‹‹ከኢትዮጵያ ጋር ከመደራደር ይልቅ ሌሎች አማራጮችን መውሰድ እንፈልጋለን›› የግብፅ የውኃ ሚኒስትር

-ግብፅ  ከኢትዮጵያ ጀርባ ቱርክ አለች ማለት ጀመረች   ባለፈው ሰኞ በአዲስ አበባ ለውይይት መጥተው ስብሰባው ተቋርጦ ወደ አገራቸው የተመለሱት የግብፅ የውኃና መስኖ ሚኒስትር መሐመድ አብዱል ሙታሊብ ካይሮ ሲደርሱ በሰጡት መግለጫ፣ ከኢትዮጵያ ጋር መደራደር እንደበቃቸው ከገለጹ በኋላ ‹‹ሌሎች አማራጮችን መውሰድ እንፈልጋለን፤›› ብለዋል…

ሚኒስትሩ በደፈናው ሌሎች አማራጮችን ከማለት ውጪ ማብራሪያ አልሰጡም፡፡ ይሁን እንጂ ንግግራቸውን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ያነበቡ ኢትዮጵያውያን ንግግሩን ፀብ አጫሪነት ነው ብለው፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን ግድቡን እንገነባለን፣ ግብፆች ያላቸው ሌላ አማራጭ ምን እንደሆነ እናያለን፤›› በማለት በቁጣ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ የመንግሥት ባለሥልጣናት ግብፅን የመጉዳት ፍላጎት የለንም እያሉ ነው፡፡ ይህንን ግን በወረቀት አስቀምጡልን ብለን ስንጠይቅ አይቀበሉም፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ በህዳሴው ግድብ ምክንያት በኢትዮጵያና በግብፅ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ለማጥበብ በግብፅ በኩል የሚደረጉ ጥረቶችን ኢትዮጵያ እያደናቀፈች ነው በማለት በአገራቸው ቴሌቪዥን ወቀሳ አቅርበዋል፡፡

ከዚህ በኋላ ውጤት ለሌለው ድርድር ጊዜ ማጥፋት ተገቢ እንዳልሆነ የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ ‹‹ሌሎች አማራጮች አሉ፣ እነርሱን ወደ መተግበር እንሸጋገራለን፤›› በማለት የአማራጮቹን ምንነት ሳያብራሩ በደፈናው አልፈዋል፡፡

በቅርቡ ኢትዮጵያን የጎበኙት የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን በተመለከተም፣ የግብፅ የውኃና መስኖ ሚኒስትር በዚሁ መግለጫቸው ላይ አስተያየት ሰጥተውበታል፡፡

 

ሚኒስትሩ አብዱል ሙታሊብ፣ ‹‹ግብፅን የማይወዱ ወገኖች ከኢትዮጵያ ግድብ ጀርባ ይገኛሉ፤›› በማለት የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የአዲስ አበባ ጉብኝትን ተችተዋል፡፡ የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአዲስ አበባ በተገኙበት ወቅት ኢትዮጵያ ለምትገነባው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ባለሙያዎችን ለመላክ ፈቃደኛ ሆነዋል ሲሉም ወቀሳ አቅርበዋል፡፡

‹‹ቱርክ፣ አታቱርክ የተባለውን ግድቧን ስትነገባ ሶሪያና ኢራቅ ተቃውሞ ነበራቸው፡፡ ቱርክ የሶሪያና የኢራቅ ተቃውሞን ቸል በማለት ሁለቱን አገሮች ለውኃ ጥም ዳርጋና ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ጥሳ ግንባታውን አከናውናለች፡፡ አፅንኦት ሰጥቼ ማለት የምፈልገው ኢትዮጵያ ቱርክ አይደለችም፡፡ ግብፅም እንደዚሁ ሶሪያ ወይም ኢራቅ አይደለችም፤›› በማለት ዛቻ መሰል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

እስካለፈው ዓርብ ምሽት ድረስ የቱርክ መንግሥት ለሚኒስትሩ አስተያየት ምላሽ አልሰጠም ነበር፡፡

የግብፅ ሚኒስትር በይፋ በአገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ የተናገሩትን ተርጉመው የዘገቡ የተለያዩ ድረ ገጾችን የተመለከቱ በርካታ ኢትዮጵያውያን፣ ‹‹ሚስተር ሙታሊብ ኢትዮጵያ አሁንም ግብፅን የመጉዳት ፍላጐት የላትም፡፡ የእርስዎ ንግግር ግን የተለመደው የግብፅ ባለሥልጣናት ድንፋታ ነው፡፡ ሌሎች አማራጮች ያሉትን እስኪ እንያቸው፡፡ ከንግግርና መግባባት የተሻለ በዚህ ጉዳይ ላይ አማራጭ የለም፤›› የሚሉ አስተያየቶችን አንፀባርቀዋል፡፡

እኚሁ የግብፅ ሚኒስትር ባለፈው ሰኞ በኢትዮጵያ ተገኝተው ከኢትዮጵያ አቻቸው አቶ አለማየሁ ተገኑ ጋር ተገናኝተው የነበረ መሆኑን፣ ሚኒስትሩ ግን የህዳሴው ግድብ ግንባታ ቆሞ እንወያይ በማለታቸው ስብሰባው መቋረጡን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

ከዚህ ስብሰባ ማግሥት ጋዜጠኞችን በመሰብሰብ በሁለቱ አገሮች መካከል ስላለው ወቅታዊ ጉዳይ በኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ማብራርያ ተሰጥቶ ነበር፡፡

በዚህ ስብሰባ ላይ ከጋዜጠኞች ከተነሱ ጥያቄዎች መካከል፣ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት በተደጋጋሚ ጦርነት በዚህ ዘመን ሊሆን አይችልም በማለት ግብፅ በአማራጭነት እንደማትመርጠው እየተናገሩ ቢገኝም፣ ጦርነት ሊፈጠር ቢችልስ ሲሉ የኢትዮጵያን አቋም ጠይቀዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጡት የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን፣ ‹‹አለመግባባቱን በጦርነት ለመፍታት ኢትዮጵያን መውረርና መቆጣጠር ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ይህ ግን መሆን አይችልም፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተው፣ ‹‹ማንኛውም አገር ጐረቤቱን ነቅነቅ ለማድረግ የሚፈልገው የጐረቤቱ እግር ወልከፍከፍ ያለ እንደሆነ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ደረጃ ግን ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ሁኔታ የለም፤›› ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያን ደኅንነት የበለጠ ለማረጋገጥ ቀዳዳዎችን መድፈን እንደሚገባ ያከሉት ሚኒስትሩ፣ ‹‹የጐረቤት አገሮችን ሰላምና ደኅንነት ማረጋገጥ፣ ከጐረቤቶቻችን ጋር ጥብቅ ቁርኝት መፍጠር፣ ለውጭ ኃይሎች ያደሩ የራሳችንን ሰዎች ነቅሶ ማውጣት፤›› ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ በመቀጠልም፣ ‹‹ጦርነት መክፈት ይቻላል ኢትዮጵያን ማሸነፍ ግን የማይቻል ነው፤›› ብለዋል፡፡

ግብፆች ኢትዮጵያን ብድር የማስከልከል እንቅስቃሴያቸውን አሁንም አጠናክረው መቀጠላቸውን የተናገሩት አቶ አለማየሁ ተገኑ በበኩላቸው፣ የህዳሴው ግድብ ግን የውጭ ኃይሎችን ዕርዳታ አይፈልግም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሪፖርተር

Advertisements

Posted on February 16, 2014, in Andinet, Andinet party, ETHIOPIA AMHARIC, Ginbot 7, OLF, oromo. Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: