‹‹ጀርባ የሚልጡ›› ትናንቶች

ለቅሶ ቤት ቁጭ ብለው የሚጨዋወቱ ሰዎች በእጃቸው ካለው የመጫወቻ ካርድ (ካርታ) እኩል ትኩረት ያደረጉበት ርዕሰ ጉዳይ የአዲሱ ዓመት በዓል ገበያ ነበር…

ሽንኩርት በኪሎ 15 ብር መግባቱ የሚገርማቸው ብቻ አልነበሩም፤ ከአገር የጠፋው በሽተኛው ቲማቲም 25 ብር ላይ መተኮሱ ጭምር ለባለካርታዎቹ መነጋገርያቸው ነበር፡፡ ‹‹ለነገሩ አንድ ኪሎ የቲማቲም ዘር ሁለት ሺሕ ብር በገባበት በዚህ ወቅት፣ ገበሬ በስንት ብር ሊሸጥ እንደሚችል መገመት ይቻላል፤›› በማለት የፀረ አረም ኬሚካሎችንና የአትክልት ዘሮችን የምታከፋፍለው ወጣት፣ የዕድምተኛውን ልብ መለስ አደረገች፡፡

(የዓውድአመት ውሎና የገበያው ውድነት)

gebeyaw

ቲማቲም በበሽታ መመታቱ ብቻ ሳይሆን ለዘርም ለዘሪም መጥፋቱ ዋጋውን ሰማይ አድርሶታል ብለን ብንስማማም፣ የበዓሉን እግር ተከትለው የናሩ ምርቶች ግን የሚጋረፉ ናቸው፡፡ ‹‹የሐበሻ›› እንቁላል አንዷ ያውም የቄብ የምታህለው፣ ከሦስት ብር በላይ ናት፡፡ በዘነብወርቅ ገበያ ደህናው ዶሮ ከ200 ብር፣ ሥጋ አልባው 170 ብር እየተሸጡ የዋሉት ባለፈው ቅዳሜ ነበር፡፡ ሽንኩርት እርጥብና ደረቅ የሚል መለዮ ተሰጥቶታል፡፡ በዘንብወርቅ እርጥቡ በኪሎ አሥር ብር ሲሸጥ ነበር፡፡ ደረቁ 14 ብርና ከዚያም በላይ ያወጣል፡፡ የቅቤ ዋጋ እንደነገሩ በአማካይ  ከ130 እስከ 180 ብር ድረስ እንደሚገኝ ከሰፈር ገበያ እስከ ቅቤ በረንዳ ያየ ያውቀዋል፡፡

እነዚህ ምርቶች ወቅት ጠብቀው፣ በዓልን ተግነው ጣርያ መንካታቸው የተለመደ ነው፡፡ የገበያው መመርያም ይመስላል፡፡ ሁሉም ይሸምታል፡፡ ዋጋው ተወድዷልና የዘንድሮ በዓል ፌሽታው ይቅርብኝ የሚል የለም፤ ወይም አላጋጠመንም፡፡ ሁሉም ልጆቹንና ቤቱን ይለውጥ ዘንድ ደፋ ቀና ሲል፣ በአዲሱ ዓመት አዲስ ነገሮችን በቤቱ ያይ ዘንድ ሲያሳምርና ሲቀይር፣ ሲገዛና ሲያጋዛ ሰንብቷል፡፡

ለበዓሉ ከሚዘጋጁት ምግቦች ባሻገር ገበያው የያዘላቸው የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች መች ይቆጠራሉ፡፡ ሶፋ፣ አልጋ፣ ቴሌቪዥን፣ ምንጣፍ፣ ብፌ፣ የማድ ቤት ዕቃዎችና ማስቀመጫው፣ የቤት ክዳን ቆርቆሮ፣ ቀለም ወዘተ. ያሉት ዕቃዎች በመኪናም በእግረኛም ተጭነው ሲጋዙ ማየት የዓመት በዓል፣ ያውም የአዲስ ዓመት ብሥራት ነው፡፡

‹‹አዲስ ዓመት ጣጣው ብዙ ነው›› ያለው አስፋው አትርፌ (ስሙ ተቀይሯል) የተባለውና ፒያሳ አካባቢ የሚኖረው ባለትዳር ነው፡፡ የሚተዳደረው የበዓል ሰሞንን ጠብቆ ዋጋው በሚንረው አትክልትና ፍራፍሬ ችርቻሮ ነው፡፡ እሱን የሚያማርሩ ገበያተኞች እንደበዙ የሚገልጸው አስፋው፣ እሱም በተራው የሚያማርረው አለው፡፡ መንግሥት በግብር ጣጣ ቆሌውን እየገፈፈው መምጣቱን፣ ሥራውን ለመቀየር ቢችል ምኞቱ መሆኑን ይናገራል፡፡ ‹‹ብርቱካን ተወደደ ብሎ እኛ ላይ ከሚጮህ፣ ሌላ ሌላውንስ ቢያየው?›› ሲል ይጠይቃል፡፡ ‹‹መንግሥት፣ ትምህርት ቤት ለምን ጨመረ ይላል እንዴ? እስኪ ምን ተገኝቶ ነው በየጊዜው የወር ክፍያ የሚጨምሩት ይላል እንዴ? አይልም፡፡ ዞር ብሎ የሚያያቸው የለም፡፡ ሌላው እንደፈለገ ሲሆን እኛን ብቻ አንዴ በኪሎ፣ አንዴ በተከራይ ስቃያችን ለምን ያሳዩናል? ድሃ ሠርቶ በበላ መከራው ማየት አለበት?›› የአስፋው ቅሬታዎች ብዙ ናቸው፡፡ በተለይ መንግሥትን የሚኮንንበት ይበዛል፡፡ ወደ ነገራችን ስንለመስ አዲስ ዓመት በመጣ ቁጥር ምንም አዲስ ነገር ሳይጨምሩ የትምህርት ቤት ሒሳብ የሚቆልሉት የግል ትምህርት ቤቶች አንገብበውታል፡፡ ዓመት በመጣና በሄደ ቁጥር በወርሃዊና በመመዝገቢያ ክፍያ ላይ የሚደረገው ጭማሪ፣ ከመደበኛው ትምህርት ውጭ ለማስጠናት፣ ለመጻሕፍት፣ ለልዩ ልዩ ክፍያዎች (ጉብኝት ወዘተ ላሉት)፣ ለደንብ ልብስ የሚከፈለው ተደማምሮ እኔም ትምህርት ቤት በከፈትሁ ኑሮ አሰኝቶታል፡፡

በቅርቡ የብርቱካን ዋጋ እንደናረ መቅረቱ ‹‹ያሳሰበው›› ንግድ ሚኒስቴር፣ ቸርቻሪዎቹን ሰብስቦ ባስፈራራበት መድረክ ላይ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ሲራጅ አሊ የትምህርት ቤቶችን ዋጋ የገለጹበት አነጋገራቸው እዚህ ቢጠቀስ ነገሩን በጉልህ ለማስረዳት ይጠቅማል፡፡ ‹‹ከእንቅልፉ ሲነሳ ዛሬ ክፍያውን በእጥፍ መጨመር አለብኝ የሚል ሰው የበዛበት አገር ሆኗል፤›› ብለው ነበር፡፡

አቶ ሲራጅ ሕዝቡ ከሚሸከመው በላይ የኑሮ ውድነቱ አድቅቆት እያለ ባልተገባ ዋጋ ጀርባው ሲላጥ መንግሥታቸው ዝም ብሎ እንደማይተኛ ያስጠነቀቁት ከጥቂት ጊዜ በፊት፣ ከአትክልትና ፍራፍሬ ነጋዴዎች ጋር በተካሄደ ስብሰባ ነበር፡፡ እሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ ከቀን ቀን፣ ከሳምንት ሳምንት ዋጋ እየናረ፣ በወራት ጊዜ ውስጥ ከእጥፍ በላይ እየጨመረ ሕዝቡ መቸገሩ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

ለአብዛኛው ሰው የሚገርመው ደግሞ እዚሁ የተመረቱ ሸቀጦችና ቁሳቁሶች በዋጋ ሰማይ ጠቀስ መሆናቸው ነው፡፡ ከአዲስ አበባ በ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ክልል ውስጥ የተመረቱ ምርቶች፣ አዲስ አበባ ሲገቡ አራትም አምስትም እጥፍ መጨመራቸው ለአገሬው መንግሥት የታወቀ ነው፡፡ ንግድ ሚኒስቴር የብርቱካን ዋጋ ከአምስት ብር እስከ 25 ብር በሚደርስ ልዩነት መናሩን ያውቅ ስለነበር ነው ነጋዴዎቹን ሰብስቦ ያስጠነቀቀው፡፡ የብርቱካን መሸጫ ዋጋ እንዲቀንስ፣ ነጋዴውም ስንጥቅ ትርፍ ከማትረፍ እንዲቆጠብ ያስጠነቀቀበት ምክንያት ጥያቄ ቢፈጥርም (የላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱትስትሪን ሚድሮክ ከገዛው በኋላ መሆኑ) ዕርምጃው ግን ሌሎች ምርቶችን ሊመለከት ይገባው እንደነበር የሚኒስቴሩ ባለሥልጣናትም ያምናሉ፡፡ ‹‹ወደፊት እንመለከታቸዋለን፣ ለአሁኑ ግን ላይኛው አዋሽ አግሮ ኢንዱስትሪ ዋጋ ሲቀንስ ነጋዴዎቹ አለመቀነሳቸው ስለተደረሰበት ነው፤›› ማስጠንቀቂያው የተላለፈላቸው በማለት ምላሽ መስጠታቸው አይዘነጋም፡፡ ጤፍ በሸዋ ሀይፐር ማርኬት ተፈጭቶ የሚሸጥበት ዋጋና በወፍች ቤቶች ውስጥ ሳይበጠር፣ ሳይፈጭ ከሚሸጥበት ጋር ሲወዳደር፣ ኧረ በሕግ ያሰኛል፡፡ በቅርቡ በመገናኛ አካባቢ የተከፈተው ሸዋ ሀይፐር ማርኬት (ከሱፐር ማርኬት በላይ) ውስጥ አንድ ኪሎ የሁለተኛ ደረጃ የተፈጨ ጤፍ 17.50 ብር ነው፡፡ በመካኒሳ አካካቢ ከሚገኙ ወፍጮ ቤቶች ግን ያልተፈጨውን ጤፍ ከነዕብቁ በኪሎ 17 ብር ይሸጣሉ፡፡

የመንገድ ዳር ጯሂዎችና አስጯሂዎች

የተገማመሰው መንገድ አዲስ የንግድ ስልት ለአዲስ አበባ ካስተዋወቀ ሰነባብቷል፡፡ ሱቆቻቸው የፈረሱባቸው፣ በመንገድ ሥራ ምክንያት አጥር የጋረዳቸው፣ ከመንገድ ወዲያ ተቆርጠው የቀሩ ቡቲኮች አዲስ የሽያጭ ስልት ቀርፀው፣ ልብስና ጫማ በቅናሽ ዋጋ መሸጥ የጀመሩ ይመስላሉ፡፡

ባለቡቲኮቹ ቀን ቀን አልሸጥ ብሎ ሲገላምጡት የሚውሉትን ጫማና ልብስ፣ ሲመሻሽ ለመንገድ ዳር ጯሂዎች ያስረክቧቸዋል፡፡ 500 ብር ይሸጡት የነበረውን ሱሪ፣ በ200 ብር ሽጥልኝ ብለው ቀን ለወጣለት አንጣፊ ይሰጡታል፡፡ አጅሬም “ከቡቲክ የወጣ፣ አዲስ ዕቃ መጣ” እያለ ጩኸቱን ያዘራዋል፡፡ በላስቲክ ንጣፉ ላይ ከደረደራቸው ልብስና ጫማዎች አማርጦ ለመግዛት የደፈረ በዋጋ ክርክር ይገጥማል፡፡ ዕቃውም በቡቲክ ዋጋ ሳይሆን በመንገድ ዋጋ ተሽጦ ያድራል፡፡ ይሄን ለማየት ሜክሲኮ፣ መርካቶ፣ መገናኛ አካካቢ ጎራ ማለት ይበቃል፡፡

አልሸጥ ብሎ ቡቲክ ያጣበበውን ጫማና ልብስ፣ ለጯሂዎቹ ባለውለታዎች ገለጻ ይድረሳቸውና ደርዘኑን አራግፈውት ያድራሉ፡፡ የአገሪቱ የንግድ ሥርዓት ነፀብራቅ የሆኑ በርካታ ጊዜ ወለድ ክስተቶችን ስናስተናግድ ቆይተናል፡፡ ወቅት ተጠብቆ፣ ሸማች ምርጫ ስለሌለው ብቻ ‹‹ከፈለግክ ግዛ ካልፈለክ…›› እየተባለ የሚገዛበት ሥርዓት ዛሬም፣ የሸማቾች ጥበቃና የንግድ አሠራር ባለሥልጣን ተቋም በተፈጠረበት ዘመንም የቀጠለ ሥርዓት ነው፡፡ አዲስ አበባ የሚዛንና የልኬት ማጭበርበርን፣ በሌላ ለማጨበርበር በማይመች ሚዛን ሳትተካ የቆየች ከተማ ናት፡፡ ያንኑ ሚዛን ልክ ነው ብሎ የሚያረጋግጥ መሥርያ ቤት ዕድሜ የሚቆጥርባት ናት፡፡ አሁን ያለው የሽቦ ሚዛን ሻጭና ገዥን ካላስማማ ዲጂታል የሚባለውን ሚዛን አምጥቶ ያንን ከአገር ማባረር እየተቻለ፣ ዓመት መጥቶ በሄደ ቁጥር ነጋዴን ሌባ እያሉ መወንጀል የመንግሥት ከአፍንጫ አርቆ አለማየት ይሆን? የሚል ወቀሳ ያስነሳል፡፡ በአንዳንድ ሱፐር ማርኬቶችና በኢትፍሩት መደብሮች የሚታዩትን ዲጂታል ሚዛኖች በልኳንዳና በአትክልት ቤቶች ማስፋፋት አይቻልም ወይ? ለእነሱ የሚመጥን ማምጣት እንዲችሉ ማድረግ ሳይቻል ቀርቶ አይመስለኝም፡፡ ይህንን ሥራ የሚቆጣጠረው ንግድ ሚኒስቴር ይሄ እውነት ሳይገለጥለት አዲስ ዓመት ሲጠባ ስንት ጊዜው ነው? (ሪፖርተር፤ ብርሃኑ ፈቃደ)

Advertisements

Posted on September 11, 2013, in Andinet, ETHIOPIA AMHARIC, Ginbot 7, OLF, oromo and tagged , . Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: