ይህ ትውልድ ሞቶ የሚቀጥለው ትውልድ ይለፍለት” ቅስቀሳና መዘዙ – ፋሲል የኔአለም

በኢትዮጵያ የውጭ እርዳታ ይጎርፋል፤ በግርድፉ ከ40-50 ቢሊዮን ዶላር ባለፉት 22 አመታት ተለግሷል። ወደ 20 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብም ተበድረናል፡፡ የውጭ ኢንቨስትመንትም ይፈሳል፤ ግንባታዎችም ይካሄዳሉ..

 

Image

በእነዚህ ፈንድሻ ዜናዎች መሃከል ግን ብዙ ችግሮችም አሉ። ውሃ ፣ መብራት፣ ስኳር እና ዘይት በፈረቃ ይከፋፈላሉ፤ ትራንስፖርት ችግር ነው፤ በቀን ሶስት ጊዜ ለመብላት ጭንቅ ነው፤ ነጻነት፣ ፍትህ፣ ሰብዓዊ መብት የሚባሉት ነገሮች ከመንግስት መዝገበ-ቃላት ተሰርዘዋል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ አንድ ልዩ ባህሪ አለው። እንደሚታወቀው ልማትና ድህነት ተጻራሪ ሃይሎች ናቸው። ሁለቱ ሃይሎች በአንድ አቅጣጫ መጓዝ አይችሉም። ልማት ወደ ግራ ከሄደ ድህነት የግድ ወደ ቀኝ መጓዝ አለበት። በሃይማኖታዊ ቋንቋ ሰይጣንና መላዕክ ማለት ናቸው። አንዱ ባለበት ቦታ ሌላው ድርሽ አይልም። ይሄ ህግ ተዛብቶ “ልማትና ድህነት በአንድ ላይ ተቃቅፈው ታንጎ የሚጨፍሩበት አገር የት ነው? ” ከተባለ ያች አገር ኢትዮጵያ ናት። ልማቱ አደገ ሲባል፣ ድህነቱም በዚያው ልክ ያድጋል።

አገሪቱ ለ10 ዓመታት በ11 በመቶ እንዳደገች ከተነገረ በሁዋላ እንኳ መሰረታዊ ፍላጎቶችን ( ምግብ፣ መጠለያና ልብስ) ማሟላት ጭንቅ ሆኗል። የልማቱን ኬክ ጥቂቶች ይበሉታል፣ ብዙዎች ፍርፋሪውን እንኳ አጥተው በረሃብ ያሸልባሉ። ቀኑ ይርዘም እንጅ የባስቲሌ አመጽ በአራት ኪሎ መደገሙ አይቀሬ ነው፤ ድህነትና ልማት ተጣምረው ታንጎ በሚደንሱባቸው አገሮች ማህበራዊ ምስቅልቅል የመጨረሻው ምርት ይሆናል።

የገዚው ፓርቲ ካድሬ ኢኮኖሚስቶች “ልማቱ ጤነኛ አይደለም” ተብሎ ሲነገራቸው አይቀበሉም፤ ክርክር ሲነሳም ብዙውን ጊዜ የሚሰጡት መልስ ” የሚቀጥለው ትውልድ ያልፍለት ዘንድ ይህኛው ትውልድ መስዋትነት መክፈል አለበት” የሚል ሆኖ ይገኛል። በካድሬው አስተሳሰብ ይሄ ትውልድ ጨለማ ውስጥ ቢኖር፣ የሚቀጥለው ትውልድ መብራት እንደልቡ ያገኛል፣ ይሄ ትውልድ ውሃ ቢጠማው ፣ መጪው ትውልድ በጁስ ይራጫል፣ ይሄ ትውልድ ትራንስፖርት ቢቸግረው፣ መጪው ትውልድ በቤት መኪና ይንበሻበሻል ።

የካድሬ ኢኮኖሚስቶች ዋና አላማ ይሄ ትውልድ የመብትና የማህበራዊ ግልጋሎት ጥያቄዎችን እንዳያነሳ የተስፋ ዳቦ እየመገቡ ማዘናጋት ነው፤ አንዳንዴ የሚገነቡ መንገዶችን እያሳዩ ” የወደፊቱ ልጅህ መኪናውን የሚያሽከረክርበት ነው፣ ዘመናዊ ህንጻዎችን እያሳዩ ” የወደፊቱ ልጅህ የሚኖርበት ቤት ነው” እያሉ ያማልሉታል። ይሄ ትውልድ የውሃና የመብራት ጥያቄ ይሟላልኝ ብሎ እስካልተነሳ ድረስ የዛሬው ካድሬ ጭንቀት የለበትም፤ ለመጪው ጊዜማ የመጪው ትውልድ ካድሬ ይጨነቅበታል። “ለመሆኑ መጪው ትውልድ የሚባለው ስንተኛው ትውልድ ነው? የሚቀጥለው ትውልድ እንደሚያልፍለትስ ማረጋገጫው ምንድነው?” እንዲህ አይነት ጥያቄዎች ለካድሬ ኢኮኖሚስቶች መጠየቅ የሌለባቸው” ነውር ” ናቸው።

“ይሄ ትውልድ ለመጪው ትውልድ ሲል መስዋትነት መክፈል አለበት” የሚለውን የካድሬ ቅስቀሳ አምነው የተቀበሉ ሰዎች አጋጥመውኛል። እነዚህም ሰዎች በፊናቸው”ልማትና ዲሞክራሲ በአንድ ጀምበር አይመጣምና ታገሱ ” ሲሉ ከካድሬው የሰሙትን ስብከት መልሰው ለሌሎች ሰዎች ለማስረዳት ሲሞክሩ አይቻለሁ። እንዲህ አይነቱ ስብከት ዜጎች ለመብታቸው እንዳይነሱ በማድረግ በኩል የራሱ አስተዋጽዎ አለው። መሰረታዊ ለውጥ በአገራችን እንዲመጣ የሚፈልጉ ሃይሎች እንዲህ አይነቱን የማዘናጊያ ቅስቀሳ ፣ በእውቀት ላይ በተመሰረተ ክርክር ሊመክቱት ይገባል። በኢትዮጵያ ስላለው ልማትና ድህነት የጠራ ግንዛቤ መያዝ ለዲሞክራሲያዊ ለውጥ የሚደረገውን ትግል ያግዛልና ሁሉም አስተያየቱን ሊሰጥበት ግድ ይላል።

በቀድሞው የሲንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር ፣ ሊ ኩዋን ስም የተሰየመ “የሊ ንድፈ ሃሳብ” የሚባል በፖለቲካ ኢኮኖሚ ትምህርት ውስጥ የሚገኝ አስተሳሰብ አለ። ይህ አስተሳሰብ ዜጎችን ከብዙ ጊዜያዊ መብቶቻቸው በመገደብ ልማትን ለማምጣት የሚያልም ሲሆን፣ ዳቦን ከመብት እንዲሁም አምባገነንነትን ከዲሞክራሲ ያስቀድማል ። በዚህ አስተሳሰብ መነሻነት ኢኮኖሚያቸውን የመሩ የእስያ ነብሮች የሚባሉ አገሮች ድህነትን “ቻው” ለማለት እንደቻሉ ይነገራል ። ኢህዴግም የዚህ አስተሳሰብ ተከታይና አራማጅ ነው። አስተሳሰቡ ለብዙ አምባገነን መንግስታት የሚጥም፣ ያለ ገደብ በስልጣን ላይ ለመቆየትም እንደምክንያት ሆኖ የሚያገለግል ” ተወዳጅ” አስተሳሰብ ሆኖ ተገኝቷል- በአንባገነኖች ዘንድ። አቶ መለስም ይህን ሃሳብ መነሻ አድርገው ” ዲሞክራሲና ልማት ግንኙነት የላቸውም” የሚል የመመረቂያ ጽሁፍ መጻፋቸውን ሰምቻለሁ፣ ባላነበውም። የኖቤል ተሸላሚው አማርትያ ሴን የነጻነትና የልማት ግንኙነቶችን የሚያሳይ ውብ መጽሃፍ ባይጽፉ ኖሮ ፣ “ልማት ያለነጻነት ዋጋ የለውም” እያልን የምንጮኸውን ጩኸት ትንሽም ቢሆን የሚሰማን አናገኝም ነበር። እንደ ኢትዮጵያ ባሉ በዘር ተደራጅተው አገር ከሚመሩት መንግስታት በስተቀር ዛሬ አብዛኛው አለም፣ ነጻነት ለልማት አስፈላጊ መሆኑን ይቀበላል። የእስያ ነብሮች ያደጉት ከነጻነት በፊት ልማትን ስላስቀደሙ ነው የሚለው መከራከሪያም ብዙ አሳማኝ ሆኖ አልተገኘም፤ የእስያ ነብሮች እድገት የራሱ የሆኑ ብዙ ፖለቲካዊና ስትራቴጂካዊ ምክንያቶች አሉት። በተለይ ስለ ቀጣይ እደገት (sustainable development) ስናስብ፣ ነጻነት እጅግ አስፈላጊ ነገር መሆኑን ከአረብ አገራት አብዮትና ውድመት ተምረናል። ነጻነት ከሌለ ዘላቂና ለትውልድ የሚተላለፍ ልማት አይኖርም፤ ዛሬ የተጀመረው ልማት ነገ ለነጻነት በሚደረግ ትግል የሚወድምበት አጋጣሚ ከፍተኛ ነው። ለዚህ ደግሞ ሊቢያ፣ ሶሪያና ግብጽ ምስክሮች ናቸው። ቻይናም ቢሆን ፖለቲካዊ ለውጥ ካላደረገች እጣፋንታዋ መስቅልቅ ነው።

“ከነጻነት በፊት ልማትን እናስቀድም” የሚሉ አምባገነን መንግስታት፣ ልማት በእነሱ ብቻ እንደሚመጣና እነሱ ከሌሉ ልማቱ እንደሚደናቀፍ በማስወራት እድሜ ልክ በዙፋኑ ላይ ለመቀመጥ ያልማሉ። ይህን ህልማቸውን እውን ለማድረግም ” አሳማኝ የሚመስሉ” የኢኮኖሚ ትንተናዎችንም ያቀርባሉ። ከእነዚህ ትንተናዎች አንዱ ይህን ይመስላል ፦ “የካፒታሊዝም ስርአት ለሰዎች ኑሮ መሻሻል አስፈላጊ ነው። ስርአቱ እውን ይሆን ዘንድ ደግሞ ካፒታሊስቶችን በብዛት ማፍራት አስፈላጊ ነው። ካፒታሊስቶች ሀብት እንዲያጠራቅሙ ደግሞ ሰራተኛው የደሞዝና ሌሎች ጥቅማጥቅሞችን መጠየቅ የለበትም። ባለሀብቱ ሃብት ማጠራቀም ከቻለ፣ አዳዲስ ግንባታዎች ይካሄዳሉ፣ ብዙ ሰራተኞችም ይቀጠራሉ። እድገትም ይኖራል፣ ሁሉም ተያይዞ ያልፍለታል። መንግስትም ቢሆን የህዝቡን ፍላጎት አሟላለሁ ብሎ ባለሃብቶች ብዙ ቀረጥ እንዲከፍሉ ማስገደድ የለበትም። የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ ሲል ባለሀብቱን ብዙ ግብር ማስገበሩ አይቀርምና የህዝቡን ጥያቄ ለጊዜው ገሸሽ ያድርግ።” አስተሳሰቡ በአጭሩ “ታገሱ፣ ይህኛው ትውልድ ባያልፍለት የሚቀጥለው ትውልድ ያልፍለታል።” የሚል ነው።

በዚህ ንድፈ-ሀሳብ መሰረት የመብትና የኢኮኖሚ ጥያቄዎችን “ያለጊዜው” መጠየቅ ጎጂ ነው፤ ህዝቡ በችግር ብዛት ቢያልቅም የሚጠበቅ ነው። መንግስት የስራ ማቆም አድማዎችንና ሌሎች የመብት ጥያቄዎችን በሃይል ለመጨፍለቅ ጦሩን ቢሰብቅና ዜጎች ቢሞቱ ለካፒታሊዝም ግንባታ እስከሆነ ድረስ የተቀደሰ እርምጃ ነው። አስተሳሰቡ ኢኮኖሚውን ነጻ ፖለቲካውን እዝ የሚያደርግ፣ “ፖለቲካው ኮሚኒዝም- ኢኮኖሚው ካፒታሊዝም” ነው።

ይህን አስተሳሰብ ወደ አገራችን ነባራዊ ሁኔታ እናምጣ እንየው። “ባለሀብቱ ሀብት ያጠራቅም ዘንድ መታገስ አስፈላጊ ነው” የሚለው ምክር አሳማኝ ነው እንበል። ይሄ ትውልድ ተበድሎ የሚቀጥለው ትውልድ ይለፍለት የሚለውም አርበኝነት ነው እንበልና እንቀበለው። ነገር ግን ይህን አስተሳሰብ በአገራችን ተግባራዊ ብናደርገው የሚፈለገውን ውጤት እናመጣለን ወይ? ብለን ስንጠይቅ ፣ የምናገኘው መልስ አሉታዊ ይሆናል። እነሆ ምክንያቶቹ-

በቅድሚያ በእኛ አገር ሃብት እንዲያጠራቅሙ ስርአቱ የሚንከባከባቸው አዲስ-ሰዎች በአብዛኛው ከአንድ አካባቢ የመጡ ወይም የአንድ ብሄር አባላት ናቸው። እነሱ ሃብት እስኪያጠራቅሙ ሌላው ህዝብ እንዲሞት መፍረድ ከሞራል አኳያ ተቀባይነት አይኖረውም። እነሱ ብቻ ካፒታሊስቶች እንዲሆኑና ኢኮኖሚውን እንዲቆጣጠሩት ከፈቀድን ሌላው ህዝብ በባርነት ስር እንዲኖር እየፈረድንበት ነው። ኢኮኖሚውን እነሱ ብቻ ከተቆጣጠሩት ፖለቲካውንም መቆጣጠር አይሳናቸውም። ደቡብ አፍሪካ በኢትዮጵያችን ትመሰረታለች፤ ልዩነት ቢኖር የካፒታሊስቶቹ ቀለም ብቻ ነው።

“ግደየለም እነሱም የእኛው ሰዎች ናቸው” ብለን ብንተዋቸው እንኳ ፣ የአገር ፍቅር ስሜት አልባነታቸው ፈቅደን እንዳንገዛላቸው ያደርገናል። እነዚህ አዳዲስ ካፒታሊስቶች ገንዘባቸውን በአገር ውስጥ ባንክ አያስቀምጡም፣ ፋብሪካ ከሚገነቡ ህንጻ ቢቀጣጥሉ ይመርጣሉ፤ ህንጻ ሲሰራ እንጅ ከተጠናቀቀ በሁዋላ ብዙ ሰው አይቀጥርም። ግሎባል ፋይናንሻል ኢንቴግሪቲ 11 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ የአገሪቱ ገንዘብ በውጭ ባንኮች መቀመጡን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል። ይህ ሃብት የማን ነው? ተከድኖ ይብሰል። ነገር ግን እነዚህ ባለሃብቶች የአገር ፍቅር ስሜት እንደሌላቸው በደንብ ያሳያል።

የእኛ አዲሶቹ ባለሃብቶች ጉራና ልታይ ልታይ ማለትን ይወዳሉ። ደሃው እየደማ በሚያገኙት ገንዘብ አንድ ጠርሙስ ውስኪ እስከ 30 ሺ ብር እየገዙ ይራጬቡታል፤ ፈረንጆች እንኳ ለመያዝ የማይደፍሩትን ዘመናዊ መኪኖችን እያሽከረከሩ በሚሞትላቸው ህዝብ ላይ ይንደላቀቁበታል። ለጎራ ካልሆነ ሃመር መኪና በእግሩ በሚሄድ ህዝብ መሃል ምን ይሰራል? የሆላንድ ባለሀብት እኩል እንደ ነዋሪው ቅናሽ ሱቅ ውስጥ ገብቶ እቃ ይገዛል፣ ሚሊኒየሩን ከሌላው ህዝብ መለየት አይቻልም። የእኛን አዳዲስ ባለሀብቶች ለመለየት በጣም ቀላል ነው። እነዚህ ባለሀብቶች ናቸው የነገውን ትውልድ ያሳልፉለታል ተብሎ የሚጠበቀው።
ከሁሉም በላይ እነዚህ አዳዲስ ባለሀብቶች ገንዘብ የሚያጠራቅሙት የመንግስትን ስልጣን ይዘው እንጅ ሰርተው፣ ለፍተው፣ በእኩልና በፍትሃዊ መንገድ ተወዳድረው አይደለም። የሃብት ምንጭ የሆነውን መሬት እንደልብ እያገኙ፣ ከታክስ ነጻ እቃዎችን እያስገቡ፣ ተቀናቃኞቻቸውን በተንኮል ከገበያ እያስወጡ ነው የከበሩት።

ከእነዚህ ባለሀብቶች ውጭ ያለው ዋና ካፒታሊስት ( ባለሀብት) ደግሞ መንግስት ነው። በኢትዮጵያ እንዲያውም ዋናው ኢንቨስተር መንግስት ነው። መንግስት መሬትና ፋብሪካዎችን እየጨሸ የሚሰበስበውን ገንዘብ ከላይ ያሉት ቁንጮዎች ይመዘብሩታል። ከዝርፍያ የተረፈው ገንዘብ ለድሃው የኑሮ መደጎሚያ ይዋል ሲባልም ጦርነት ይሰበቃል። መንግስት ሃብት እስኪያጠራቅም ጥያቄዎችን ከመጠየቅ ታገሱ የሚባል ነገር ተቀባይነት የለውም ። መንግስት ሲደኸይና ዜጎች ሲበለጽጉ እንጅ ተቀራኒው ከተፈጠረ አደጋ ይኖራል።

አሁን ያሉት አዲሶቹ ባለሀብቶችም ሆኑ አሁን ያለው መንግስት የሚቀጥለውን ትውልድ ህይወት መለወጥ የሚችሉ አይደሉም። ባለሀብቶች ሃብት ሲያጠራቅሙ ለድሃው ተንጠባጥቦ ይደርሰዋል የሚለው የ trickle-down የኢኮኖሚ አስተሳሰብ ለአሁኑዋ አገራችን አይሰራም፤ ምክንያቱም ያሉን ባለሀብቶችና መንግስት በድሃው ላይ የሚዘምቱ እንጅ ለድሃው የሚቆሙ አይደሉም። ጤነኛ ካፒታሊዝም በጤነኛ ከፒታሊስቶች ይገነባል፣ ጤነኛ ካፒታሊስት ባይኖርም፣ አገር ወዳድ ካፒታሊስት ግን አለ። የእኛዎቹ፣ ከመንግስት ጀምሮ ጤነኞችም አገር ወዳዶችም አይደሉም።
ደሃው ኢትዮጵያዊ ዛሬ ለመብቱእና ለማህበራዊ አግልግሎት መሻሻል ካልተነሳ፣ ነገ በህይወትም ላይኖር ይችላል።

ስደመድመው – “የዛሬው ትውልድ ተበድሎ የነገው ትውልድ ይለፍለት” የሚለው አስተሳሰብ አሁን ባለው የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ፈጽሞ የማይሰራ ፣ ሰዎች ለነጻነታቸውና ለመብታቸው እንዳይነሱ የሚያዘናጋ እንዲሁም የአንድን በዘር ላይ የተመሰረተ ስርዓት ቀጣይ ህልውና ለማረጋገጥ ተብሎ የሚነዛ አደገኛ አስተሳሰብ በመሆኑ፣ ዜጎች በዚህ አስተሳሰብ ሳይዘናጉ ዛሬውኑ ለመብታቸው መከበር መነሳት አለባቸው- ነገን ስንጠብቅ ዛሬ እንዳንሞት እንጠንቀቅ።

Advertisements

Posted on March 26, 2014, in Andinet party, ETHIOPIA ENGLISH, Ginbot 7, OLF, oromo. Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: