ኑ እንዋቀስ፣ የአንድ ተራ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ድምፅ (ከይኄይስ እውነቱ)

ከይኄይስ እውነቱ

ኢትዮጵያ የምትባል አገር ከምድረ ገጽ እንድትጠፋ ከደደብ (ቢት) በርሃ ስለተነሳውና መሠረቱን ትግራይ ያደረገው የደናቁርት ስብስብ ማንነት ዛሬ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የአደባባይ ምሥጢር ሆኗል፡፡ ይህ መሠሪና ዘረኛ የመንደርተኞች ቡድን ከሰውነት በታች ያዋረዳቸው ኢትዮጵያውያን በሚችሉት ሁሉ ከጥፋቱ እንዲመለስ ቢመክሩት ቢያስመክሩት ተማጽኖ ቢያደርጉለትም በእምቢተኝነቱ ፀንቷል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ በወያኔ መሪር አገዛዝ ከተያዘበት ካለፉት 25 ዓመታት ጀምሮ አሉ የሚባሉ ጸዋትወ መከራዎች ኹሉ የደረሰበት ሲሆን፣ አሁንም በዚህ የጥቂት ዘረኞች ሥርዓት የባርነት ቀንበር ሥር ይገኛል፡፡ አሁን የግፍ ጽዋው ሞልቶ እየፈሰሰ ያለበት ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡ በአንፃሩም ብሶቱ/ምሬቱ ጣራ በመንካቱና ሕዝቡም በቃኝ እምቢኝ በማለቱ ያለማንም አደራጅና አስተባባሪ በግፈኛው ወያኔ ላይ ቆርጦ ተነስቷል፡፡ መሞትን ብቻ ሳይሆን ከአውሬዎቹ ወያኔዎች ጋር የትግል ትንቅንቅ ከጀመረ ውሎ አድሯል፡፡ እኔ የዚህ አስተያየት አቅራቢ የደርግም ሆነ የዚህ ቆሻሻ ሥርዓት ሰለባ ስሆን በተለይም በወያኔ ውክቢያ፣ ዛቻና ክትትል ከሚደረግባቸው አንዱ ነኝ፡፡ በዚህ ዘረኛ ሥርዓት ምክንያት እንቅልፍ ማጣት ብቻ ሳይሆን የልዩ ልዩ በሽታዎች ተጠቂ ሆኛለሁ፡፡ የሕይወት መሥዋዕትነት እየከፈሉ ካሉ ወገኖቼ አንፃር የኔ አካላዊና አእምሮአዊ ጉዳት ግን ኢምንት ሆኖ ይሰማኛል፡፡ በደርግም ሆነ በዚህ ነውረኛና ባለጌ ሥርዓት ውስጥ የፖለቲካ ተሳትፎ የለኝም፡፡ የማናቸውም ፖለቲካ ድርጅቶች አባል አይደለሁም፡፡ እንደ አንድ ተቆርቋሪ ዜጋ ግን የአገሬ ጉዳይ እጅግ ያሳስበኛል፣ያመኛል፣ እንቅልፍ ይነሳኛል፡፡ በመሆኑም ይህን መንደርተኛ የወንበዴዎች ቡድን ከኢትዮጵያ ለማስወገድ በሚደረገው ሕዝባዊ ጥረት ውስጥ አቅሜ የፈቀደውን ከማድረግ ጀምሮ ከፋም ለማም የማምንበትን አሳብ አልፎ አልፎ ለወገኖቼ ለማካፈል እሞክራለኹ፡፡ በቅድሚያ ለወገኖቼ ግልጽ ማድረግ የምፈልገው ራሴን ከፍ ሲል ሰው ዝቅ ሲል ኢትዮጵያዊ ብቻ አድርጌ ስመለከት የኖርኩና በዚሁ እምነት ዐረፍተ ዘመኔ እስኪገታ ድረስ ለመዝለቅ ለራሴ ቃል የገባኹ ኢትዮጵያዊ ነኝ፡፡ ወያኔ ከፈቃድና ፍላጎቴ ውጭ በነዋሪነት መታወቂያዬ ላይ የለጠፈብኝ ማንነት የባሕርይው መገለጫ በመሆኑ ለኔ ትርጉም አይሰጠኝም፡፡ በዚህም ምክንያት ከባርነት ግዕዛን ወጥተን ‹‹ሰው›› ሆነን የምንኖርባት፣ ፈቃደ ሕዝብ የነገሠባት፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዜግነቱ እኩል ተጠቃሚ የሚሆንባት፣ ያለክልል አጥር በነፃነት ተንቀሳቅሶ በፈለገበት የአገራችን ግዛት ሠርቶ የሚያድርባት፣ የሕግ የበላይነት የሰፈነባት፣ አንድነቷና ግዛታዊ ሉዐላዊነቷ የተከበረ ኢትዮጵያ እውን እንድትሆን በውስጥ በአፍአ የሚደረገው ማናቸውም ዓይነት ትግል ከጎሣ አስተሳሰብ የፀዳ መሆን እንዳለበት አምናለሁ፡፡ በዚህ አስተሳሰብ ማዕቀፍ ለዛሬ ያሰብኩትን አስተያየት እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡ ዛሬ የአፍ መፍቻ ቋንቋቸውን ኦሮምኛና አማርኛ ባደረጉ ኢትዮጵያውያን ግንባር ቀደምትነት በወንበዴው አገዛዝ ላይ እየተደረገ ያለው የሞት ሽረት ተጋድሎ/መገዳደር (መነሻ ሰበባቸው የወያኔ ጎሣ ሥርዓት የፈጠራቸው በደል ምልክቶች ቢሆኑም) ጽንፈኛ የሆኑ የተቃዋሚ ፖለቲካ ማኅበራት ወይም ግለሰቦች እንደሚያናፍሱት የዚህ ወይም የዛኛው ጎሣ ትግል ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ትግል አካል ተደርጎ መታየት ይኖርበታል፡፡ አንድን ጎሣ ‹‹ነፃ›› ለማድረግ የሚደረግ ትግል ከሆነ ከወያኔ የምንሻልበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ የንጹሐን ዜጎች ደም እየፈሰሰ፣ አካል እየጎደለ ባለበት በአሁኑ ወቅት እገሌ የሚባል ጎሣ፣ ፓርቲ፣ ቡድን ወይም ግለሰብ እውቅና (ክሬዲት) የሚወስድበት ወይም ለዚህ ሽሚያ የሚያደርግበት አይደለም፡፡ ሊሆንም አይገባም፡፡ ይህንን መንፈስ ያዘሉ አስተያየቶችና መግለጫዎች ሕዝባዊ ትግሉ ከሚካሄድባቸው አካባቢዎች በቀልን ከሚሉ ግለሰቦች ወይም የተቃዋሚ ፖለቲካ ማኅበራት ተጽፎ ማንበብ እጅግ የሚያም፣ወገኖቻችን እየከፈሉ ያለውን የሕይወት መሥዋዕትነት የሚያቀል ብቻ ሳይሆን ትግሉንም የሚያዳክም ይሆናል፡፡ የምንዋጋው ኢትዮጵያን እንደ አገር እንዳትቀጥል ሌት ተቀን እየሠራ ካለ፣ አገራችንን ድውይ ካደረገ አፍራሽ ኃይል ጋር መሆኑን ለአፍታም መዘንጋት የለበትም፡፡ ውጥረቱ በሁሉም የኢትዮጵያ ማዕዝናት ነግሦ ባለበት በአሁኑ ጊዜ ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች የበኩሌን አንድ ሁለት አሳቦች (በጎና ጠቃሚ ሆኖ ከተገኘ) ለወገኖቼ ለማካፈል እወዳለኹ፡፡ በእኔ እምነት እነዚህ የእፉኝት ልጆች (ሕወሓት/ወያኔ) በኢትዮጵያ መጻኢ ዕድል ውስጥ የመፍትሔ አካል ይሆናሉ ብዬ ማሰብ ከኵርንችት በለሰን መልቀም ይሆንብኛል፡፡ 1ኛ/ ወያኔ በባሕርይው ከይቅርታ፣ ከድርድር፣ ከሰላም ጋር ኅብረት/አንድነት የሌለው መሠሪና ቀጣፊ ቡድን መሆኑ (ለጊዜያዊ ስልትና እስትንፋስ መግዣ ካልሆነ በቀር) ታውቆ በራሱም ሆነ በውጭ አሳዳሪዎቹ የሚደረግ የውይይት/የድርድር ጥያቄ እጅግ፣ እጅግ፣ እጅግ በብርቱ ጥንቃቄ መታየት ይኖርበታል፡፡ ይደረግ ቢባል እንኳን በርካታ ቅደመ ሁኔታዎች መሟላታቸውን በሚገባ ማረጋገጥ ይጠይቃል፡፡ በዚህ ረገድ ሊነሱ ከሚገባቸው አንኳር ነጥቦች መካከል፤ ሀ/ ማናቸውም ከወያኔ ጋር የሚደረግ ድርድር የሥርዓት ለውጥ ከማምጣት ያነሰ ከሆነ ትርጉም የለውም፡፡ አገራዊ አጀንዳው በጠባቡ የሚታይ፣ ለዓመፃ መነሻ የሆኑ የማንነት ወይም ወያኔ አጣብቂኝ ውስጥ ሲገባ እንደሚያጭበረብረው  ‹‹የመልካም አስተዳደር››፣ ‹‹የኪራይ ሰብሳቢነት›› ጉዳይ ብቻ አይደለም፡፡ መሠረታዊው ጭብጥ የመብትና የነፃነት፣ የሕግ የበላይነት፣ የእኩልነት፣ የፍትሐዊ ሀብት ሥርጭት፣ የአገር አንድነትና ሉዐላዊነት፣ባጠቃላይ ፈላጭ ቆራጭነትና አምባገነንነት የሰፈነበትን የዘረኞች ሥርዓት አስወግዶ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ እኩል የሆነች ኢትዮጵያን የመገንባት ጥያቄ ነው፡፡ ለ/ ድርድር ይደረግ ቢባል እንኳን የሕዝብን ጥያቄ ሳይቀንሱ እንዳለ ለማቅረብ ተአማኒነት ያላቸው፣ ለሕዝቡ ተጠያቂነትና ኃላፊነት ያላቸው የሕዝብ ወኪሎች እነማን ናቸው? የትኞቹ የተቃዋሚ ፖለቲካ ማኅበራት፣ የትኞቹ የሲቪክ ማኅበራት? የትኞቹ የሃይማኖት መሪዎች? የትኞቹ የአገር ሽማግሌዎች? የትኞቹ ምሁራን? የትኞቹ ታዋቂ ግለሰቦች? ወዘተርፈ፡፡ ይህንን ጥያቄ በቀላሉ ለመመለስ የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ሆኖም ይህ ምርጫ በየትኛውም መልኩ በወያኔ ሥርዓት ውስጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተሳትፎ ያላቸውን በተለይም ከትግራይ ነፃ አውጪ ድርጅት (ሕወሓት) ጋር አባልነት ብቻ ሳይሆን ንክኪ ያላቸው ግለሰቦችን (ቀድሞም ሆነ አሁን ያሉ ለምሳሌ፣ በሕወሓት ክፍፍል ጊዜ የተባረሩ ግለሰቦች በሙሉ፣ የሕወሓት ማኒፌስቶ መሐንዲስ የሆነው አረጋዊ በርሄና ከሱ ጋር ኢትዮጵያን ለማፍረስ መሠረት የጣሉ ግለሰቦች በሙሉ)፣ ወያኔ የፈጠራቸው የሐሰት ተቃዋሚ ‹‹ፓርቲዎች›› በሙሉ በፍጹም በፍጹም፣ በፍጹም ሕዝብን ወክለው ከወያኔ ጋር ለድርድር ሊቀርቡ አይችሉም፡፡ እነዚህ ከሕወሓት ጋር ዛሬም ሆነ ትናንት ንክኪ ያላቸውና የነበራቸው ግለሰቦች ለድርድር ብቻ ሳይሆን በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ የፖለቲካና የሲቪክ ማኅበራት ወያኔን ለማስወገድ በሚያደርጉት ኅብረት ውስጥ አንዳችም ቦታ ሊኖራቸው አይገባም፡፡ በዚህ ረገድ እነ አረጋዊ በርሄ ‹‹የሽግግር መንግሥት ይቋቋም›› በማለት በግለሰብ ደረጃ ያወጡት መግለጫ ላይ ጥብቅ ተዐቅቦ (ሪዘርቬሽን) ካላቸው ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ነኝ፡፡ ከታሪክ ደጋግመን መማር ካቃተን የዋሆች ብቻ ሳንሆን ጅሎች ነን፡፡ ይህም ሲባል እነዚህ ኢትዮጵያን የድንክዬዎች አገር ያደረጉ (የጋሼ መሥፍንን ቃል ተውሼ ነው) ጉዶችና ተባባሪዎቻቸው (በፈጸሙት ወንጀል መጠየቁ እንዳለ ሆኖ) ወደፊት በሕዝብ ፈቃድ በሚመሠረተው ሁሉን አሳታፊ ሥርዓት ውስጥ እንደ ኢትዮጵያዊ ዜጋ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት በግልም ሆነ በቡድን ተደራጅተው በኢትዮጵያ የፖለቲካ ሕይወት ውስጥ መሳተፍ መብታቸው ነው፡፡ ሐ/ ለድርድር እንደ ቅድመ ሆኔታ መቀመጥ ካለባቸው ዐበይት ጉዳዮች አንዱ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል በወያኔ አገዛዝ በፖለቲካ ምክንያት የታሠሩ ዜጎች በሙሉ ያለምንም ቅደመ ሁኔታ መፍታት፤ በወያኔ የሕዝብን መሬት መንጠቅ ‹‹ፖሊሲ›› ምክንያት ከቤት ንብረታቸው፣ ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ኢትዮጵያውያንን በሙሉ በተቻለ መጠን ወደ ቤት ንብረታቸው መመለስ፣ እንዲህ ዓይነቱን አፍራሽ ድርጊት በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል በአስቸኳይ ማቆም፤ በወየኔ ሥርዓት ላይ ሕዝባዊ ተቃውሞ እንቅስቃሴ እየተደረገባቸው ካሉ የአገሪቱ ክፍሎች ሁሉ የ‹‹ደኅንነት››፣ የ‹‹ፌዴራል ፖሊሰ›› ፣ የመከላከያ በተለይም ሕዝብን ያለምንም ርህራሄ ለመግደል ወደኋላ የማይለውን አውሬውን የአግአዚ ጦር ቡድን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ለቀው እንዲወጡ ማድረግ፤ ወዘተርፈ 2ኛ/ ወደ ኅብረት የመጣችሁ ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች እሰየው፣ አበጃችሁ፣ ማለፊያ ተግባር ፈጽማችኋል፡፡ ግን የሚዘልቅና እውነተኛ ለማድረግ አበክራችሁ ሥሩ፡፡ ሌሎችም (በሕዝብ ደም ለመነገድ ድብቅ አጀንዳ ያላችሁም ካላችሁ) ይህንን አብነት አድርጋችሁ ቢያንስ ወያኔን ለማስወገድ በጋራ ለመሥራት ኅብረትን ቀዳሚ አጀንዳችሁ አድርጉ፡፡ 3ኛ/ ሕዝብ ወያኔ ካሠማራቸው ‹አውሬዎች› ጋር ግብግብ ሲገጥም ዳር ቆማችሁ ተመልካች የሆናችሁ የ‹ተቃዋሚ ድርጅቶቸ ዓላማችሁ ምንድን ነው? በመግለጫና በወሬ፣ በይስሙላ ስብሰባ ኅብረት/አንድነት ይመጣል? በውኑ እናንተ ራሳችሁን ከተቃዋሚው ጎራ የመደባችሁ የፖለቲካ ድርጅቶች የሕዝብ ውክልና አላቸሁ ወይ? በተለይም በጎሣ የተደራጃችሁ (በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ) እና ጎሳችሁን ‹ነፃ› ለማውጣት እንታገላለን የምትሉ ድርጅቶች ከምንታገለው ወያኔ ስለመሻላችሁ ምን ዋስትና አለን? ዓላማችሁ ኢትዮጵያን እንደ አንድ ሉዐላዊት አገር ያማከለ ከሆነና በጎሣ ለመደራጀታችሁ ዐቢይ ምክንያቱ የመብት፣ የፍትሕ፣ የእኩልነት ወዘተርፈ ጥያቄ ከሆነ ቢቻል ወደ ኅብረ ብሔራዊነት፣ ቢያንስ ደግሞ አንድን ጎሣ የምትወክሉ የጎሣ ድርጅቶች ለምን አንድ አትሆኑም? 4ኛ/ መጻፍ፣ አስተያየት መስጠት መብታችሁ ቢሆንም በሌሎች መሥዋዕትነት የተደላደለ ሕይወት የምታልሙ ብቻ ሳይሆን ትግሉን በተግባር የተቀላቀሉ ኢትዮጵያውያንን እና ትግሉን የሚያስተባብሩ መሪዎችን በስንኩል አስተያየታችሁ የምታዳክሙና በነውረኛ ድርጊታችሁ በትግሉ ዙሪያ ለተሰባሰበው ሕዝብ ክብር የሌላችሁ ከወያኔ ጋር ኅብረት የለንም የምትሉ ከርሳም ወገኖች ከወያኔ ካድሬዎች በምን ትሻላላችሁ? 5ኛ/ የሕዝብስ ፍላጎት በየጎሣው በተናጥል ‹ነፃ› መውጣት ነው? ከዛ በኋላስ ተረኛ ገዢዎች ለመሆን ላሰፈሰፉ ኃይሎች ራስን አሳልፎ መስጠትና የባርነቱን አዙሪት ማስቀጠል ነው? በእጅጉ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ወያኔ በአሽከሮቹ አማካይነት ለጊዜ መግዣና ወገኖቻችንን አድብቶ ለማጥቃት በሚጠራቸው ስብሰባዎች እንዳትዘናጉ፤ እንዲሁም በተቆጣጠራቸው የብዙኃን መገናኛዎች የሚያስተላልፋቸው አፍራሽ ወሬዎች ከትግሉ እንዳያዘናጋችሁ መመካከር፣ አንዱ ለሌላው ትክክለኛ መረጃ ማስተላለፍ ተገቢ ይመስለኛል፡፡ በዘወትር ጸሎቴ አስተያየቴን እቋጫለኹ፡፡ ኢታርእየኒ ሙስናሃ ለኢትዮጵያ!!! የኢትዮጵያን ትንሣኤ ልዕልናዋን እንጂ ጥፋቷን አታሰየኝ፡፡ ልዑል አምላክ ከግለሰብ እስከ ማኅበረሰብ የኅብረት የአንድነት መንፈሱን አሳድሮብን በጎ ዘመን ለማየት ያብቃን፡ – See more at: http://ecadforum.com/Amharic/archives/16823/#sthash.HuXn4H6f.dpuf

Posted on August 19, 2016, in Andinet, Andinet party, esat.com, ETHIOPIA AMHARIC, Ginbot 7, OLF. Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a comment