ ለሆነው ሁሉ ‹ቪቫ አብዮታዊያን፣ ቪቫ ደርግ፣ ቪቫ መንጌ!› ማለትን ወደድኩ!

 የአብዮቱ-ማግስት

ንጉሱ ከዙፋናቸው ከተነሱ በኋላ የታሪኩ ‹ምዕራፍ ሁለት› እንዲህ ይቀጥላል፡- የመሀይምነት ጨለማ አስጥሞት ለነበረው አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ማንበብና መፃፍ የሚችልበትን መሰረት ለመጣል ‹‹የዕድገት በህብረት የዕውቀትና የሥራ ዘመቻ››ን አውጇል፤ ኃይማኖትና መንግስት የተለያዩ መሆናቸውን እና ‹ሁሉም ቤተ-እምነት ያለአድልኦ በዕኩልነት ይታያሉ› የሚል ደንብ አውጥቷል፤ በስርዓቱ ሹማምንትና ባላባት ቁጥጥር ስር የነበረውን የገጠር መሬት፣ እንዲሁም የከተማ ቦታና ትርፍ ቤቶች የመንግስት መሆናቸውን ደንግጓል፡፡ …እነዚህ ሁሉ ተንሻፈው የተመለሱ ቢሆኑም ተማሪው ያነሳቸው ከነበሩ ጥያቄዎች ውስጥ መመደባቸውን ግን መካድ አይቻልም፡፡

በአናቱም በወቅቱ ከኢትዮጵያ በተሻለ ጥራት ሠራዊቷን ያደራጀችው ሶማሊያ ‹በእኔነት› ዕብሪት በሐረርጌ፣ ባሌና ሲዳሞ የፈፀመችውን የኃይል ወረራ ለመመከት ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያምና ጓዶቻቸው ኃላፊነታቸውን በሚገባ ተወጥተዋል፤ በሶቭየት ህብረት፣ በኩባና የመን አደራዳሪነት የተሞከረው ሽምግልና በሶማሊያ እምቢ-ተኝነት ከከሸፈ በኋላ፣ ከምስራቁ ካምፕ የጦር መሳሪያ እና ፖለቲካዊ ድጋፍ ለማግኘት ያደረጉት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት የሚያስመሰግን ነው፤ የሶማሊያው መሪ ዚያድ ባሬ በወታደሩ ጥንካሬ ተማምኖ በሰላም ሂደቱ ላይ ለመሳተፍ ከመለገሙ ጋ ተያይዞ መንግስቱ ኃ/ማርያም በየመን-ሰንዓ በተደረገ ድርድር ላይ የተፈተነበትን ገጠመኝ ከራሱ መፅሀፍ ልጥቀስላችሁ፡-

‹‹ጓድ ፊደል ካስትሮ ከምክትል ፕሬዘዳንታቸው ጋር፣ ጓድ አብዱል ፈታህ ከፕሬዘዳንቱ ጋር አራት ሆነው መጡ፤ ከስብሰባው በፊት ወደ እኛ የመጡበት ምክንያት ‹ሶማሊያዎቹ ይህ ውይይት እንዳይሳካ የማይፈጥሩት ችግር ስለሌለና ምናልባትም የእናንተን ትዕግስት የሚፈታተን የብልግናና የዘለፋ ቃላቶችን ከመሰንዘር ስለማይመለሱ በእናንተ በኩል እስከ መጨረሻው ትዕግስታችሁን እንጠይቃለን›  አሉን፡፡ በእኛ በኩል ምንም ችግር እንደማንፈጥር በማረጋገጥና በማበረታታት መልሰን ሸኘናቸው፡፡ …የሶማሊያው መሪ ማንንም ሳያነጋግር ወይም ሳይጨብጥ አዳራሹ ማዕከል ሜዳ ላይ ሁለት እጁን ሱሪ ኪሱ ከቶ ዘለግ ባለ ድምፅ ‹ሁለት ስቱፒድ የሆንን ሕዝቦች አስቸገርናችሁ አይደለም?› በማለት ተናግሮ ወደ መቀመጫው ሲያመራ ከአነጋገሩ በላይ ጠቅላላ ሁኔታው፣ ኩራቱና ትእቢቱ ደሜን ስላፈላው፣ ለትዕግስቴ ዳርቻ አይኖረውም ብዬ ለራሴ ቃል የገባሁት ሰውዬ ‹የራስህን ስቱፒድነት ተናገር እኛ ግን አንተን ወይም እናንተን አይደለንም›  ስለው አስተናጋጆቹ ተደናገጡ፡፡ ዚያድ ባሬ ያልኩትን ያልሰማኝ ይመስል ‹ምንድነው ያለው?› እያለ ሰዎቹን ሲጠይቅ አስተውለው ነበር፡፡ ›› (ገፅ 354)

የሰላም ድርድሩ ባለመሳካቱም ኮለኔሉና ጓዶቹ ሕዝባቸውን ከዳር ዳር ቀስቅሰውና አስታጥቀው፣ ከሶሻሊስት ሀገራት ጋር በመተባበር፡-

‹ማን ይፈራል ሞት

ማን ይፈራል

ለእናት ሀገር ሲባል!›ን እየዘመሩ ወራሪውን የሶማሊያ ወታደር የኢትዮጵያ ምድር ግዛቱ ሳይሆን፣ መቀበሪያው ማድረጋቸውን ታሪክ መዝግቦታል፡፡

ዛሬ ስለመንግስቱ ኃ/ማርያም እና ጓዶቹ አምባገነንት፣ ጨፍጫፊነት፣ ጦርነት ናፋቂነት… ካልሆነ በቀር ሀገራዊ አስተዋፅኦዋቸውን መናገሩ ያስቀስፋል፤ ምክንያቱም እነመንግስቱ ተራቸው ደርሶ ተሸንፈው ከስልጣናቸው ተባረዋል፤ ታሪክ ደግሞ ምንጊዜም ከአሸናፊ ጋር ትወግናለች፡፡

የሆነው ሆኖ መንግስቱ ኃ/ማርያም እንደ መለስ ዜናዊ ስልጣን ላይ እያለ ህይወቱ ቢያልፍ ኖሮ እነጓድ ለገሰ አስፋው ምን የሚያደርጉ ይመስላችኋል? …እልፍ አዕላፍት ‹ፓርክ› በስሙ ይሰይማሉ፤ በተማረበት ‹ሆለታ ገነት የጦር አካዳሚ› ግቢ ውስጥ በ20 ሚሊዮን ብር የምርምር ተቋም ይገነባሉ፤ ለሙት አመቱ መታሰቢያ በየዓመቱ ችግኝ መተከሉ ስለማይቀርም በርካታ ‹አማዞኖች› በስሙ ይኖሩታል፤ ‹ራዕዩ› የሚቀጥልበት ፋውንዴሽንም ይቋቋምለታል… ይህ ነው የጉልበተኞች የ‹ታሪክ› ትርጓሜ (አረዳድ)፤ አስገራሚው ጉዳይ ይህ ብቻ አይደለም፤ ሁሉም አምባገነን ተመሳሳይ መሆናቸው ነው፤ ራሱ መንግስቱ ኃ/ማርያም በዘመኑ የጃንሆይን ሀገራዊ አስተዋፅኦ ሊያወድስ ቀርቶ፣ ስማቸውንም እንኳ መስማት አይፈልግም ነበር፤ ተራው ደርሶ በተሸነፈ ጊዜም ያጨደው የዘራውን ይመስለኛል፤ ግና! ይህንን ባህል (ክፉ ልማድ) መቀየር አለብን፤ የአሜሪካኖቹ ‹የምስጋና ቀን› ምክንያትና ዓላማንም እንዲህ በሆንበት ክፉ ጊዜ በልባችን ብናስበው ምንኛ መልካም ይሆናል፡፡

በመጨረሻም በዚህ ፅሁፍ ለጠቀስኳቸው ሁነቶች ብቻና ብቻ ‹ቪቫ ደርግ፣ ቪቫ መንግስቱ› እላለሁ! ለዜጎች ጥቅም ዛሬም፣ ነገም ኢትዮጵያ ትቅደም!

መልካም አዲስ ዓመት!!

Posted on September 11, 2013, in Andinet, ETHIOPIA AMHARIC, Ginbot 7, OLF, oromo and tagged , . Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: