‹‹ይኼ ግብፅ ነው እኛም ግብፃውያን ነን እናንተ ሰዎች [ኢትዮጵያዊያንም] ለቀቅ አድርጉን›› ግብፃዊው ዶ/ር ሃኒ ኢልሻላከሚ

‹‹ትንሽ ስሜታዊ ሆኜ እንደሆነ በጣም ይቅርታ፡፡ ዓለም በመላ የእኛ ፀር ሆኖ ይታየኛል፤ ለምን እንደሆነ አይገባኝም፤›› በስሜት ያደረጉት ሰፊ ንግግራቸው መቋጫ ነው….ለምንድን ነው ወታደራዊ መንግሥት የምትሉት? ለምንድን ነው ወታደራዊ ብላችሁ የምትጠሩት? ከ39 ሚኒስትሮች መካከል አንድ ብቻ ነው ወታደራዊ መኮንን፡፡ መከላከያ ሚኒስትሩ የእኛ ፀር ለመሆኑ ለምን እውነቶችን ታጣምማላችሁ?›› ቀጠሉ፡፡

‹‹ይኼ ግብፅ ነው እኛም ግብፃውያን ነን እናንተ ሰዎች [ኢትዮጵያዊያንም] ለቀቅ አድርጉን››  ግብፃዊው ዶ/ር ሃኒ ኢልሻላከሚ

ዶ/ር ሃኒ ኢልሻላከሚ ይባላሉ፡፡ ግብፃዊው ናቸው፡፡ በዕድሜም በትምህርትም የገፉ ናቸው፡፡ ስሜታዊ ከመሆናቸው ውጪ የተናገሩትን እንግሊዝኛ ለሚያዳምጥ የሌሎች ሰዎችን እንግሊዝኛ በትክክል መረዳት የሚያቅታቸው አይመስሉም፡፡ አስተያየታቸውን የተናገሩት አንድ ኢትዮጵያዊ ምሁር በሰጡት አስተያየት ላይ ተነስተው ቢሆንም፣ እንዲህ የሚያስቆጣ ወይም አሻሚ ትርጉም የነበረው አይደለም፡፡ ሕይወታቸውን በሙሉ በግብፅ የኖሩ ሜዲካል ዶክተር ናቸው፡፡ በግብፅ ሦስት መንግሥታትን አሳልፈዋል፡፡ የመንግሥት አካል አለመሆናቸውንም ይናገራሉ፡፡

‹‹ነገር ግን ግብፃዊ ነኝ፡፡ በአገሬ ጉዳይ ያገባኛል፡፡ ይቅርታ ይኼ ግብፅ ነው፡፡ እኛም ግብፃዊያን ነን፡፡ አገራችንን ወደምንፈልገው አቅጣጫ እንድንመራ ሊፈቀድልን ይገባል፡፡ በውስጥ ጉዳያችን ለምን ትገባላችሁ? ለምንድን ነው እውነትን የምታጣምሙት? ወታደራዊ መንግሥት የምትሉት የትኛው ነው? ሥልጣን ላይ ያለው የሲቪል መንግሥት ነው፡፡ ወታደራዊ መንግሥት አይደለም፡፡ እጅግ በጣም ይቅርታ፡፡ ዓለም በመላ የእኛ ፀር እየሆነ ስለመሰለኝ ነው፡፡ ለምን እንደሆነ ባላውቅም፡፡››

‹‹አልጄዚራ የሚላችሁን አትስሙ››

የግብፃዊው በስሜት የተሞላ ንግግር ታዳሚዎችን ያስደነገጠ ነበር፡፡ ከእሳቸው በፊት ከኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞች በተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ላይ ምላሽ የሰጡ ሌላ ግብፃዊው ዲፕሎማት፣ እዚህ ኢትዮጵያ ሦስት ቀናት አሳልፈዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሚዲያ ስለግብፅ የሚዘግበው የተጣመመና የተሳሳተ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹አልጄዚራ የሚነግራችሁን አትስሙ፡፡ የተጣመመ ነገርም አትጻፉ፡፡ ግብፅ በአሁኑ ወቅት እናንተ እንደምታስቡት ቀውስ ውስጥ አይደለችም፡፡ ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሰው ልጆች ምቹ ሆናለች፡፡ አሁን የማወራው በሕይወት ታሪኬ የሚሰፍር ነው፡፡ ግብፅ በአሁኑ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ ሰላም የሰፈነባት ነች፡፡ ለቢዝነስም ምቹ ነች፤›› ያሉትን ነበር ቀጠል አድርገው የተናገሩት፡፡

በኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞችም ሆነ በፕሮፌሰር ፍስሐ ፅዮን መንግሥቱ የተነሱ ጥያቄዎች ግልጽና ብዙም ለትርጉም አሻሚነት የተጋለጡ አልነበሩም፡፡ ለግብፅ ሕዝብ ዲሞክራሲ ምን ማለት ነው? የሕዝብ ፍላጎትና ድምፅ የሚገለጸው በኮሮጆ ወይስ በጎዳና ላይ ነውጥ (Mob) ነው? ከመፈንቅለ መንግሥት በኋላ ግብፅ ውስጥ ብዙ ሰው እየሞተ ነው፡፡ ወታደራዊ መንግሥት እየሄደበት ያለው መንገድ የአፍሪካ ኅብረት ውሳኔን የሚያከብር ነው? የሚሉ የፕሮፌሰሩ ጥያቄዎች ግን ግብፃዊያኑን ሳያበሳጫቸው አልቀረም፡፡

በተለይ ዶ/ር ሃኒ ኢልሻላከሚ ዓለምንም የኢትዮጵያ ሕዝብንም፣ ‹‹እባካችሁ ለቀቅ አድርጉን፣ ይኼ ግብፅ ነው፤ እኛም ግብፃዊያን ነን፡፡ የራሳችንን ዕጣ ፈንታ ራሳችን እንወስን፡፡ ጣልቃ አትግቡብን፡፡ የማንንም ጣልቃ ገብነት አንሻም፤›› ያሉበትን ምክንያት አብራርተዋል፡፡ ቀጥለውም በግብፅ የተካሄደው ለዓለም ተምሳሌት የሆነው ሕዝባዊ አብዮት እንዴት ‹‹ነውጥ›› (Mob) ብለው አሳንሰው ይጠሩታል? ይህ እውነታን ማጣመም ነው፤›› ማለታቸው በፕሮፌሰሩ ጥያቄና አስተያየት ላይ ብስጭታቸውን ለመግለጽ ነበር፡፡

የዶክተሩ ብስጭት ግን ከፕሮፌሰሩና ከጋዜጠኞች ጥያቄ ብቻ የተነሳ ነው ማለት ይከብዳል፡፡ ብዙዎች ኢትዮጵያዊያን በግብፃዊያን ሚዲያዎችና ፖለቲከኞች ላይ ሁሌም ጥርጣሬ አላቸው፡፡ በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው አቋምም እጅግ አሉታዊና የተጣመመ ነው የሚል ነው፡፡ ግብፃዊያን ልሂቃን በበኩላቸው ተመሳሳይ እምነት ያላቸው ይመስላል፡፡

ኢትዮጵያ የዓባይን ወንዝ ተጠቅማ እንዳትለማና የወንዙ መጠን እንዳይቀንስባቸው፣ ሁሌም በፀረ ኢትዮጵያዊነት ይንቀሳቀሳሉ የሚል እምነት አለ፡፡ የኤርትራ መገንጠልን ጨምሮ በኢትዮጵያ የሚከሰቱ የሽብር ጦርነቶችና ጥቃቶችም ከጀርባቸው ግብፃዊያን አሉበት የሚል ሥር የሰደደ እምነት አለ፡፡

በተለይ በዓባይ ወንዝ ላይ እየተሠራ ያለው የህዳሴ ግድብ ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ሚዲያዎቻቸውና ፖለቲከኞቹ በኢትዮጵያ ላይ አሉታዊ ሪፖርቶች እያሠራጩ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በመንግሥታቱ መካከል ሞቅና ቀዝቀዝ የሚል ግንኙነት ቢኖርም፣ ግብፃዊያን ላለፉት ሦስት ዓመታት የቆየውን ውስጣዊ የፖለቲካ ቀውሳቸውን ወደ ኢትዮጵያ ለማስቀየስ አልሞከሩም አይባልም፡፡ ይህ በተደጋጋሚ የተሞከረ ጉዳይ ቢሆንም፣ ለውጥ ፈላጊ የግብፅ አብዮተኞች ግን ጥያቄያቸው በዚህ የሚቀለበስ አይመስልም፡፡ የዲሞክራሲና የነፃነት ጥያቄያቸውን ሲያስቀድሙ ተስተውሏል፡፡ ባለፈው ዓርብ ግብፅ የዛሬ 40 ዓመት በእስራኤል ላይ የፈጸመችውን ‹‹ኦክቶበር 6›› ጥቃት የሚዘክር በዓል ምክንያት በማድረግ፣ በአዲስ አበባ የግበፅ ኤምባሲ በነበረው መድረክ ግን ግብፃዊያን በኢትዮጵያ ላይ ያላቸው ቅሬታና ግንዛቤ ኢትዮጵያዊያን ያላቸውን ያህል መሆኑ ተስተውሏል፡፡

ምላሹ ወይስ ጥያቄው ነበር የተጣመመው?

በዚህ መድረክ ዶ/ር ሃኒን ጨምሮ ግብፃዊያኑ ዲፕሎማቶች ወይም ግብፃዊያን ዜጎች የሰጡዋቸው አስተያየቶች፣ ኢትዮጵያዊያን በግብፅ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡብን ነው የሚል መልዕክት ያዘለ ይመስላል፡፡ ‹‹ለቀቅ አድርጉን›› ማለታቸው፡፡

በዚሁ የዓረብ ፊቶች የሚበዙበት የምሽት ፕሮግራም ከተገኙ ታዳሚዎች መካከል ጥቂት ኢትዮጵያዊያን ነበሩበት፡፡ ከኢትዮጵያዊያኑ ብዙዎች ጋዜጠኞች ናቸው፡፡ አምባሳደሩ በዚሁ ‹‹ግልፅና ነፃ ውይይት የሚደረግበት›› ባሉት መድረክ በመክፈቻ ንግግራቸው አንዳንድ ወሳኝ ነጥቦች ጠቃቅሰው ነበር፡፡ ባለፉት ሦስት ዓመታት በግብፅ የተከሰተው አገሪቱ ከተፈጠረች ጊዜ ጀምሮ ታይቶ የማይታወቅ እንደሆነ በመግለጽ፣ ‹‹እኛ የሞተ ፕሬዚዳንት እንጂ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ብለን አናውቅም፡፡ አሁን ግን በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ሁለት የቀድሞ ፕሬዚዳንቶች እያልን የምንጠራቸው አሉን፡፡ በሦስት ዓመታት ውስጥ ሁለት ዓበይት ሕዝባዊ አብዮቶች አስተናግደናል፤›› ብለዋል፡፡ አሁን ግብፅ ውስጥ የተሻለ ሁኔታ መኖሩን በመጠቆም፡፡

በመድረኩ የተዋወቁት የግብፅ የመጀመርያዋ ሴት ሚኒስትር (የጤናና የሥነ ሕዝብ ሚኒስትር ሚስስ ማሐ ኢልራባት)  በወቅታዊ የአገራቸው ሁኔታ ላይ ተጨማሪ ማብራርያ ከሰጡ በኋላ የግብፅን አብዮት የሚያሳይ አንድ ዘጋቢ ፊልም ቀርቦ ነበር፡፡ በፊልሙ ውስጥ ሁለት መሠረታዊ አነጋጋሪ ጉዳዮች ተነስተዋል፡፡

አንደኛው በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ሥልጣን ላይ ወጥተው ከአንድ ዓመት በኋላ ባለፈው ሐምሌ ወር የተወገዱት መሐመድ ሙርሲ ላይ የተጠነሰሰው መፈንቅለ መንግሥት ‹‹ወታደራዊ›› ግልበጣ አለመሆኑን ለማሳየት ያለመ ነበር፡፡ እንዲሁም ደግሞ ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲና ፓርቲያቸው ሙስሊም ወንድማማቾች በተሳሳተ አቅጣጫ መጓዙ ሃይማኖትንና ፖለቲካን ቀላቅሎ አገሪቱ ወዳልተፈለገ አቅጣጫ መውሰዱን ያሳያል፡፡ ሁለተኛው በኢትዮጵያ ላይ ጠንካራ አቋም አለመውሰድና የህዳሴ ግድቡን ማስቆም አለመቻሉ የግብፅን ፍላጎት ያላስጠበቀ መንግሥት መሆኑን የሚያሰርፅ ዘጋቢ ፊልም ይመስላል፡፡ በዚህም የግብፅ ብሔራዊ ደኅንነት በሁለት መሠረታዊ ነገሮች ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ እነሱም የሲናይና የኢትዮጵያ ጉዳይ መሆናቸው ከፊልሙ መገንዘብ ይቻላል፡፡ እነዚህ ደግሞ በሙርሲ ወቅት ሁለቱም በአግባቡ አልተያዙም የሚል መልዕክት አስተላልፏል፡፡

የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ጥያቄዎችም በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ነበር፡፡ ‹‹ስለዚህ አሁን ያለው መንግሥት በዓባይ ግድብ ላይ ያለው አቋም ምንድን ነው?›› የሚልና ከሙስሊም ወንድማማቾች ፓርቲ ጋር ዕርቅ የመፍጠር ፍላጎት እንዳለ የሚመለከቱ ጥያቄዎች ተንፀባርቀዋል፡፡ ለዚህም ነበር ስማቸው ያልተገለጸው አንድ ዲፕሎማት፣ ‹‹የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በግብፅ ላይ የሚያንፀባርቁት አስተያየት የተጣመመ ነው፤›› በሚል የተጀመረው ክርክር በዶ/ር ሃኒ ኢልሻላከሚ ‹‹እባካችሁ ለቀቅ አድርጉን›› በሚል ቁጭት አዘል ምላሽ የተቋጨው፡፡

‹‹ግብፅ አንድም አገር ወራ አታውቅም››

ዶ/ር ሃኒ፣ ‹‹ግብፅ አገሬ ነው፡፡ የሰባት ሺሕ ዓመት የሥልጣኔ ታሪክ ያላት አገር፤ ነገር ግን አንድም ቀን ሌላ አገር የወረረችበት አጋጣሚ የለም፡፡ ላለፉት ሁለት ዓመታት በተደረጉ ሰላማዊ ሠልፎችም አንድም ድንጋይ አልተወረወረም፡፡ አሁን ምን እየሆነ እንደሆነ ተመልከቱ፡፡ በሲናይና በሌሎች አካባቢዎች የአገር መከታ የሆኑት የመከላከያ ኃይሎችና ፖሊሶች እየተገደሉ ነው፡፡ ይህንን እያደረጉ ያሉት የሙስሉም ወንድማማቾች ናቸው፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤተ ክርስቲያናት ተቃጥለዋል፡፡ ብዙ ሰዎች ተገድለዋል፡፡ ያንን ማስቆም አለብን ወይስ ዝም ብላችሁ ተመልከቱ ነው የምትሉን?›› አሉ አሁንም በስሜትና በቁጭት በተሞላበት ሁኔታ፡፡ ግብፅ ኦክቶበር 6 ቀን 2013 ብሔራዊ በዓሏን ስታከብርም፣ በአንዳንድ ባሥልጣናት ላይ የግድያ ሙከራ የተደረገ ሲሆን፣ በተለያዩ አካባቢዎች በተከሰተው ግጭት ከ50 በላይ ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል፡፡ ይኼ ደግሞ ዲፕሎማቶቹ ስለግብፅ ወቅታዊ ሁኔታ ከገለጹት በተቃራኒ ነው፡፡

የእንግሊዝ ቅኝ ግዛት የነበረችው ግብፅ ከአንድም ሦስቴ በአፄ ዮሐንስ ዘመነ መንግሥት ኢትየጵያ ላይ ወረራ ፈጽማ የተሸነፈች ቢሆንም፣ ዶ/ሩ ግን ‹‹ኃይሏ የላቀ ከፍታ ላይ በነበረበት ወቅትም በማንም አገር ላይ ወረራ ፈጽማ አታውቅም፡፡ ሰላማዊ ሕዝቦች ነን፡፡ እባካችሁ የእኛ ፀር አትሁኑ፡፡ እውነታዎችን አታጣምሙ፤›› ሲሉ ስሞታቸውን አሰምተዋል፡፡ ‹‹ዓለምንና እናንተን የምማፀነው እኛ ለራሳችን ጉዳይ ራሳችን አለን፡፡ የምንፈልገው እንድትተውን ነው፤›› ብለዋል፡፡

ፕሮፌሰር ፍስሐ ፅዮን መንግሥቱ ግብፃውያኑ ዲፕሎማቶች አስተያየታቸውን በተዛባ መንገድ እንደተረዱዋቸው መልሰው ሲናገሩ፣ ‹‹አልተረዳችሁኝም እንጂ የግብፅ ሕዝብ ስኬት የኢትዮጵያ ሕዝብ ስኬት ነው፡፡ የግብፅ ሕዝብ ውድቀት ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ውድቀት ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሐሳባቸውን ለተዛባ ግንዛቤ መጋለጡን አስቀድመው ይቅርታ በመጠየቅ፡፡

ከግብፅ አምባሳደር መሐመድ ኢድሪስና ከሚኒስትሯ ዶ/ር ማሐ ውጪ አስተያየት የሰጡ አብዛኞቹ ግብፃዊያን ስሜታዊነት የተሞላበት ሲሆን፣ አንዳንዶችን የሚያስደነግጥ ነበር፡፡ በዚሁ መድረክ የኢትዮጵያ ዲፕሎማቶች አልተገኙም፡፡ አንዳንድ ታዳሚዎችም የዶ/ሩ ወሬ አልጥም ብሏቸው ይሁን በራሳቸው ጉዳይ፣ መድረኩን ከመጠናቀቁ በፊት አቋርጠው ሲወጡ ተስተውለዋል፡፡

በዚህ አብዛኞቹ ግብፃዊያን ‹‹ግብፅ ነገ ሰላም ትሆናለች፤ መልካም አቅጣጫ ላይ ነች፤›› ዓይነት ቁጭት የተሞላበት ንግግር ሲያደርጉ፣ ዓባይን በተመለከተ በግልጽ አስተያየት አልሰጡም ነበር፡፡ አምባሳደር መሐመድ ኢድሪስ ግን ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ በመጨረሻ ማጠቃለያቸው ምላሽ ሲሰጡ፣ የግብፅ መንግሥት አቋም አሁንም ‹‹ዊን ዊን›› ላይ የተመሠረተና ሁለቱንም አገሮች የማይጎዳ ትብብር ማድረግ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የዓባይ ግድብና የኢትዮጵያ እንቅስቃሴ ግብፅ ውስጥ ላለው የፖለቲካ ቀውስና በፕሬዚዳንት ሙርሲ ላይ ለተደረገው ‹‹መፈንቅለ መንግሥት›› ምክንያት ሆኖ እንደሆነ ተጠይቀው፣ ‹‹የግብፅ ቀውስ በውስጥ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ምክንያት የመጣ ነው፤›› በማለት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

Advertisements

Posted on October 9, 2013, in Andinet, Andinet party, ETHIOPIA AMHARIC, Ginbot 7, OLF. Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out / Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out / Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out / Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out / Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: