ይታገሉታል እንጂ አይታደሉትም !

ቢንያም ግዛው (ኖርዌይ ኦስሎ) ይታደሉታል እንጂ አይታገሉትም ተብለን እድላችንን ስንጠብቅ ብዙ ቆየን። በርካታ ቋንቋ የሚወራባት ሀገራችን በተረትና ምሳሊያዊ ንግግር ሀብታም በመሆንዋ ብዙዎች ሀሳባቸውን በተለያየ መንገድ እየገለጹ ይግባባሉ..

አሁን አሁን ግን የማይፈቱ ህልሞች፣ ፍቺ ያልተገኘላቸው ተረቶች እና ቅኔዎች መስማት ከጀመርን ሁለት አስርት አመታት አልፈው ሦሥተኛው አጋማሽ ላይ ደርሰናል። በሀገራችን ኢትዮጵያ የሕዝብን ምላሽ የሚጠብቁ በየቀኑ ተፈብርከው ፈቺ ያጡ ብዙ እንቆቅልሾች እና ፈሊጦች ለጆሮ አታክተዋል።ወያኔ ህዝቡን እንደ ሁለተኛ ዜጋ ቆጥሮ ነዋሪው በፍርሀት እና በስጋት እንዲኖር አድርጎ አፋኝ እና ጨቋኝ ስርዐት ካነገሰበት ጊዜ አንስቶ እንኳን በቀለማችን እና በደማችን ብቻ መግባባት ይቅርና በአንድ ቋንቋ እየተነጋገርን በሁሉም ዘርፍ አለመደማመጡ እና ግርግሩ ተባብሷል። ግር ግር ለሌባ ይመቻል እንዲሉ ወያኔም በስርቆት ጉዞውእንዲዘልቅ ሰበብ ሆነለት። ስለዚህም ድህነትን አስከትሎ ከፊት ለፊት የተጋረጥውን ጭቆና ለማስወገድ በሁሉም እድሜ ክልል የሚገኝ የህብረተሰብ ክፍል የነቃ ኢትዮጵያዊ ተሳትፎው በእጅግ አስፈላጊ እንደሆነ ቢታመንም በተለይ ደግሞ የታመቀ የአዳዲስ ፈጠራ ባለቤት የሆነው ወጣቱ ትውልድ ህልሙንም ቅኔውንም የምድሪቷን እንቆቅልሽንም ለመፍታት የሚጫወተው ትልቅ ሚና አለ። ገበሬ በዘራበት መሬት ላይ ሁሉም ሰብል እኩል በቅሎ እኩል ታርሞ እኩል ታጭዶ እኩል ተውቅቶ ወደጎተራ እኩል ሲከማች እንዲሁም ከአንዱ ወገን ጠርጥረው የበሉት እሸት ከወዲያኛው ጫፍ በልምላሜ ሳይተናነስ እኩል ካሼተ ለእርሻው ባለቤት ደስታ ነው። ግና አንዱ ዝቅ ሌላው ከፍ አንዱ ለምለም ሌላው ደረቅ ሆኖ ሲታይ ልብን እንደሚያሳዝን በኢትዮጵያም በግልጥ እየተስተዋለ የመጣው ስርዐት ከዚሁ ጋር ተመሳሳይ ነው። አንዱ ያሼተበት ሌላው የደረቀበት የአድሎ ዘመን። እርግጥ ነው ፍትህ ሲጓደል አንዱ ገዝፎ ተለማኝ ሰጪ ሲሆን ሌላውም ተረግጦ ለማኝ ተቀባይ በመሆን የላቀ የሀብት ፣የጤንነት፣ የነጻነት እና የመሳሰሉት ልዩነቶች በህዝብ መካከል በጉልህ ይታያሉ። ኢትዮጵያም የዚህ ግፋዊ አገዛዝ ጽዋ ተጋቺ በመሆንዋ በህዝብ መካከል ያለውን ልክ የለሽ የኑሮ መራራቅ ምን ያህል ሀገሪቷ አደጋ ላይ እንደሆነች ያሳያል።ከሀያ አራት አመታት በፊት የነበረውን የደርግ ስርዐት ለሰፊው ህዝብ ነጻነት እታገላለሁ በማለት የአስመሳይነት ጭምብል አጥልቆ ብረት የጨበጠው ወያኔ ወደተለያዩ ከተሞች ሲገባ ታጣቂዎቹ ካደረጉት የላስትክ በረባርሶ ጫማ፣ጠባቃ የሆነች ቁምጣቸው እና ከጭንቅላታቸው ላይ የጠመጠሙት አዳፋ ጨርቅ በቀር ሌላ ነገር ነበራቸው ተብሎ ቢጠቀስ ሐሰት ነው። ግንቦት 20 .1983 ዓ.ም አዲስ አበባ በገቡበት ቀን ሳያቸው ከስለው ነበር።ተስፋ ያደረጉት የኢትዮጵያን ሀብትና ንብረት ከዚያችው ቀን ጀምሮ ቢቦጠቡጡ እንጂ ትላንት አፈር መስለው የከተሙ ሽፍቶች ሀገሪቷን በጎሳ በብሔር በባንዲራ ከፋፍለው ኢትዮጵያውያንን ለረሀብ ለስደት ቆርቋዛ አድረገው የጀመሩት ኑሮአቸው ከምን ግዜው የአክሲዮን ፣ ባለ ረጃጅም ፎቆች ፣ በተለያዩ ሀገራት ሸሽተው የተጠራቀሙ የዳጎሰ የባንክ ደብተር ባለቤት አደረጋቸው? ካልተዘረፈ በቀር እንዴት በኢትዮጵያ ምድር እነሱ ብቻ አካበቱ? ዳሩ አስቀድመው ለዚሁ ነበርና የሸፈቱት ከርሳቸውን ቢሞሉ የራዕያቸው ውጤት ነው። የኢትዮጵያም ህዝብ ከዘራፊ ስርዐት ምንም አይሻም? ከኩርንችት በለስ አይለቀምም እንደተባለ ። መልካም ዛፍ መልካም ፍሬ ያደርጋል ክፉም ዛፍ ክፉም ፍሬ አፍርቶ ስራው ይገልጠዋልና ወያኔ ምድሪቷ ላይ የነሰነሰው የእሾህ ዘር በቅሎ ህዝብን በየክልሉ እርስ በእርስ በማወጋጋት የቆሰሉት የተናቆሩት የተኳረፉት እና ደም የተቃቡት ኢትዮጵያውያን ስፍር ቁጥር የላቸውም። ለዚህም ነው ከ 1983 ዓ.ም ጀምሮ ወያኔ ከድንቁርና ጎተራው እየዘገነ በኢትዮጵያ ከርሰ ምርድ ላይ ዘርቶት የበቀለው እሾህ እና አሜኬላ ለመንቀል የተባበረ የወጣቱ ክንድ ያስፈለገው። ግፍ እና ረገጣው በቃ በሚል መንፈስ የተሞላ ወጣት በግንባር ቀደምነት በመሰለፍ የትግሉ ፋና ወጊ ለመሆን ከአባቶቹ የወረሰው ወኔ እንደገና በውስጡ ሊቀሰቀስ ይገባል። የወያኔን ፈላጭ ቆራጭነት በወጣት ክንዱ ገርስሶ ሰላም የሰፈነባት አንዲትን ሀገር ኢትዮጵያ በህዝባዊ አብዮታዊ መንግስት የመመስረት አላማን በማንገብ በሀገሪቷ ወቅታዊ ፖለቲካዊ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ በመሳሰሉት አለማቶች ውስጥ ሰርጎ በመግባት የኢትዮጵያን ደም መጣጭ ስርዐት መፋለም ያስፈለገው። ይህም መስዋዕትነት የሚጠይቅ ትግል ሀሰትን ሀሰት እውነትን ደግሞ እውነት ብሎ በህዝባዊ አመጽ የሚካሔደው ኢትዮጵያዊ ትግል ታሪክ ቸል ሳይል የሚያወሳው ገድል ነው። በዚህ አጋጣሚ ወጣቱ ሀይል በጤናማ ህሊና ኢትዮጵያን የሚያለማ ራዕይ እንዲኖረው እና አምራች እንዲሆን ሀገርን በአደራ ተቀብሎ የአንድነትና የእኩልነት አቅምን በማጠናከር አኳያ ወጣት ተኮር እንቅስቃሴዎችን የሚያደርገው የኢትዮጵያ ህዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ ወጣት ክንፍ ድርጅት (ኢህአፓ ወክንድ) ወጣቱን በማነሳሳት በማሰልጠን በማስተባበር ወቅታዊ የሀገር ጉዳዮችን አስመልክቶ ግንዛቤን በማስጨበጥ በአጽናዖት እያደረገ ያለው ከፍተኛ ጥረት እጅግ የሚደነቅ ከመሆኑም ባሻገር የወጣቶችን አቋም ዴሞክራሲያዊ ሆኖ በእውቀት የጎለበተ እና በስነ ምግባር የታነጸ ትውልድ እንዲፈጠር ራዕዩ አድርጎ፥የቀደመውን የኢትዮጵያ ታሪክ ከመጪው ጋር በማዋሐድ እንዴት ሀገሪቷ ልትለማ እንደምትችል እና ነጸነትን የተሞላ አስተዳደር ግንባታ ላይ የሚያነጣጥር መልዕክቱ በኢትዮጵያ ወጣቶች ላይ እየቀረጸብን ያለው የሀገር ፍቅር ስሜት እንዲሁም በእኩልነት ለሁሉም ክልል ያለአድሎ ክንዳችንን እንድናስተባብር ታላቅ ወኔን አጸንሦናልና የኢህአፓ ወጣት ክንፍ ድርጅት ስላደረግው እና እያደረገ ስላለው ትልቅ የሆነ ኢትዮጵያዊ ትግል ሊመሰገን ይገባል። በመላው አፍሪቃ ተስፋፍቶ የነበረው ቅኝ ግዢ በኢትዮጲያ እንዳይከሰት ወራሪውን የፋሺስት ሀይል ድል ያደረገው የተባበረው ክንድ በዘመናቸው ወጣትነታቸውን ለሀገራቸው ሉዐላዊነት ከስክሰው ነው በኛ ዘመን ቅድመ አያት የሆኑት ቀድሞ ትኩስ እና የጋለ የሀገር ፍቅር የሞላባቸው ወጣት ኢትዮጵያዊያኖች ነበሩ። የእነርሱ አንድነት እና ክንድ ጠላትን እንደጣለው አሁንም ኢትዮጵያን ነጻ ለማውጣት የትግሉ ጀማሪ እና ፈጻሚ በመሆን ቀንደኛውን ጠላት ወያኔን ታሪክ ለማድረግ መታገል ይኖርብናል።በሀገሪቷ ላይ ያለውን የጽልመት ስርዐት ቀርፎ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ የወጣቱ ተሳትፎ ትልቅ በመሆኑ ይህን ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት ሀገር አድን ትግሉን ለማጠናከር እድል አምላኪነትን ትቶ በትግል ሞት ህይወትን ለመጪው ትውልድ ዘርቶ ማለፍ የወደፊቱ ግዴታ ሆኖ ከፊቱ ተደቅኗልና ወጣቱ ቆርጦ የመታገል ሀላፊነት አለበት ። ይታገሉታል እንጂ አይታደሉትም። ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ ! እናቸንፋለን! biniamnor@gmail.com

Advertisements

Posted on March 15, 2015, in ETHIOPIA ENGLISH. Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s

%d bloggers like this: