የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ አቶ አስራት ጣሴ ፍርድ ቤትን መዝለፍ በሚል ፍርድ ቤት ሊቀርቡ ነው

-ጉዳዩ ከአኬልዳማ ዶክመንተሪ ጋር የተያያዘ ነው

የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የምክር ቤት አባል አቶ አስራት ጣሴ፣ ፍርድ ቤት ፍትሕ የማይሰጥ አካል መሆኑን የሚገልጽ ዘለፋ አዘል ጽሑፍ ጽፈዋል በሚል ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲያስረዱ ትዕዛዝ ተላለፈ…

የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ዘጠነኛ ፍትሐ ብሔር ሁለተኛ የቤተሰብ ችሎት ጥር 21 ቀን 2006 ዓ.ም. ወጪ ያደረገው የትዕዛዝ ደብዳቤ እንደሚያስረዳው፣ አቶ አስራት ጣሴ በአዲስ ጉዳይ ሳምንታዊ መጽሔት ቅጽ 7 ቁጥር 198 የጥር ወር 2006 ዓ.ም. ዕትም አንድ መጣጥፍ አቅርበዋል፡፡ ‹‹… አሁን ደግሞ ከሰሞኑ ‘አኬልዳማ’ ድራማ በድጋሚ በተከታታይ እየቀረበና እየታየ ነው፡፡ ይህ እየሆነ ያለው አንድነት ፓርቲ የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትን በስም ማጥፋት ወንጀል በፍርድ ቤት ከሶ ገና ውጤት ባልተገኘበት ወቅት ነው፡፡ እሱም ፍትሕ ከኢሕአዴግ ፍርድ ቤቶች ይገኛል ተብሎ ሳይሆን፣ በታሪክ ምስክርነት እንዲመዘገብ ሲባል ነው፤›› የሚል ጽሑፍ ማቅረባቸውን ፍርድ ቤቱ በፖሊስ በኩል ለአቶ አስራት እንዲደርሳቸው ባስተላለፈው የትዕዛዝ ደብዳቤ ላይ ሰፍሯል፡፡

ፍርድ ቤቱ ከላይ በትዕዛዝ ደብዳቤው ላይ ያሰፈረውንና አቶ አስራት በአዲስ ጉዳይ መጽሔት ላይ ጽፈውታል የተባለውን ጽሑፍ ‹‹ፍርድ ቤት ፍትሕ የማይሰጥ አካል መሆኑን የሚገልጽ ዘለፋ አዘል ጽሑፍ›› ሲል ገልጾታል፡፡

በመሆኑም መዝገቡ ከመመርመሩና ማለትም አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ ከሳሽ ሆኖ የቀረበበትንና የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅትና የድርጅቱ ሠራተኛ የሆነው ጋዜጠኛ አብዲ ከማል ተከሳሾች የሆኑበት መዝገብ ከመመርመሩ በፊት፣ የአቶ አስራትን ጉዳይ ማጣራት አስፈላጊ ሆኖ ማግኘቱን አስታውቋል፡፡ በመሆኑም አቶ አስራት ጣሴ ጥር 30 ቀን 2006 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲያስረዱ በአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በኩል ደብዳቤው እንዲደርሳቸው ትዕዛዝ ተላልፏል፡፡

Posted on February 5, 2014, in Andinet, Andinet party, ETHIOPIA AMHARIC, Ginbot 7, OLF, oromo. Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a comment