የሞኝ ዘፈን አሁንም አሁንም አበብዬ

ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎች ከዚህ ቀደም በቁንጯቸዉ በመለስ ዜናዊ በኩል እንኮረኩማለን፤ ምላስ እንቆርጣልን ወይም እጅ እናስራለን እያሉ ለኢትዮጵያ ህዝብ ያስተላልፉ የነበረዉን የማስፈራሪያ ቃላት ጋጋታ ባለፈዉ ዐርብ መስከረም 26 ቀን ለዚሁ እኩይ ተግባራቸዉ በቀጠሩት ታማኝ ሎሌያቸዉ በኃ/ማሪያም ደሳለኝ በኩል ሲያስተላልፉ ተደምጠዋል..

379902_189182111178517_478402269_n

እንዳሰለጠኑት ጌኛ ፈረስ ወያኔ ባሳየዉ አቅጣጫ ሽምጥ የሚጋልበዉና ከጭንቅላቱ ወጥቶ የሚነገር ምንም ነገር የሌለዉ ኃ/ማሪያም ደሳለኝም የአሜሪካዉን ፕሬዚዳንት የባራክ ኦባማን አባባል እንዳለ በግርድፉ ወስዶ “ከቀይ መስመር በላይ መሄድ የሚፈልግ ይቆነጠጣል” ሲል በዚያ ባልተቆነጠጠ አፉ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ደንፍቷል። የወያኔዉ ተላላኪ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ አልገባዉም እንጂ ይህ ቀይ መስመር ታልፉና ወዮላችሁ የሚሉት ዛቻ አንኳን በአንድ ጀምበር ትርምስምሱ ሊወጣ በሚችል የጦር ኃይል ለሚተማመነዉ ወያኔን ለመሰለ ፀረ ህዝብ ኃይል ቀርቶ በህዝብ ሙሉ ፈቃድ የተመረጠዉና የአለማችንን አስፈሪና እጅግ ጠንካራ ጦር የሚመራዉ ባራክ ኦባም ከተናገረና ከዛተ በኋላ ዛቻዉ አላዋጣ ስላለዉ ሌሎች አማራጮችን ለመመልከት ተገድዷል።

ባለፈዉ ዐርብ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ የተናገራቸዉን ተራ ንግግሮች ሁሉ እንመልከት ብንል እንደሱ ስራ ፈቶች አይደለንምና ግዜዉም ፍላጎቱም የለንም፤ ሆኖም አንዳንድ ንግግሮቹ የኢትዮጵያ ህዝብ ለመብቱና ለነጻነቱ የሚያደርገዉን ትግል በንቀት አይን የተመለከቱ ናቸዉና ግንቦት 7 የሚያካሄደዉ የነጻነት ትግል ኃ/ማሪያም ደሳለኝን ከወያኔ ባርነት ነጻ ማዉጣትንም ያጠቃልላልና ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ይህንን ምክር አዘል መልዕክታችንን እንዲያዳምጥ እንጋብዘዋለን። ደግሞም የግንቦት ሰባትን እንቅስቃሴ እከታተላለሁ ብሎ ሲናገር ከራሱ አንደበት ሰምተናልና ምክራችንን ይሰማል የሚል ሙሉ እምነት አለን።

ኃ/ማሪያም ደሳለኝ አገር ዉስጥ የሚገኙ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያነሷቸዉን ጥያቄዎች አስመልክቶ ከጋዜጠኞች የቀረበለትን ጥያቄ ሲመልስ ኢትዮጰያ ዉስጥ ወደ ዘጠና የሚጠጉ ፓርቲዎች ስላሉ ዘጠና እሁዶችን መጠበቅ አለብን በማለት ከተጠየቀዉ ጥያቄ ጋር በፍጹም የማይገናኝና እንኳን ከአገር መሪ ከሦስተኛ ክፍል ተማሪም የማይጠበቅ ተራ መልስ መልሷል። ከዚህ በተጨማሪ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እሁድ እሁድ በሚያደርጓቸው ሰላማዊ ሠልፎች የሚያቀርቡት ጥያቄ ተመሳሳይ ስለሆነ መንግሥት ምን ምላሽ መስጠት እንዳለበት ሊገባው አልቻለም በማለት ኃ/ማሪያም የእሱን የራሱን ብቻ ሳይሆን እሱ የሚመራዉ መንግስትም ምን ያክል ጨቅላ መንግስት አንደሆነ በግልጽ ተናግሯል። የኃ/ማሪያምና የጌቶቹ ጨቅላነትና ባዶነት ደግሞ አገር ያወቀዉና ፀሐይ የሞቀዉ እዉነት ነዉና ብዙ መረጃ የሚያስፈልገዉ አይመሰለንም።ከሰሞኑ አማካሪ ተብለዉ ኃ/ማሪያምን የከበቡትን ሰዎች መመልከቱ ይበቃል። የጭንቅላቱ ዝገት ለይቶለት በመለስ ዜናዊ ግዜ ስኳር እንዲቅም መተኃራና ወንጂ የተላከዉ አባይ ፀሐዬ እሱ እራሱ ይመረመር እንደሆነ ነዉ እንጂ አባይ ፀሐዬ እንኳን ለፖሊሲ ምርምር የተመራማሪዎችን ዶሴ ለመሸከም የማይበቃ ሰዉ ነዉ . . . ችግሩ “ግም ለግም አብረህ አዝግም” ነዉና ከምሁርና ከአዋቂ ጋር የተጣሉት የወያኔ መሪዎች አንዱን ጅል የሌላዉ ጅል አማካሪ እያደረጉ የፈረደባትን አራት ኪሎን የጅሎች መንደር አደረጓት።

ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ባለፈዉ ዐርብ ከአንድ ሰዐት በላይ በፈጀዉ ጋዜጣዊ መግለጫዉ ወቅት የተናገረዉ አንድ ብቸኛ እዉነት ቢኖር “መንግስት ተቃዋሚዎች ለሚያቀርቡት ጥያቄ ምን አይነት ምላሽ መስጠት እንዳለበት ሊገባዉ አልቻለም ብሎ የተናገረዉ ንግግር ብቻ ነዉ። አዎ በተራ የመንገድ ላይ ፖለቲከኞችና ዘራፊዎች የሚመራዉ የወያኔ /ኢህአዴግ አገዛዝ ከኢትዮጵያ ህዝብ የሚቀርብለትን የመብትና የነጻነት ጥያቄ ቀርቶ በአገዛዙ በራሱ መሃል የሚነሱ ጥያቄዎችን በቅጡ ተረድቶ የመወያየት ብቃትም ችሎታም ያለዉ አገዛዝ አይደለም። ኃ/ማሪያም ደሳለኝ በአንድ በኩል ተቃዋሚ ፓርቲዎች ለህዝብ ማለት የፈለጉትን ብለዋል፤ ህዝብም በሚገባ ሰምቷቸዋል በማለት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ተቃዋሚዎች ለጠየቁት ጥያቄ መንግስት ተገቢዉን ምላሽ ሰጥቷል አሁን እየጠየቁ ያሉት ተመሳሳይ ጥያቄ ነዉ በማለት እሱም ሆነ ፈላጭ ቆራጩ የወያኔ አገዛዝ እንመራለን የሚሉትን ህዝብ የፖለቲካ ምጥቀት በፍጹም የማይመጥኑና ቀድሟቸዉ የሄደዉን ህዝብ ከኋላ ሆነዉ የሚመሩ ኋላ ቀሮች መሆናቸዉን በግልጽ አሳይቷል። ኃ/ማሪያም በሰላማዊ ሰልፍና በህዝብ መካከል ያለዉ አንድነትና ልዩነት የገባዉ ሰዉ አይመስልም፤ ለዚህ ነዉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያቀረቡት ጥያቄ ለህዝቡ መስሎት ህዝብ ሰምቷቸዋል ብሎ የተናገረዉ፡፡

ኃ/ማሪያም እንደሚለዉ መንግስት የህዝብን ጥያቄ መልሶ ቢሆን ኖሮ ኢትዮጵያ ከዘረኞች ተላቅቃ ፍትህና ዲሞክራሲ የሰፈነባት አገር ትሆን ነበር፤ ወይም ኃ/ማሪያም እራሱ የሞተ ሰዉ ራዕይ መሸከሙን አቁሞ የራሱ ጭንቅላት ያመነጨዉንና በራሱ እይታ ያየዉን ራዕይ ያጋራን ነበር። ተቃዋሚ ፓርቲዎች በተደጋጋሚ ፍትህ፤ ነጻነት፤ እኩልነትና ዲሞክራሲ እያሉ የሚጮሁት እነዚህ ጥያቄዎች ካልተመለሱ በሚወክሉት ህዝብና በአገራቸዉ በኢትዮጵያ ላይ ሊደርስ የሚችለዉን መጠነ ሰፊ ችግር ከወዲሁ ስለሚታያቸዉ ነዉ። እርግጠኞች ነን፤ ኃ/ማሪያም ደሳለኝም እንደ ተቃዋሚዎች አገሩን የሚወድ ኢትዮጵያዊ ነዉና ዘረኞች ያጠለቁለትን ማስክ አዉልቆ በራሱ አይን ማየት ሲጀምር እሱም እንደ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ከተቃዋሚዎች ጋር ተሰልፎ ለነጻነቱ መጮህ ይምራል ብለን እናምናለን።

በእርግጥ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ከፖለቲካ ብስለቱና ካለዉ ልምድ አኳያ ሲታይ ብዙዎቹ አገር የመምራት ዉስብስብ ነገሮች ላይገቡት ይችሉ ይሆናል፤ ሆኖም ግን የአገርና የመንግስት መሪ ነኝ የሚል ሰዉ ህዝብ ላቀረበለት ጥያቄ ምን አይነት ምላሽ መስጠት እንዳለብን ሊገባን አልቻለም ማለቱ የሚያሳየን አገራችን ኢትዮጵያ የምትመራዉ ለዕድር ዳኝነትም በማንመኛቸዉ ባዶ ሰዎች መሆኑን ነዉ። በተለይ 99.6% የህዝብ ድምጽ አገኘሁ ብሎ የሚመጻደቅ መንግስት የዚሁኑ መረጠኝ የሚለዉን ህዝብ ጥያቄ እንዴት መመለስ እንደሚገባዉ ካላወቀ ሌላ ምን ሊያዉቅ ይችላል!

ኢትዮጵያ ከ90 ሚሊዮን በላይ ህዝብ የሚኖርባት ትልቅ አገር ናት፤ በእርግጥ 90 ሚሊዮን ህዝብ የሚጠይቀዉን ጥያቄ ማስተናገድ ለማንም አገር መንግስት አዳጋች ሊሆን ይችላል ፤ ነገር ግን መልስ የለንም ወይም ጥያቄዉ አልገባንም እየተባለ የህዝብ ጥያቄ ቆሻሻ ቅርጫት ዉስጥ አይጣልም ። በእርግጥ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ በጠ/ሚኒስቴርነቱ ጥርስ የለሌዉ አንበሳ ነዉና የህዝብን ጥያቄ መመለስ አይችል ይሆናል፤ ሆኖም ኃ/ማሪያምን በቅርብ የሚያዉቁት ሰዎች ሐይማኖታዊ ስነምግባሩንና አንደበተ ጨዋነቱን ተመልክተዉ ሌላ ሁሉ ቢቀር በእነዚህ ሁለት ባህሪይዎቹ ብቻ የተቀመጠበትን ወንበር ይመጥናል ብለዉ ገምተዉ ነበር። ችግሩ “ከአህያ ጋር የዋለች ጊደር ፈስ ተምራ ትመጣለች” ነዉና ዛሬ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ አንደ ገለባ ቀልሎ የሚታየዉ በዚሁ በተነገረለት ጠንካራ ጎኑ በኩል ነዉ። ለመሆኑ መቼ ነዉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እትዮጵያ ዉስጥ በየእሁዱ ሰላማዊ ሰልፍ ያደረጉት? ደግሞስ የወያኔ አገዛዝ ሰላማዊ ሰልፍ በተጠራ ቁጥር የሰላማዊ ሰልፉን አስተባባሪዎችና ሰልፈኛዉን የሚደበድብ ኃይል ነዉ የሚያሰማራዉ እንጂ ከመቼ ወዲህ ነዉ ወያኔ ለህዝብ ደህንነት አስቦ የጥበቃ ኃይል አሰማርቶ የሚያዉቀዉ? ካለፈዉ ግንቦት ወር ጀምሮ ሰማያዊ ፓርቲና አንድነት ፓርቲ አዲስ አበባ ዉስጥ የጠሩት ሰላማዊ ሰልፍ ሦስት ወይም አራት ቢሆን ነዉ፤ በዚህ ግዜ ዉስጥ ደግሞ ማንን እንደሚቃወም ባይታወቅም ገዢዉ ፓርቲም ሰላማዊ ሰልፍ አድርጓል። ታድያ የቱን ሰላማዊ ሰልፍ ነዉ ኃ/ማሪያም በየሳምንቱ የሚደረገዉ ሰላማዊ ሰልፍ ሰለቸን ብሎ የተናገረዉ? ወይስ የጌታዉን የመለስ ዜናዊን ራዕይ ከግቡ ማድረስ እንደጌታዉ መዋሸትንም ያጠቃልላል?

ዘረኞቹ የወያኔ መሪዎችና አንደቤት መኪናቸዉ የሚዘዉሩት ኃ/ማሪያም ደሳለኝ በተፈጥሯቸዉ የህዝብ ጥያቄ የማይገባቸዉ ግዑዞች ሆነዉ ነዉ እንጂ የኢትዮጵያ ህዝብ ባለፉት ሃያ ሁለት አመታት መብቴንና ነጻነቴን አክብሩልኝ ብሎ የጠየቀዉ በየእሁዱ ብቻ ሳይሆን በየቀኑ ነዉ። ሆኖም ይህ ህዝባዊና ህጋዊ ጥያቄዉ ከወያኔ በኩል ያገኘዉ ምላሽ ድብደባ፤ እስር፤ ግድያና ስደት ብቻ ነዉ። ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ሚኒልክ ቤ/መንግሰት ከገባ ገና አመት ከመንፈቅ አልሞላዉም፤ ችግሩ ኢትዮጵያ ዉስጥ ሚኒልክ ቤ/መንግስት የሚገቡ ሰዎች ሁሉ የሚያስቡት በጭንቅላታቸዉ ሳይሆን በጡንቻቸዉ ነዉ፤ የኃ/ማሪያም ደሳለኝ የሰሞኑ ከቀይ መስመር በላይ መሄድ ያስቆነጥጣል የሚለዉ ማስፈራርያ የሚያሳየዉ እሱም እንደ ጌቶቹ በጡንቻዉ ማሰብ መጀመሩን ነዉ። የሚገርዉ ኃ/ማሪያም ጡንቻ ያላቸዉ ሰዎች የሚጠቀሙበት መሳሪያ ነዉ እንጂ የራሱ የሆነ ጡንቻ ያለዉ ሰዉ አይደለም። ይህ ጡንቻ ቀርቶ የራሱ የሆነ ራዕይ የሌለዉ ሰዉ በስልጣን ዘመኑ አዲስ አበባ ዉስጥ ያያቸዉ ሰላማዊ ሰልፎች አምስት አይሆኑም። እንግዲህ ይታያችሁ አመት ከመንፈቅ አገር እየመራ አምስት ሰላማዊ ሰልፎች ባልተደረጉበት ከተማ ዉስጥ ነዉ በየእሁዱ የሚደረጉት ሰላማዊ ሰልፎች ይሰለቻሉና ለማቆም እንገደዳለን ያለዉ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ግን ሃያ ሁለት አመት ሙሉ ጥያቁ በጠየቀ ቁጥር እየታሰረ፤ እየተደበደበና እየተገደለ ሰለቸኝ አላለም። ደግሞስ የተቃዉሞ ሰልፍ ማድረግ ህገ መንግስቱ የፈቀደዉ መብት ነዉ፤ የዲሞክራሲም አካል ነዉ እያለ ያቅራራዉ ኃ/ማሪያም ለመሆኑ እሱ እራሱ ማነዉና ነዉ ሰላማዊ ሰልፎችን ለማቆም እንገደዳለን ያለዉ?

ሌላዉ አንደ ሰነበተ የድሃ ድሪቶ እምቅ እምቅ የሚሸትተዉ የኃ/ማሪያም ንግግር የአገር ዉስጥ ተቃዋሚ ድርጅቶች ያነገቡት ጥያቄ የግንቦት 7 ጥያቄ ነዉ ብሎ የተናገረዉ እርባና ቢስ ንግግር ነዉ፤ ለመሆኑ ወያኔን የመሰለ ዜጎችን በየአደባባዩ የሚገድል ወንጀለኛ መንግስት ባለበት አገር የሚኖሩ ተቃዋሚ ድርጅቶች ምን ጎድሏቸዉ ነዉ የራሳቸዉ ያልሆነ ጥያቄ አንግበዉ የሚታገሉት? ኃ/ማሪያምም ሆነ ጌቶቹ የወያኔ ዘረኞች አንድ ሊረዱት የሚገባ ነገር ቢኖር ኢትዮጵያን ህዝብ በተመለከተ የአገር ቤትና የዉጭ አገር ወይም ህጋዊና ህጋዊ ያልሆኑ ተቃዋሚ ድርጅቶች የሚባል ክፍፍል የለም። ሁሉም ተቃዋሚ ድርጅቶች ጥያቄያቸዉ አንድና ተመሳሳይ ነዉ፤ እሱም የህዝብ የመብትና የነጻነት ጥያቄ ይመለስ የሚል ጥያቄ ነዉ።

የአዛኝ ቅቤ አንጓቹ ኃ/ማሪያም ኬንያ ዉስጥ የደረሰዉ የሽብር ጥቃት በኢትዮጵያ ላይ እንደደረሰ ይሰማናል ብሎ ሲናገርም ተደምጧል፤ ይህ አባባል ፖለቲካ፤ ቋንቋ፤ ዘርና ሀይማኖት ሳይለይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ እምነት ነዉ። ሆኖም የጎረቤቱ ህዝብ አደጋ ሲደርስበት ኃዘን የሚሰማዉ መሪ የራሱን አገር ህዝብ ለጦር ሜዳ በሰለጠነ ኮማንዶ አያስጨፈጭፍም። ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ለኬንያ ህዝብ መራራቱና ሀዘናቸዉን መጋራቱ መልካም ነዉ፤ ነገር ግን ባለፈዉ ሐምሌ ወር ኮፈሌ ዉስጥ በዘረኛዉ የወያኔ አገዛዝ ለተጨፈጨፉት ሃያ አምስት ሰላማዊ ኢትዮጵያዉያንስ ማን ይዘንላቸዉ፤ ማንስ ሞታችሁ ሞቴ ነዉ ይበላቸዉ? ወይስ ወያኔና ኃ/ማሪያም ደሳለኝ የሚያሳስባቸዉና የሚያሳዝናቸዉ አገር ዉስጥ እነሱ የሚጨፈጭፉት ኢትዮጵያዊ ሳይሆን ጎረቤት አገር ዉስጥ የሚሞተዉ ሰዉ ብቻ ነዉ!

ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሐይማኖት ተቋሞች የሚያነሱት ጥያቄ የፖለቲካ ጥያቄ ነዉና መንግስት የሚሰጠዉ ምላሽም የፖለቲካ ምላሽ ነዉ ብሏል። መቼም እንዲህ አይነቱ ንግግር በህዝብና በአገር ላይ የሚደረግ ሽሙጥና ስድብ ነዉ እንጂ ከአገር መሪ የሚጠበቅ አስተያየት አይደለም። ለዚህም ይመስለናል ባለፈዉ አመት መለስ ዜናዊ ሞቶ ኃ/ማሪያም ብቅ ሲል የኢትዮጵያ ህዘብ “የዘንድሮዉ ሐምሌ ምንኛ ቅጥ አጣ ተሳዳቢዉ ሲሄድ አሽሟጣጩ መጣ” ብሎ የተረተዉ። መለስ ዜናዊ ሃያ አንድ አመት ሙሉ ህዝብና አገር እንደሰደበ ተገላገልነዉ፤ አሁን ደግሞ እሱን የተካዉ ሰዉ እስከመቼ ይሆን እያሽሟጠጠ የሚኖረዉ? ደግሞስ የሐይማኖት ተቋሞች ለሚያነሱት ጥያቄ ያለን መልስ የፖለቲካ መልስ ነዉ ሲባል እየተላለፈ ያለዉ መልዕክት አናስራለን ነዉ? እንቆነጥጣለን ነዉ ወይስ እንገላለን ነዉ? ኃ/ማሪያምም ሆነ ጌቶቹ ከዚህ የተለየ መልስ ካላቸዉ ይንገሩን። እስሩ፤ ዱላዉና ግድያዉማ ድሮም የምናዉቃቸዉ የወያኔ የቀን ከቀን ድራማዎች ናቸዉ።

ወያኔ የዛሬ ሃያ አመት ሰላማዊ ዜጎችን ይገድል ነበር ዛሬም ይገድላል፤ አዲስ አበባ ዉስጥ አንዴ ቦምብ እያፈነዳ ሌላ ግዜ ደግሞ እራሱ መሬት ቆፍሮ የቀበረዉን ፈንጂ የቴሌቪዥን ካሜራዉን ደርድሮ እራሱ እያወጣዉ በተቃዋሚዎች ላይ እያሳበበ ኖሯል፤ ዛሬም ከዚህ ርካሽ ተግባሩ አልተቆጠበም። ዛሬማ ጭራሽ ኢትዮጵያ ዉስጥ ነጻነትና ዲሞክራሲ እያለ የጮኸዉን ሁሉ ግንቦት 7 ነህ እያለ እስር ቤት እየወረወረ ነዉ። ባለፈዉ አመት መለስ ዜናዊን የተካዉ ኃ/ማሪያም ደሳለኝም እንደዚሁ ነዉ። እንዳዉም ኃ/ማሪያም ሂድ ሲሉት የሚሄድ፤ ተናገር ሲሉት የሚናገር፤ ዝም በል ሲሉት ደግሞ አፉን ዘግቶ የሚቀመጥ ተንቀሳቃሽ ዕቃ ነዉ። ይህ ሰዉ በጌቶቹ እየታዘዘ ከአመታት በፊት በክልል ደረጃ በሲዳማ ህዝብ ላይ የፈጸመዉን ይህ ነዉ የማይባል በደል ዛሬ በብሔራዊ ደረጃ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ እየፈጸመ ነዉ። ኃ/ማሪያም ባለፈዉ ዐርብ መስከረም 26 ቀን በየሳምንቱ የሚደረገዉ ሰልፍ ሰለቸኝ እያለ በህዝብና በአገር ላይ አሽማጥጧል፤ ይህ ማንነታችን ያልገባዉ ሰዉ እሱና ጌቶቹ የማምለክ መብቴ ይከበር ያለዉን አክራሪ፤ መብቴና ነጻነቴ ይከበር ያለዉን ሽብርተኛ፤ ፍትህና ዲሞክራሲ ናፈቀኝ ያለዉን ደግሞ ግንቦት ሰባት ናችሁ እያሉ የሞኝ ዘፈን ሲዘፍኑ የኢትዮጵያ ህዝብ መሰልቸት ብቻ ሳይሆን ቋቅ እንዳለዉ ማወቅ አለበት። ሞኝን ሞኝ ብለን የምንጠራዉ አንድን ነገር ሺ ግዜ ስለሚደጋግም ወይም ዘፈኑ አሁንም አሁንም አበብዬ ስለሆነ ነዉ። ኃ/ማሪያም ደሳለኝ ሞኝ ብለን እንዳንጠራዉ የሚፈልግ ከሆነ ይህንን ከወያኔ መዝገብ እየተዋሰ የሚዘፍንብንን “ሁል ግዜ አበብዬ” ዘፈኑን ማቆም አለበት። አለዚያ “ከኑግ የተገኘህ ሰሊጥ አብረህ ተወቀጥ” ነዉና ግንቦት ሰባትና የኢትዮጵያ የነጻነት ኃይሎች ኃ/ማሪያምንና ዘረኞቹን የወያኔ መሪዎች ጠራርገዉ አራት ኪሎንና የሚኒልክ ቤ/መንግስትን የሚያጸዱበትን ግዜ ኃ/ማሪያም ደሳለኝ በህልሙ ሳይሆን በዉኑ ያየዋል።

Advertisements

Posted on October 12, 2013, in Andinet, Andinet party, ETHIOPIA AMHARIC, Ginbot 7, OLF. Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: