የፖለቲካ ፓርቲዎች ለማሸነፍ ተስፋ የሚያደርጉባቸውን ሥፍራዎች አስታወቁ

ግንቦት 16 ቀን 2007 ዓ.ም. በሚካሄደው አምስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ተሳታፊ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ለማሸነፍ ተስፋ የሚያደርጉባቸውን አካባቢዎች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡  በዚህም መሠረት ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተለያዩ ሥፍራዎችን ለማሸነፍ ተስፋ እንዳደረጉባቸው የገለጹ ሲሆን፣ ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ ግን በሁሉም ሥፍራዎች ለማሸነፍ እንደሠራ አስታውቋል፡፡

የኢሕአዴግ የሕዝብና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደስታ ተስፋው፣ ‹‹በሁሉም የምርጫ ክልሎች እናሸንፋለን በሚል ነው እየሠራን ያለነው፡፡ ምርጫ ውድድር ነው፡፡ ውጤቱ የሚታወቀውም በመጨረሻ ሕዝቡ በሚሰጠው ውሳኔ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ሕዝቡ ገና ድምፁን ሳይሰጥ እዚህ አሸንፋለሁ እዚህ ደግሞ እሸነፋለሁ ማለት ትክክል አይደለም በማለት፣ ትንበያ ከምርጫ ሥነ ምግባር መርሆዎች ጋር የሚጣጣም አለመሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በዚህ ሐሳብ የሚስማሙት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ፕሬዚዳንት አቶ አበባው መሐሪ፣ ‹‹ጠንካራ ቦታዎች የሚባሉትን የሚወስነው ሕዝቡ ነው፡፡ እዚህ ላይ ነው ብለን ለማለት ያስቸግረናል፤›› ብለዋል፡፡ ነገር ግን ከክልል ከተሞች ይልቅ በአዲስ አበባ ተስፋ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል፡፡

ከዚህ በተቃራኒ ደግሞ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) የምርምር ጉዳይ ኃላፊ አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ፣ ፓርቲያቸው በሦስት የተወሰኑ ቦታዎች ላይ ተስፋ እንደሚያደርግ ገልጸዋል፡፡

በዚህም መሠረት የፓርቲው ፕሬዚዳንት የሚወዳደሩበት የዘንዘልማና የጢስ ዓባይ የምርጫ ክልል፣ ደብረ ማርቆስና ወላይታ ፓርቲው ለማሸነፍ ተስፋ የሚያደርግባቸው ሥፍራዎች መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

አዲስ አበባ በፓርቲው ከፍተኛ የቅስቀሳ ሥራ የሚሠራበት እንደሆነ የገለጹት አቶ ዋሲሁን ‹‹ነገር ግን በከተማው 11 ተቃዋሚ ፓርቲዎችና ገዢው ፓርቲ በመኖራቸው ድምፅ የመከፋፈል ዕድሉ ከፍተኛ ነው፤›› በማለት በክልል ከተሞች ያተኮሩበትን ምክንያት አብራርተዋል፡፡

አዲስ አበባ ላይ በእርግጠኝነት እንደሚያሸንፉ የገለጹት ደግሞ የሰማያዊ ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬ ሲሆኑ፣ በክልልም እንዲሁ ፓርቲው ተስፋ የሚያደርጋቸውን ከተሞች አስታውቀዋል፡፡

በዚህም መሠረት ጅማ፣ ኢሉአባቦርና የባሌ አካባቢዎች ከኦሮሚያ፣ ኮንሶና ሆሳዕና ደግሞ ከደቡብ ክልል ለማሸነፍ ተስፋ የሚያደርጉባቸው ናቸው፡፡ ከአማራ ክልል ደግሞ ባህር ዳር፣ ደብረ ማርቆስ፣ ደሴና ወልድያ ፓርቲው ጠንካራ እምነት አግኝቼባቸዋለሁ የሚላቸው ከተሞች ናቸው፡፡

‹‹ደቡብ ውስጥ በሁሉም ቦታዎች ለማሸነፍ እየሠራን የነበረ ቢሆንም፣ ባለው ሁኔታ ከፍተኛ ቅስቀሳ ማድረግ ባለመቻላችን ዕቅዳችን ሊያንስ ችሏል፤›› በማለት በደቡብ ተስፋ ያደረጉትና አሁን የሚጠብቁት የተለያዩ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

በአብዛኛው የኦሮሚያ ክልል በተወሰኑ የደቡብና የትግራይ ክልሎች የማሸነፍ ተስፋ እንዳለባቸው የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፌዴራላዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ዶ/ር መረራ ጉዲና ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት የትግራይ ክልል ርዕሰ ከተማ በሆነችው መቐለ፣ እንዲሁም ከደቡብ ከንባታና ሀድያ አካባቢዎች፣ ጋሞ ጐፋ፣ እንዲሁም ቡርጂ ዞን ውጤት የሚጠብቅባቸው ቦታዎች ናቸው፡፡

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) ፕሬዚዳንት አቶ ትዕግሥቱ አወሉ በበኩላቸው፣ በተወሰኑ የአዲስ አበባ የምርጫ ክልሎች እንዲሁም በደቡብ ሐዋሳና ዳውሮ፣ በኦሮሚያ ክልል ደግሞ በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ የኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞችና ጅማ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ተስፋ አለን ብለዋል፡፡

ዜና ምኝጭ ሪፖርተር

Posted on May 17, 2015, in ETHIOPIA ENGLISH. Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a comment