«AmOr!» «አሞር!» – የአምባገነኑን የህውሀት/ወያኔን ስርአት ውድቀት የሚያፋጥን የህዝብ ድምጽ ይሆን?

ልዑልሰገድ ወልደየስ ሂርጳ

«AmOr!» «አሞር – የአምባገነኑን የህውሀት/ወያኔን ስርአት ውድቀት የሚያፋጥን የህዝብ ድምጽ ይሆን? (Could «AmOr» will be the final nail in the coffin of TPLF?)

ወደ ዋናው ርዕሴ ከመግባቴ በፊት በቅድሚያ በወያኔ ጥይት በቅርቡ በግፍ ለረገፉት የአገራችን ጀግና ወጣቶች ጥልቅ የሆነ ሀዘኔን እየገለጽኩ፤ ለቤተሰቦቻቸውና ለመላው ፍትህ፤ ዲሞክራሲና ነፃነት ናፋቂው የኢትዮጵያ ህዝብ እግዚአብሔር መጽናናቱን እንዲሰጠው ከልብ እመኛለሁ፡፡

ከዛሬ 18-19 ዓመት በፊት ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን (ነፍሳቸውን ይማረውና) በአንድ የአውሮፓ ዋና ከተማ ላይ በተደረገ ትልቅ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የተናገሩትን ምንግዜም አስታውሰዋለሁ፡፡

በዚህ ስብሰባ ላይ ብዙ የኦሮሞ፤ የአማራ፤የትግራይና እንዲሁም የኤርትራ የፖለቲካና የታሪክ ምሁራን ተገኝተው ነበር፡፡ ያውም በዚያ ትልቅ አዳራሽ ውስጥ የመጀመርያውን ረድፍ የያዙት እነዚህ ከላይ የጠቀስኳቸው (በሚያሳዝን ሁኔታ እርስ በእርሳቸው እንኳ የአግዚአብሔር ሰላምታ የማይለዋወጡትን) የታሪክና የፖለቲካ ምሁራን እንደነበሩም አስታውሳለሁ፡፡ ወቅቱም ልክ እንዳሁኑ፤ ወይም ባልሳሳት አሁን ካለው ሁኔታ ባላነሰ «ሰይጣን የፈረደበት፤ ብዙ ዱላ የሚችለው» የብሔር፤ የዘር ጭቅጭቅና የማንነት ጥያቄ ተጋኖ የሚነገርበት፡፡ በተቃራኒው «ኢትዮጵያዊነት» ደግሞ ሳይሞት ተገንዞ የመቀበርያው ጉድጓድ እየተቆፈረ ባለበት ጊዜ ነበር፡፡

የሎሬት ፀጋዬ እንደዋና ተናጋሪነት በመጋበዛቸው፤ ህዝቡም ለእሳቸው ያለው አክብሮትና ፍቅር ከፍተኛ በመሆኑና እንዲሁም እኚህ ታላቅ አገር ወዳድ ምሁር ስለምን ይናገሩ ይሆን ብሎ በማሰብ ይመስለኛል በስብሰባው ላይ ብዙ ታዳሚ ከሩቅም ከቅርብም የተገኘው፡፡ ታድያ እኚህ ታላቅ አገር ወዳድ የስነጽሑፍ የቲያትርና የታሪክ ምሁር በስብሰባው አዳራሽ ውስጥ ገብተው የተመደበላቸውን መድረክ እንደያዙ ንግግራቸውን የጀመሩት እንዲህ በሚል አንድ ጥሩ ጥያቄ ነበር፡፡ «እዚህ አዳራሽ ውስጥ የአፋር ደም በጭራሽ የለብኝም የሚል እስቲ እጁን ያውጣ!»

ሎሬት ፀጋዬ እጁን የሚያወጣ ሰው ካለ ብለው በአዳራሹ ያለውን ታዳሚ ከዳር እስከዳር እየቃኙ ለጥቂት ደቂቃ ቆዩ፡፡ አዳራሹም አንድም ሰው የሌለበት በሚመስል ሁኔታ እርጭ ብሏል፡፡ ሁሉም እርስ በርሱ ይተያያል እንጂ ደፍሮ እጁን የሚያወጣ አልነበረም፡፡(እኔ እንኳን በመጀመርያው ረድፍ ላይ ከተቀመጡት፤ የታሪክና የፖለቲካ ምሁራን መካከል ቢያንስ አንድ ሁለቱ እጃቸውን አውጥተው ሎሬት ፀጋዬን ይሞግቷቸዋል፡ እኛም የተጧጧፈ ክርክርና ትምህርት እንቀስማለን ብዬ ገምቼ ነበር – ግን እንደዚያ አልሆነም፤ ምናልባት መልሱ አጣብቂኝ ውስጥ ስለሚያስገባና ብዙም ጥናትና ውይይት ስለሚያስፈልገውም ይሆናል ምሁራኖቹ ዝምታን የመረጡት! አላውቅም)፡፡

ሎሬት ፀጋዬ በአዳራሹ ከተሰበሰበው ምንም መልስ ሲያጡ፤ ፈገግ በማለት እና በመገረም እይታ «ታድያ እዚህ ያለነው ሁላችንም አፋሮች ነን ማለት ነዋ!» ሲሉ፤ ህዝቡም በአንድ ላይ ጸጥታውን በሳቅ ቀየረው፡፡

ሎሬት ፀጋዬ ከአንድ ሰዓት ላላነስ ጊዜ በኢትዮጵያዊነትና ግንዳችን/መነሻችን ከአንድ ምንጭ እንደሆነ ብዙ ምሳሌዎችን እና የታሪክ ማስረጃዎችን እያጣቀሱ አስተማሩን፡፡ ብዙዎቹ ሀሳቦች አብዛኛዎቻችን በመደበኛው ት/ቤት ያልተማርናቸው እንደነበሩም ትዝ ይለኛል፡፡

ስለ አገራችን የተለያዩ ቋንቋዎች ከአንድ ምንጭ መፍለቅ ሳይቀር ሲያስረዱ፤ በአሁኑ ጊዜ ዝምድና የሌላቸው የሚመስሉ ቋንቋዎች ሳይቀሩ ምንጫቸው አንድ እንደነበሩ በማስረዳት፤ እንደ ምሳሌም የኦሮምኛውንና የትግርኛውን የሰላምታ አሰጣጥ በማንሳት ምን ያህል መቀራረብ እንዳለ ተንትነው እንዳስረዱ ትዝ ይለኛል፡፡ በእሳቸውም አገላለጽ የኦሮምኛው «አካም» እና የትግርኛው «ከመኤላሀ» ምንጩ አንድ እንደሆነ ሲያስረዱ፡ በእነዚህ ሁለት ቃላቶች ውስጥ አንድ የሚያገናኛቸው የጋራ ቃል አለ፡ ይሀውም «ካም» የሚለው ቃል ሲሆን፤ ትርጉሙም በጥንት በፈርዖኖች ጊዜ «ፀሀይ» ማለት እንደነበረና፤ እንግዲህ ከመነሻው ትርጉሙ « መልካም ፀሀይ» «መልካም ቀን» ከዚያም ከጊዜ ብዛት «እንደምን ዋልክ» «እንደምነህ»፤«ሰላም» ወደሚለው እንደተለወጠ በመግለጽ፤ የአገራችንም ግዛት በወቅቱ እስከ ሜደትራንያን ይደርስ እንደነበር አብራርተዋል፡፡

ለማንኛውም የሳቸው ዋና መልዕክት – «መነሻችን አንድ ነው፤ አብረን እየወደቅን፤ አብረን እየተነሳን እዚህ ደርሰናል እና መከፋፈሉን ማንጸባረቅ ትተን የሚያገናኙን ነገሮች እጅግ ብዙ ስለሆኑ፤ በፍቅር በሰላም እየተሳሰብንና እየተከባበርን በአንድነት እንኑር» ነበር፡፡

የሎሬት ፀጋዬን ትምህርትና ምክር እዚህ ላይ ላብቃና፤ ታዲያ መነሻችን አንድ ሆኖ፡ ከምንለያይበት ነገሮች ይልቅ፤ የሚያገናኘንና የሚያስተሳስረን ነገሮች እጅግ በዝቶ እያለ ለምን በተለይ በብሔር ተከፋፍለን እንናቆራለን? ብዙዎቻችን ከሶስትና ከአራት ትውልድ በፊት የነበሩትን የቅድም አያቶቻችንን ስም እንኳን በቅጡ መጥራት የምንችል አይመስለኝም፡፡ በወንድ አያቶቻችንና ቅድመ አያቶቻችንን በኩል ያሉትን ስም መጥራት ብንችል እንኳን፤ በተመሳሳይ ሁኔታ በእናቶቻችን በኩል ያለውን ስም መጥራት የምንችል ብዙም ያለን አይመስለኝም፡፡ (ባህላችን ያንን አለመደም ትሉኝ ይሆናል – እሺ እቀበለዋለሁ ግን ያ ያልተለመደ እና ያለማወቅ ከጀርባው ስንት ኮተት አንዳለበት ስለማናውቅ፤ የብሔር ጥላቻ እንዳይሰፍን ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግ አለብን)፡፡

ምን ያህሎቻችን ነን በእርግጠኛነት ከአምስትና ከስድስት ትውልድ በፊት በአያቶቻችን ዙሪያ ማን ከማን ጋር እንደተጋባ የምናውቀው? በዚያን ጊዜ የኖሩት ቅድመ አያቶቻችን የትኛዋን ሴት ለማግባት የማንን አጥር እንደዘለሉ ወይም እንዳልዘለሉ፤ የትኛውን ወንዝ እንደተሻገሩ ወይ እንዳልተሻገሩ ዛሬ እንዴት በእርግጠኝነት ማወቅ እንችላለን?

የሰው ልጅ ታሪክ የሚነግረን፤ ህዝቦች በተለያየ ምክንያቶች ሁልግዜ በእንቅስቃሴ ወይም በዝውውር ላይ መሆናቸውን ነው፡፡ የሰው ልጅ እኮ ከጥንስሱ ጀምሮ «የእንቅስቃሴ» ውጤት ነው፡፡ «እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል » እንዲሉ ህዝቦችም አንድ ቦታ ካልተመቻቸው ወደሚመቻቸው ሌላ ቦታ በመሄድ ይሰፍራሉ፤ አዲስ ከሰፈሩበትም ቦታ ካለው ህዝብ ጋር በመጋባት ይዋለዳሉ፤ የአገሩም/የአካባቢውም ሰዎች ሆነው ይቀራሉ፡፡ እንደዚህማ ባይሆን ኖሮ ዛሬ አሜሪካን የምትባል አገር ዛሬ እንደምናውቃት ባልኖረችም ነበር፡፡

ስለዚህ እኛም ስለ አገራችን ኢትዮጵያ እና በውስጧ ስለሚኖሩት የተለያዩ ብሔሮች ስናስብ፤ በሰላም፤ በፍቅርና፤ በመከባበር መኖር እንዳለብን ወይም እንደሌለብን፤ ለክርክር እንኳን መቅረብ ያለበት ጉዳይ አይመስለኝም፡፡

እኛ አሁን ያለነው በአንድ «ኢትዮጵያ» በምትባል መርከብ ላይ ተሳፍረን ካለ ምንም ካፕቴንና መሪ በአንድ ትልቅ ባህር ላይ እየተጓዝን ነው፡፡ መርከቧ ወዴት አቅጣጫ እየተጓዘች እንደሆነ አይታወቅም፤ ካፕቴንም የላትም ግን ትጓዛለች እና በመርከቧ ላይ ያለነው ተሳፋሪዎች በተለያየ ምክንያት ግሩፕ እየፈጠርን እርስ በርስ መጣላት ብንጀምር፤ ሳንወድ በግድ ከመርከቧ ላይ ወደ ባህሩ መወራወር እንጀምራለን ወይም ነገሮች በጣም ከባሱ ሁላችንም እንሰጥማለን፡፡ ስለዚህ ሁላችንም እንድንድንና መርከቧም አንድ ወደ አልታውቀ ወደብ እስክትደርስ ድረስ የግድ ተፋቅረን፤ በመከባበር መጓዝ ይኖርብናል፡፡

ጤነኛ ሀሳብ የሚያስብ ማንም ግለሰብ አብሮ በጋራ በመተሳሰብ መኖር እንዳለበት ያምናል፡፤ ይፈልጋልም፡፡ ሌላ የውጭ ግፊት ተቃራኒውን እንዲያደርግ ወይም እንዲያስብ ቢገፋፋው እንኳን የውስጥ ልቦናው ምንጊዜም የሚነግረው አብሮ ተፋቅሮ መኖር የተቀደስ፤ ጥሩና ተገቢም እንደሆነ ነው፡፡ እንደዚህማ ባይሆን ኖሮ ዛሬ የዓለም ህዝብ ቁጥር አሁን ካለው እጅግ በጣም ያንስ ነበር፡፡

በእርግጥ የሰው ልጅ በመሳሳት እና በገዢዎቹ በመታለል በግሩፕ/በብሔር ተለያይቶ ቢኖር ከሌላው ግሩፕ/ብሔር የሚያድግ፤ የሚከብርና የተሻለም ኑሮ የሚኖር ሊመስለው ይችላል፡፡ እንደዚያ ዓይነት ሁኔታ ቢፈጠር እንኳን ውጤቱ ዘለቄታ የለውም፤ በጣም ግዜያዊ ነው፡፡ (ብዙ ብሔሮች ባሉበት አገር አንድን ብሔር ወይም ክልል ብቻ ለይቶ ማልማት ቢቻልም ከሌላው ብሔር ጋር ሰላም እና ስምምነት ከሌለ የለማው ሁሉ በጥቂት ቀናት ሊፈርስ ይችላል)፡፡

ልቦናችን፤ ስብእናችን፤ ደማችን፤ ታሪካችን፤ ባህላችን፤ እምነታችን በብሔሮች እና በህዝቦች መካከል አብሮ በመከባበርና በመተሳሰብ መኖርን እየመረጠ፤ ታዲያ መናቆርን፤ ጥላቻንና ንቀትን ከሁሉም በላይ በህዝቦች መካከል የመፈራራት መንፈስ በአንድ አገር ውስጥ እንዲሰፍን የሚያደርገው ምንድን ነው? ማን ነው?

መልሱ አጭር ነው፡ ምንድን ነው ለሚለው «ከፋፍለህ ግዛ» የተባለ የገዢዎቻችን ፖሊሲ ሲሆን፤ ማን ነው ለሚለው ደግሞ መልሱ «አምባገነን ገዢዎች» ናቸው ነው፡፡

በዲሞክራሲ በሚተዳደሩ አገሮች፤ የስልጣን መሰረታቸው የህዝብ ድምጽ ስለሆነ በህዝቦች መካከል «እየከፋፈልን እንግዛ» የሚል ፖሊሲ የላቸውም፤ ሊኖራቸውም አይችልም፡፡ በነገራችን ላይ እነዚህ አገሮች ህዝባቸውን ከብዙሀኑ አደራን ተቀብለው በግልጽ ያስተዳድራሉ እንጂ «አይገዙም»፡፡

በጉልበት በሚገዙ አምባገነኖች ስር ያለች አገር ግን የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ ከጦር ኃይላቸው ባላነሰ ሁኔታ የሚተማመኑበት ስርአታቸውን ይዞ ካቆመው አንዱ ምሰሶ ነው ማለት ይቻላል፡፡

የወያኔንም ስርአት እና ስልጣን ከተሸከሙት ከአምስት ያልበለጡ ምሰሶዎች (the supporting/bearing wall)ውስጥ ይሄ የከፋፍለህ ግዛ ምሰሶ አንዱ ነው፡፡

ሌሎቹ ምሰሶዎች በአጭሩ፦

1)የጦር ኃይሉ፤ ደህንነቱና ካድሬዎቹ

2)ኤኮኖሚው-ያከማቸው የተዘረፈ ገንዘብ፤ ሀብት ንብረት የኢትዮጵያ መሬት በሙሉ

3)ድርጅቱን ከመነሻው የደገፉትና፤ አሁንም በመደገፍ ላይ ያሉ፡፡ ህልውናውን በማወቅ ወይም በመሳሳት ወይም በጥቅም ከራሳቸው ህልውና ጋር ያያያዙ ግለሰቦች፤ ህዝቦች እና የህብረተሰብ ክፍሎች፤ እንዲሁም ሆድ አደሩ

4)የአፍሪካ ቀንድ ሰላም መጥፋት እና እንደ አልሻባብ አይነት አሸባሪ መፈጠሩ በውጭ በተለይም በምዕራባውያን ዓይን የወያኔ እንደ «ዋስትና» መቆጠርም ስርአቱ በከፊልም ቢሆን የሚተማመንበት ሌላው ምሰሶ ይመስለኛል፡፡

አንድን ቤት ወይም ህንጻን ለማፍረስ የተሸከመውን ምሰሶ በግድ ማፍረስ እንደሚያስፈልገው ሁሉ፤ ስርአትንም ለማፍረስ የግድ ስርአቱን የተሸከሙትን ምሰሶዎች ማፍረስ ያስፈልጋል፡፡ የወያኔንም ምሰሶዎች ማፍረስ ካልተቻለ፤ የወያኔን ዕድሜ፤ ህዝብና ተቃዋሚዎች እንደሚመኙት ለማሳጠር አስቸጋሪ ይሆናል፡፡

አንድን ነገር ለማፍረስ በቅድሚያ በቀላሉ መፍረስ ያለበትን ነገር ጠንቅቆ ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ከላይ የተገለጹትን ምሰሶዎች በአንዴ ማፍረስ ያስቸግራል፡፡ ግን አንዱን ምሰሶ ብቻ በማፍረስ ስርአቱን ማናጋት ይቻላል፡፡ የአንድ ምሰሶ መፍረስ ስርአቱን በግድ ወደ አንድ አቅጣጫ እንዲያዘነብል (ባላንሱን እንዲያጣ)ያስደርገዋል፡፡ የአንዱ ምሰሶ መፍረስ አጠገቡ ያለውን፤ በተለያየ መዋቅር የተሳሰረውን ምሰሶ ጫና ያሳድርበትና እሱም መናድ ይጀምራል፡፡ ከዚያ በኃላ የተቀሩት ምሰሶዎች መፍረስ ለተፈጥሮ ህግ ብቻ መተው ነው፡፡

ታድያ ዛሬ ህዝባችን በከፍተኛ የወያኔ ወከባና ግድያ ላይ እያለ በቀላሉ ሊያፈርሰው የሚችለው የትኛውን ምሰሶ ነው ብለን ስንጠይቅ የምናገኘው መልስ ይሄ «የከፋፍለህ ግዛ» ምሰሶ ነው፡፡ ይሄ «የከፋፍለ ግዛ» ምሰሶ ልብ ብሎ ላጠናው ሰው፤ ከሌሎቹ ምሰሶዎች በተቃራኒ የወያኔ ስርአት ደካማ ጎን የሚጋለጥበት ነው፡፡ (the weakest link in the system) ይሄን ምሰሶ ከሌሎቹ ምሰሶዎች ጋር ስናወዳድረው፡

1)ምሰሶውን ያቆመው የውሸት ፕሮፖጋንዳና፤ ህዝቡ ዓይኑን ያለመክፈቱ መሆኑ፡

2)በቁሳዊ ንጥረ ነገር ያልታሰረ መሆኑ-ገዢዎች ከፋፍለው ለሚገዙት ህዝብ ሁሉ በገንዘብ መደለል አይቻልም፡፡ ለድለላውም የሚበቃ በቂ ገንዘብ አይኖርም፡፡

3)ምሰሶው ሙሉ በሙሉ በገዢዎቹ በወያኔ ቁጥጥር (ግቢ)ውስጥ አለመሆኑ፡

ይህና ሌሎችም ሁኔታዎች ተደማምረውና ህዝቡም ጥሩ አንቀሳቃሽ እና አስተባባሪ ከተገኘ፤ ምሰሶዎን ለማፍረስ በሚቀየሰው ስትራተጂ ላይ ጥሩ የተለያየ ታክቲክ የሚነድፍ ግብር ኃይል በመፍጠር ከታሰበው ግብ ለመድረስ የሚቻል ይመስለኛል፡፡

ሁሉም አገር ወዳድ! የኢትዮጵያን ወደ ጨለማ ጉዞ እና ወደ እርስ በርስ ግጭት ለማስቆም የሚያስብ ሁሉ የበሰለ ሀሳቡን በጨዋነት የሚለግስበትና እና ገዢዎችን በቃችሁ የሚልበት የርብርቦሽ ጊዜው እሁንና አሁን ብቻ ነው፡፡

ዋናው ትግል በሰላም እና ለሰላም መሆን እንዳለበት እንደ መሰረታዊ ሀሳብ መወሰድ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ግቡም የገዢውን ክፍል፤ ወያኔን ካለምንም ቅድመ ሁኔታ በክብ ጠረጴዛ ዙርያ ስልጣኑን ለህዝብ እንዲያስረክብ ማስደረግ መሆን አለበት፡፡ ህዝብ ጠላቱን ካላወቀ ወዳጁንም አያውቅም፡፡ የኢትዮጵያ ጠላቶች ገዢዎቹ ወያኔዎች እናወያኔዎች ብቻ ናቸው አራት ነጥብ፡፡

እነሱ የመጡበት ብሔር እነሱ ላመጡት ጣጣ ሰለባ መሆኑ እጅግ በጣም ስለሚያሳዝን፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ምን ጊዜም ወያኔንና የመጡበትን ብሔር ለይቶ ማየት አለበት፡፡ በሁለት በኩል አጣብቂኝ ውስጥ የገባውን ብሔር የሞራልና የትብብር ድጋፍ ከምንጊዜውም በበለጠ ሁኔታ በመለገስ የኢትዮጵያን ትልቅ ጨዋነት፤ ባህል፤ ታሪክ እና እምነት ምን ያህል ስር የሰደደና ከዘር ዘር ተላልፎ የመጣ መሆኑን ለዓለም ህዝብ ሁሉ ማስመስከር ያስፈልጋል፡፡

ሰዎች! ዛሬ የሚፃፈውን ብቻ ሳይሆን ነገም ምን ተብሎ ሊፃፍ ነው ብላችሁ አስቡ፡፡ ነገን የሚጽፉት ልጆቻችን ናቸው ግን ምን ብለው መጻፍ እንዳለባቸው የምንወስነው እኛ ነን፡፡

እንግዲህ በእኔ በኩል ያሰብኩትን እና በርዕሴ ላይ የገለጽኩትን፤ ለድል ሊያደርስ ይችል ይሆናል ያልኩትን «የህዝብ ድምጽ» ላካፍላችሁ፡፡

ሁላችንም እንደምናውቀው አንድን ህዝባዊ እንቅስቃሴ ግቡን እንዲመታ ወይም ቢያንስ እንዲያፋጥነው ከሚያስፈልጉት ዋና ዋና ነገሮች አንዱ በአንድ ድምጽ የሚጮህ «slogan» ወይም «የህዝብ ድምጽ» ነው፡፡

ድምጹ ጠንካራ መልዕክት ያዘለና ገዢው ክፍል በጭራሽ መስማት የማይፈልገው፤ ቃሉን ለመያዝ ቀለል ያለ፤ በወረቀትም ለመበተንም ሆነ በግድግዳ ለመጻፍ የቀለለ፤ በሶሻል ሜዲያ በቀላሉ የሚሰራጭ፤ የውስጥም ሆነ የውጭ (ጉዳዩ የማያገባው እንኳን ቢሆን -ለምሳሌ የውጭ ጋዜጠኛ በቀላሉ ሊረዳው እና ለአዳማጮቹ በቀላሉ ማስረዳት የሚችለው)፤ መልዕክቱ ሰምና ወርቅ የያዘ እና በብዙ መንገድ የሚተረጎም፤ ሰላማዊ እና የስምምነትን መልዕክት ያዘለና ብዙሀኑን ህዝብ ያካተተ ቢሆን ይመረጣል፡፡

የሶቭዬት ህብረትንና የምስራቅ አውሮፓን የኮሚንስት ጨቋኝ ስርአት ከነ ስሩ ነቅሎ የጣለው በ80 ዎቹ ላይ በፖላንድ የተነሳው «ሶሊዳርኖሽች» የሚል የህዝብ ድምጽ ነበር፡፡

«ሶሊዳርኖሽች» ማለት «ትብብር» ወይም « solidarity» ማለት ሲሆን፤ በእርግጥ «ሶሊዳርኖሽች» ክመነሻው እዚህ ግባ የማይባል በህቡዕ የተደራጀ፤ በአንድ እስክ ስምንተኛ ክፍል ደረጃ ድረስ የተማረ ኢሌክትሪሽያን የሚመራው፤ የነጻ የሰራተኛ ማህበር ነበረ፡፡ በኋላ ግን በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህዝቦች፡ ከሰራተኛው፤ከገበሬው፤ ወጣት፤ሽማግሌው፤ወንዱ ሴቱ ሁሉም በአንድ ድምጽ ወጥቶ «ሶሊዳርኖሽች» እያለ እየጮሀ «ነፃነቱን»፤«የዲሞክራሲ መብቱን» «በነጻ የመምረጥና የመደራጀት መብቱን» መጠየቅ ጀመረ፡፡ በዚህ ይህን ከባድ መልዕክት በያዘ «አንድ ቃል»፡ አገዛዙ ተሽመድምዶ ወደቀ፡፡ህዝቡም አሸነፈ!

እንዲህ አይነት ኃይለኛ መልዕክት ያለው ቃል በታሪክ ብዙ ቦታ ተስተውሏል፡፡ የፕሬዚዳንት ኦባማም «Yes we can» ን እንደ ምሳሌ መጥቀስ ይቻላል፡፡ የሚገርመው ነገር ቢኖር አንዳንዴ እንደዚህ አይነት ቃላቶች ህዝቡን ለማሰባስብና በአንድ ድምጽ ለመጮህ የሚረዱትን ያህል ከስሜት ባለፈ ትክክልኛ ትርጉማቸውን እንኳን ሁሉም ህዝብ በቅጡ አለማወቁ ነው፡፡ (አንድ የሪፓብሊካን ፓርቲ ደጋፊ የነበረ የአሜሪካን አምባሳደር፤ ፕሬዚዳንት ኦባማ ከመመረጣቸው በፊት ማን እንደሚመረጥ፤ በአንድ ለአውሮፓ ለሚገኝ ጋዜጠኛ ቃለ መጠይቅ ሲሰጥ «አይ አሁንማ ሁሉም ነገር yes we can ሆኗል፤ ባይገርምህ አሜሪካን የምትኖረውን ፤የአምስት ዓመት ዕድሜ ያላትን ልጄን ከስራ ከተመደብኩበት አገር ሆኜ ሁልጊዜ ስልክ እየደወልኩ አናግራት ነበር፡፡ አሁን በመጨረሻው የስልክ ንግግራችን ላይ፤ ስልኩን ከመዝጋቷ በፊት ፡ Daddy! Yes we can! ብላ ስልኩን ዘጋችው» «ይታይህ Yes we can እና «የፕሬዚዳንት Obama መመረጥ እኔን ከስራ እንደሚያሰናብተኝ እንኳን አልተረዳችውም ነበር» ብሎ ሲናገር ሰምቼ ነበር)፡፡

ለእኛ ኢትዮጵያውያኖችስ፤ አሁን ተቀጣጥሎ ያለውን ህዝባዊ እንቅስቃሴ እና የአንድነት ፍቅር ለመርዳት ምን አይነት «ሶሊዳርኖሽች» ወይም «Yes we can» ያስፈልግናል?

እኛ መጠቀም ያለብን «AmOr» የሚለውን የፍቅርና የኃይል ቃል መሆን አለበት እላለሁ፡፡ «AmOr» -አሞር ምን ማለት ነው? AmOr በጣም የቆየ የጥንት ቃል ሲሆን፤ ትርጉሙም «ፍቅር» ማለት ነው፡፡ (ቃሉ የመጣው ከግሪክ እንዲሁም ከላቲን የፍቅር አማልክት ከሚለው ሲሆን)፤ሀይማኖታዊ ትርጉሙ ደግሞ «መተላለፊያ» «ኮሪዶር» «Passage» እንደ ማለትም ይሆናል፡፡

ወደ እኛው አገር ደግሞ ስንመጣ የእንግሊዘኛ ቃላቱን ልብ ካላችሁት፤ «Amhara» አማራ ከሚለው የመጀመሪያውን ሁለት ፊደላት «Am» የሚለውን ወስዶ «Oromo» ከሚለውም እንዲሁ ሁለት ፊደላትን «Or» የሚለውን በመውሰድ አምላክ ሳይታሰብ ለአገራችን የገነባው ቃል ነው፡፡

«AmOr»! – አሞር በዚህ አተረጓጎም፤የአማራውና የኦሮሞው ፍቅር ማለት ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ከወያኔው «ከፋፍለህ ግዛ» በሽታ የሚድንበት መድሀኒት እና ለወያኔ ደግሞ የመሞቻው «መርዝ» ነው፡፡

«AmOr» – አሞር በሀይማኖት መጽሀፍ ደግሞ «መተላለፊያ» ነው ብዬአለሁ፤ ያም ማለት ለአገራችን ከጭቆና እና ከአምባገነን የጉልበተኛ አገዛዝ ወደ ዲሞክራሲ እና የግለስብ ነጻነት ወደሚረጋገጥበት የህዝብ አስተዳደር የምንሸጋገርበት የመተላለፊያ ኮሪዶር ማለት ነው፡፡

ቃሉ ኦሮሞና አማራን ብቻ ነው የሚወክለው ልትሉ ትችላላችህ፡፡ ግን ዋናው ትርጉሙ «ፍቅር» ማለት መሆኑን አትዘንጉ – ፍቅር በሁሉም ብሔሮችና ህዝቦች መካክል፡፡ ሌላው ደግሞ ሁለቱን ትልልቅ የኢትዮጵያ ብሔሮች መወከሉ፤ በእነሱ መካክል ያለው ፍቅር በአገሪቷ ውስጥ ለዘላቂው ለምንመኘውም ባላንሱን የጠበቀ ሰላም ይረዳል፡፡ (በአሜሪካና በረሽያ መካከል ፍቅር ከሰፈነ በመላው ዓለም ሰላም ይሰፍናል እንደማለት እንደሆነው)

የኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም የሚረጋገጠው በእነዚህ ሁለት ትልልቅ ብሔሮች መካከል ፍቅር፤ መተማመን፤ መረዳዳት እና የኃላፊነት ስሜት ሲሰፍን ነው፡፡

የኢትዮጵያ ጠላቶችና ጨቋኝ ገዢዎች ይህንን ጉዳይ ከህዝቡ የበለጠ ስለሚያውቁት በተለይ በእነዚህ ብሔሮች መካከል አለመስማማት እንዲሰፍን ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋሉ፤ እያደረጉም ነው ያሉት፤ ይሄ ደግሞ ያደባባይ ሚስጥር ነው(በኦሮሞና በአማራ ህዝቦች መካከል በቅርቡ የተፈጠረው የትግል ህብረትን አስመልክቶ «ይሄ የኛን ድክመትና የቤት ሥራችንን አለመስራታችንን ነው የሚያሳየው» በማለት የኢትዮጵያ መንግስት ቃል አቀባይ በንዴትና በቁጭት ሲዘባርቅ ተደምጧል)፡፡

እንግዲህ ሁሉም አገር ወዳድ AmOr! AmOr! AmOr! የሚለውን ቃል በየአደባባዩ ማሰማት ሲጀምር፤ የወያኔ ጠንካራ ምሰሶ የሚመስለው ቀስ በቀስ መፍረስ ይጀምራል! ያኔውኑ ሌላኛው ምሰሶ (ከአሜሪካንና ከአውሮፓ የሚመጣው የገንዘብም ሆነ የዲፕሎማሲያዊው እርዳታ)መንገዳገድና መፍረስ ይጀምራል፡፡

በመጨረሻም ለመግለጽ የምፈልገው፤ ይህ AmOr «አሞር» የሚለው ቃል የማንንም የፖለቲካ ድርጅት እንደማይወክልና፤ እኔም እንደ አንድ አገር ወዳድ፤ የወንድሞቼና የእህቶቼ ያላግባብ ደም መፍሰስ ካንገበገቡኝ አንዱ በመሆኔ፤ ቃሉን በቅርቡ በግፍ፤ ለመብትና ለነፃነታቸው ሲሉ በወያኔ ጥይት ለረገፉት ጀግና የኦሮሞና የአማራ ወጣቶች መታሰቢያ ይሁናቸው፡፡

Posted on August 29, 2016, in Andinet, Andinet party, esat.com, ETHIOPIA AMHARIC, Ginbot 7, OLF. Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: