ልፎክር ላገሬ! (ይፍሩ ኃይሉ

ይፍሩ ኃይሉ

“በፈረስ የፈለጉት፤ በዕግር ይገኛል” እንደሚሉ፤ከሃያ አምስት ዓመት በላይ፤በየኢምባሲው፤በዓለም ዙሪያ ዋና ዋና ከተማዎች፤እየዞርን፤ኧረ አለቅን! ኧረ የኢትዮጵያን ሕዝብ መከራና ስቃይ ተመልከቱን! በዕርዳታ ስም እያላችሁ፤ለገዳዮቻችን፤መትረየስ ከነጥይቱ አትስጡብን! እያልን ጉሮሮአችን እስኪነቃ ድረስ ጮኸን ያላገኘነውን፤ የዓልምን መንግሥታትና የሕዝባቸውን የሚያዳምጥ ጆሮ፤የሚመለከት ዓይን፤ጀግናው አትሌታችን፤ ፈይሣ ለሌሳ፤ብቻውን፤ሁለት እጆቹን አጣምሮ ወደላይ በማንሣት፤ ብቻ፤ዓለም ትኩር ብሎ እንዲያየው አድርጎታል። አሁን ገና፤ዕውነተኛው የአገራችን ወቅታዊ ሁኒታ፤አድማጭና ተመልካች አግኝቷል። የባለ ዝናዎቹ፤የነገረሱ ዱኪ፤የነአብዲሳ አጋ፤የነ ሙሉጌታ ቡሌ፤እንደዚሁም ስፍር ቁጥር የሌላቸው፤የናት አገርህ የኢትዮጵያ ጀግኖች፤ከመቃብር ቀና ብለው፤ ጎሽ ልጃችን! እንደዚህ ነው ጀግና!ይሉሃል። ስመጥሩው አርበኛ፤ክቡር ጀኔራል ጃጋማ ኬሎ፤ከተያዙበት የአልጋ ቁራኛ፤ ቀና ብለው፤በለሰለሰ ድምጻቸው፤ “የኢትዮጵያ አምላክ፤ ይባርክህ፤ይጠብቅህ! ሳልሞት ይህን አሳየኸኝ፤ስለዚህም ኮራሁብህ!” ይሉሃል። በሚሊዮን ከሚቆጠሩ፤ ኢትዮጵያውያን ወገኖችህ መሃል አንዱ ስለሆንኩ፤በኩራትና በደስታ ተሞልቼ፤ “ማነው ጀግና ጠፋ ያለው!” እያልኩ እኔም እፎክራለሁ።አየህ ወንድሜ! ጀግና ሲነሳ የሚከተለው መዓት ነው። ከእንግዲህ ወዲህ፤ የኢትዮጵያን አትሌቶችና ባለሙያዎች አስተሳሰብ፤ 180 ዲግሪ ለውጠኸዋል። ምሳሌ ሆነሃል። ስምህ በታሪክ ማሕደር ዉስጥ በክብር ተመዝግቧል። እኔም ባለሁበት ሆኜ ነዎር( አርካ ፉኔ) ብያለሁ።እንዲያውም ከማስታወስ ኮሮጂዬ ዉስጥ አንዲት ግጥም ይቺውልህ።Gojjam Protests

“ዳማን ፈርዳ ሙጃኛቱ፡
ያ! ፈይሣ!  አልጋን ኬሲ ሲያባቱ” ላንተ ትሁንልኝ፤ ግጥሟ ግን የሕዝብ ነች።

ለሁሉም ገደብ አለው።ከበርካታ ዓመታት መከራና ስቃይ በኋላ፤ ሲበቃ በቃ!ነውና፤የጀግናው የኦሮሞሕዝብ ቀደም ሲል ያቀጣጠለውን እሣት፤ባለታሪኩም የጎንደር ሕዝብ ጠለሱን እየተከተለ፤የወልቃይት ጠግዴ የማንነት ጥያቄ ተመርኩዞ፤በተዳፈነው እረመጥ ላይ ቤንዚን አርከፍክፎ፤የሰደድ አሣቱን ቦግ አድርጎ እንዲበራ ክብሪት ለኮሰበት። ወያኔ ተደናገጠ፤የሚይዘውና የሚጥለው ጠፋበት። ሕገ መንግሥቱን እየጠቀሰ በሕግ አምላክ፤ እያለ፤ሕግ በመጥቀስ “እርምጃ እወስዳለሁ” እያለም ማስፈራራት ጀመረ። እንዳለውም ተኩሶ ገደለ። ግን አልሠራለትም።”ጀግናው ጎንደሬ፡” እሱማ ዱሮ ቀርቶ!ያንተ ሕግ ከንግዲህ አይመለከተኝም!” አለው። ወያኔ እንደለምደው በመሣሪያ ኃይል ለማበርከክ ሞከረ፤ አሁንም ባልጠበቀው ሁኔታ፤ ተኩሱን በተኩስ መመለስ ጀመረ። የጎንደር ጀግና፤ ሲወድቅበት እሱም ወያኔን አንዱን ባንዱ ላይ መከመር ጀመረ።ሆኖ በማያውቅ ሁኔታ ወያኔ ያቺን የሰደባትንና ያዋረዳትን የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን “አማልጅኝ” አለ። ጎንደሬ ወይ ፍንክች!! የም ዕርቅ!የምን ገላጋይ አለ።

የጎንደር ሲገርመው፤ ጎጃምም “ዘራፍ!” አለና ከፍተኛ ለሰላማዊ ሰልፍ ሕዝቡን በባሕር ዳር ከተማ ጠራ።በከተማዋ እስከ ጥርሱ ድረስ የታጠቀውን የወያኔን ጦር ሳይፈራ፤ጀግናው ጎጃሜ በተባለው ቀንና ሰዓት በስፍራው ተገኝቶ ድምጹን ከፍ አርጎ፤፡የወያኔ የግፍ አገዛዝ ይብቃ!እያለ መጮህ ሲጀምር፤ የወያኔ የግል ምልምል የሆነው የአጋዚ ጦር፤ ምንም ባልታጠቀ ሰላማዊ ሕዝብ ላይ የመትረየስ ጥይት ማርከፍከፍ ጀመረ። የጎጃም ወጣቶች እንደ ቅጠል እየረግፉ ከመሬት ላይ ወደቁ።የጎጃም እናት ጥቁር ከል ለበሰች። ጀግኖች ልጆቿ ግን ለወደቁት ከማልቀስ ፈንታ፤ ለክብራቸው መፎከር ጀመሩ። ዕምቢተኛነቱን ቀጠሉበት። የወንድሞቻቸው ደም እንደጎርፍ እየወረደ፤ የአባይን ሸለቆ እየተከተለ ወደ ወለጋና ጋምቤላ ወርዶ ደሙ ከወግኖቹ ደም ጋራ ተቀላቀለ። የጀማን ወንዝ ተክትሎ፤መርሃቢቴ፤መንዝንና ግሼን አልፎ፤በወራኢሉና በጃማ በኩል ወደወሎ አሸቀበ። ወሎ ተናግቶ አካባቢውንም አናጋው።ይህ የሕዝብን አመጽ፤በአንጾኪያና በማጀቴ በኩል፤ወደ ኢፍራታና ግድም፤በካራቆሬ አዝቅዝቆ’የአጣዬን ከተማ ሰንጥቆ፤ከእነ “አትንኩኝ” አገር፤ መሃል ይፋት ደርሶ፤እነጥይት ኳሱን፤ የቀወት ልጆች፤ቀፎው እንደተነቃነቀበት ንብ ቀስቅሶ፤በጥፍሩ ቆሞ እንዲጠብቀው አድርጎታል። የየለንና የምንግሥት፤የአጋምበርና የማፍድ ነበልባሎች፤ መሣሪያቸውን ወልውለው፤ጥይታቸውን አቅባብለው፤በፍጥነት እየተቃረበ የመጣውን አደጋ፤ለዋይሎ አጋምበሮችና ለራሳ ለጆች ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል። ወያኔም፤ ከኢትዮጵያ የዘረፈውንና፤ቤተሰቡን ወደመጣበት ወደ ደደቢት የመመለሻ መንገዱ ይቺው፤ካዲስ አበባ እስከ ደሴ የተዘረጋችዋ ጠባብ  መንገድ ስለሆነች፤”አለኝ! የሚለውን ጦሩን፤ ከባድ መሣርያ አስጣጥቆ፤ከደብረ ብርሃን እስከ ደሴ ያለውን መንገድ ለመቆጣጠር ከፍተኛ ጥረት እያደረገ ነው። ሰሜን ሸዋና፤በተለይም፤ይፋቴና ወያኔ የሚፈታተኑበት ሰዓት በፍጥነት እየተቃረበ ነው። የሚያሳዝነው ይህ ጀግና ሕዝብ፤ለናት አገሩና ለክብሩ ባለው አቅም ሊቋቋማቸው ቆርጦ መነሳቱ፤የወያኔ የግፍ ቀንበር ምን ያህል ቢያንገፈግፈው ነው? የቅርብ ዘመዶቼና አብሮ አደግ ጉደኞቼ ዛሬም እዚያው ስለሆኑ፤በተቻለ መጠን ሁኔታውን ለመከታትልና ለማስረዳት ስሞክር፤ በተለይም ጠላት የመሣርያ ብልጫና የሰለጠነ ወታደር እንዳለው ለማስረዳት ስሞክር፤የሚሰጡኝ መልስ ያስገርንማል።

ኧረ ባክህ! እንኳን ክላሽ ይዘን፤ በለበስና፤በጉንዴ፤በአልቤንና በቤልጅግ እናራውጠዋለን። አይዞህ! አትፍራ፤ለኛም አታስብ። ይሉኛል። እንዲህ ሲለኝ፤የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአድዋ መልስ፡የተቀኛት ትዝ አለቺኝ።

“በሠራው ወጨፎ ባመጣው፤እርሳስ፤
ተፈጠመ ጣሊያን ካበሻ እንዳይደርስ። ወይ ጉድ “ጀግናና ጭስ መውጫ አያጣም” እንደሚባለው፤ ዛሬም የቀድሞዎቹ፤ የነዚያ ጀግኖች ዘር፤አሁንም፤ እነሱም እንደ አባቶቻቸው፤

“እኛ ምን ቸገረን ቢሰፋ ደረቱ፤
ቢደነድን ባቱ
እንቀደዋለን በገዛ ዱቢቱ።
እንኳን ቤልጅግ ይዘን፤እንኳን ጓንዴ ይዘን፤
እንገጥመዋለን ዱላችንን መዘን። እያሉ ያቅራራሉ።

ታዲያ ይህንን ልበ ሙሉ ጀግና ሕዝብ ነው፤ወያኔ በመሳሪያ እያስፈራራ በኃይል ሊገዛ የሚሞክረው! ሕግ አለ ብሎ፤ ሕግን በማክበርና በጨዋነት አብሮ ለመኖር መስሎ ቢያድር፤ ወያኔ እንደ ደካማነትና እንደ ፍርሃት ቆጠረበት። ይህን፤ቆፍጣና ጀግና ሕዝብ “ሽንታም አማራ!” ብሎ ሰደበው። ለይፋቴው “ከኔ ሌላ አንጣጥሮ ተኳሽ ላሳር ነው!” አለው። እንኳን ጠመንጃ፤ ቋራም የወይራ ዱላ እንዳይዝ ከልክሎ፤እሱ ክላሽና ኡዚ አንግቦ፤ማካሮል ሽጉጥ አገንድሮ፤ያገሬን ልጅ “ና!ይዋጣልን!” እያለ ሃያ አምስት ዓመት ሙሉ ደነፋበት። ዛሬ የኢትዮጵያ ጀግና “እምቢ አሻፎረኝ!!” ብሎ ተነስቷል። ወያኔ እንግዲህ፤”የምትወጂው ቂጣ፤ሰተት ብሎ ወጣ፡” እንደሚባለው ያ፤ “ፈጠርኩህ” እያልክ ስትደነፋበት የኖርከው ጦርነት ሳታስበው፤ ጊዜውን ጠብቆ ከተፍ ስለአለልህ። ያገሬ ጀግና፤

“አሻፎረኝ! እምቢ አሻፎረኝ!
ዋስም አልጠራ ናና ሞክረኝ!
ቀጭን የቀጭን ኩሩ!
ላይን አሳቻ በሚዛን ሙሉ!
ይምጡ ባይ! ይሰብሰቡ ባይ!
ሲሰበሰቡ እንበላቸው ባይ!

ዘራፍ የይትፋት ዉልዱ
እንደ መዳኒት ይበቃል አንዱ!
ወያኔ ታንክህን በአምባሻ ለውጠው፤
መትረየሰ፤ መድፍህን በቁልቋል ለውጠው፤
መጣን ይፋቴዎች፤ የማንደነግጠው።”

እያለ እየፍከረና እያቅራራ፤ጥይቱ ከመሬት ጠብ የማትለው ጀግና፤በተጠንቀቅ እየጠበቀህ ነው። የሚገርመው፤ ወንዱ ብቻ ሳይሆን፤ የይፋትም ቆነጃጅት፤ ዉሃም ሲቀዱ ሆነ እነጨት ሲሰብሩ፤የሚያንጎራጉሩት፤የጀግናውን ወኔ የሚቀሰቅስና፤የሚያበረታታ ነው። ከማስታውሰው በጥቂቱ ላካፍል፤

“ ጀግናው ያገሬ ልጅ የአንበሳው ግልገሉ፤
ጥይቱ ቢያልቅበት ገባው በሽመሉ።
ቆፍጣናው ይፋቴ ተኩሱ መከረኛ፤
አስቀምጦ ገዳይ እማኝና ዳኛ።
ጀግናው ያገሬ ልጅ ባለቁምጣ ሱሪ፤
ፈረሱን እንደሰው አስታጠቀው ሱሪ።

በጣም ያኮራኛል ይፋት መወለዴ፤
የሚያርሰው በቤልጅግ፤መጎልጎያው ጓንዴ፤
የሚዘራው ጥይት፤ የሚያጭደው ጎራዴ።
ጀግናው ያገሬ ልጅ ያሞራው ሲሳይ፤
ጥይቱን ወልዉሎ፤ አሰጣው ለጣይ።

ቀሚሴ ቢያልቅብኝ ተባኖ፤ ተባኖ፤
ኩታዬ ቢያልቅብኝ ተባኖ፤ ተባኖ፤
ያልብሰኝ የለምወይ ያገሬ ልጅ ፋኖ።
ገዳይ እወዳለሁ፤ ገዳይም አልጠላ
ሲደክመኝ አርፋለሁ ከጎፈሬ ጥላ።

ምነው ከሱ ጋራ አብረው ቢመንኑ፤
የድኩላ ቋንጣ ባፍ እያበነኑ።
አልፎ በዶምትፈር ካላሽቆጠቆጠው፤
አልፎ በመትረየስ ካላንቆራጠጠው፤
በነጭ ቃታ ቤልጅግ ካላንጎራደደው፤
እኔ እናቱ ነኝ ወይ ሲሸሽ የምወደው።

እያሉ ነው ወኔውን የሚቀሰቅሱት። ጀግንነቱ ከወንዶቹ ዘንድ ብቻ አይደለም።  በእሴቶቹ ይብሳል። ጀግናው ሲሞት፤ ደረቷን እየደለቀች፤ግሩም ድንቅ ሥራውን እየዘረዘረች፤ አልቅሳ ባልቴቱን የምታስለቅስ፤ጀግናው በንዴትና በቁጣ፤ ውኔው ተቀስቅሶ፤

ዘራፍ! አካኪ ዘራፍ!
ገዳይ በግንቦት፤ ሲነሳ አቧራ፤
ገዳይ በሰኔ ባባገሪማ!
ገዳይ በሐምሌ ዉሃ ሲሞላ፤
ገዳይ በጳጉሜ ዘመን ሲለወጥ፤
ለልጆቻችን ለወግ ይቀመጥ።

ጠቦ የጠቦ ጊኡእታ!
እራስ ይመታል እንድበሽታ።
ከታች ተላሚ፤
ከላይ ገጣሚ፤
የዶባ በሬ ጀርባ ገራፊ፤
አምራች ገበሬ፤ ነግዶ አትራፊ።
መልካው ሲናጋ ፎክሮ ወራጅ፤
በቤልጅግ ጥይት ኩላሊት አንዳጅ፤
ለባልጀራው ብዙ ተዋራጅ።”

እያለ፤ መሳሪያውን ይዞ እየተንጎራደደ፤ጥይት ወደ ሰማይ፤እየተኮሰ፤ ፉከራውን ሲደረድረው፤እንኳን ወንዱን ልጅ፤ ሴቷንም ይሸንጣታል። አንበሣና ነብሩን፤ጎሽና ዝሆኑን፤ከደኑ ያስበረግግርዋል። እኔ አዲስ አበባ ተምሬ አብዛኛውን ዕድሜን ከዚያ ላሳልፍ እንጂ እኔ ሁልጊዜም ልቤ ይፋት ነበር። ለገናም ሆነ ለፋሲካ፤ ትምህርት ቤት ሲዘጋ፤በዚያው ዕለት፤መርካቶ አድሬ፤የመጀመሪያውን፤የወሎ ፈረስ አውቶቡስ ይዤ ይፋት ገብቼ ነበር የማድረው። በይበልጥ ግን፤ገና ከወላጆቼ ጉያ ሳልወጣ፤ከነሱ የቀሰምኩትን ትምህርት በምንም መንገድ ልለካው አልችልም። በተለይም የኛ ቤት የንግዳ ቤት ስለነበረ፤አዋቂዎች ሲነጋገሩ፤ በመሃላቸው ገብቶ ማውራት በጭራሽ የማታሰብ ጉዳይ ነበር። አንዳንድ ጊዜ፤በተለይም የምወዳቸው ዘመዶቻችን ሲመጡ፤ተሳስቼ፤ ወይም አቅብጦኝ፤መቀባጠር ከጀመርኩኝ፤ እናቴ ከሩቅ ሆና፤በግልምጫ ብቻ፤አፈር ድቤ ታስገባኝ ነበር። ያም ካልሠራ፤በአጠገቤ የምታልፍ መስላ፤በቁንጥቻ ወይም በክርኩም አልሳኝ ትሄድ ነበር። ታዲያ ይህ በፍቅር የተሞላ ጥብቅ አስተዳደግ፤አዋቂዎች ሲያወሩ፤አፌን ከፍቼ፤ጸጥ ብሎ የዳመን ችሎታ ፈጠረልኝ። የሚገርመው፤ከዛሬ ሃምሣ ዓመት በላይ የሰማሁትን፤ታሪክ፤ክፉም ሆነ ደግ፤ከነቀኑ፤እነማን እንደነበሩ፤ስለምን ያወሩ እንደነበረ፤ በትክክል አስታዉሰዋለሁ። እንደዛሬው ሰዓት አልነበረም አእንጂ፤ በተለይ ይፋት፤ቢኖር ኖሮ፤ሰዓቱንም እንግራችሁ ነበር። የዛሬ ዓመት ወይም የዛሬ ወር የሠራሁትን አስታውስ እንዳትሉኝ!!

የማስታወስ ነገር ከተነሣ ዘንዳ፤ከቤትችን ጓሮ አንድ የወይራ ዛፍ ነበረ። ከአጠገቡም፤ ሰው የጠረበውና ያስተካከለው የሚመስል ጥቁር ድንጋይ ነበር። አባቴ ከዚያ ድንጋይ ላይ ተቀምጦ ነበር፤ብዙውን ጊዜ በአፈላም ሆነ በሌላ ምክንያት የተጣሉትን የሚያስታርቅበት፤የመስኖ ዉሃ ያሚያደላድልበት፤የአካባቢውን ጸጥታ በሚመለከት፤ ነቃ፤ ነቃ፤ ያሉትን እየመረጠ፤” በዚህ፤በዚያ ጉዳይ ላይ እናንተ ስለአላችሁበት አያሳስብኝም” ይላቸዋል። በተለይ ማታ፤ ጨረቃዋ ፈክታ በምትታይበት ወቅት፤ጎረቢቶችም፤የአካባቢውም አዛውንቶች ተሰብስበው፤ስለአለፈው ሲያወሩ፤ስለሚመጣውም ሲወያዩ፤ጸጥ ብዬ አዳምጥ ነበር። ወጋቸው አብዛኛውን ጊዜ፤ ጀግንነትና፤ ስለ ጣሊያን ጦርነት ነበር። ጦርንቱን ያካሄዱባቸው ጎራዎች፤ስማቸውም ደስ ይለኝ፣ነበር። “ የቆሎ ማርገፊያውን፤ የባሊ ደከሙን፤የወይፈን መግረፊያ ዉሎአችንን ታስታውሰምውለህ?” ይላል አንዱ። “እንዴታ!ከዚያማ፤ጣሊያን የሃማሴን ጦር አፍሦብን እንዳልነበር ያደረግንበት ቦታ አይደለም እንዴ!!ከዚያ አይደለም እንዴ ሃማሴንን አምርተነው፤ እንዳልነበር አድርገን ለቀን አሞራ፤ለሌት ጅብ የሰጠነው!! እንዴት ይረሳል ጃል!!ከዚያ በኋላ ፈረንጁ እራሱ ተግበስብሶ፤ መቶ በሮቢላና በትረጌስ ሊፈጀን ሞክሮ፤አልፈጀነም እንዴ?የፈረንጁን እሬሣ በዝሆን አንጀት ሐረግ በአንገቱ እየጎተትን ከጉድባ የዶልነው! አዬ ጊዜ ያ ቸርነት ያንለት ሲያቅራራ ያለው ትዝ ይልሃል? ምን ነበረ ያለው ተዘነጋኝ እኮ?” ይላል። ያለውማ እንዲህ ነበር፤ አይ ጓዴ!ያጉደኛ ነፍሱን ይማረው፤

የጦቢያ ልጆች ሁሉም ሆዳምን ናቸው፤
እንኳን ነጭ አግኝተው ጋሬ አይመክታቸው። ነበር ያለው።

እንዲያው ለነገሩ አማሴን ያልመከተን፤ ፍረንጅ እንዴት ያሽንፈናል ማለቱ ነበር እኮ ጃል! መቼ እዚህ ላይ ቆሞ! መጣልህ! ፈረንጅ የቦብና የጥይት ዉርጅብኝ ሊያወርድብን! ስንት ጀግና  ወደቀብን፤ ስንቱ ተማረከብን! የቀወትንና የግድምን ጀግኖች ቁም ድንጋይ ላይ በመትረጌስ ፈጃቸው። እነግራዝማች አፍራሳን ግድመፋራ መቀጣጫ አደረጋቸው። የቀበርነውን ፈረንጅ ቆፍራችሁ አውጡ ቢለን አውጥተን ሰጠነው። እሬሳውን ቢመለከት ከሁሉም አንገት ላይ የዝሆን አንጀት ሐርግ አለ። ምንድነው ይኸ? ብሎ ፈረንጁ ቢጠይቀን፤ እኛ ጀግና ሲሞት ለክብሩ በዚህ ሁኔታ ነው የምንቀብረው፤ ብንለው፤ ቦኖ! ቦኖ! ብሎ ተወው ነገሩን።”   አዬ አጅሬ! ሮቢላው ቦንቡን ሲያወርደው በዲሞትፈር አልወርድ ቢልህ ለበኔን! ለበኔን! ብለህ በረዥም ለበን ለመጣል አልምከርክም? ያንተማ ስንቱ?” እያሉ ነበር የሚያወጉት። ታዲያ ወያኔ የነዚህን፤ ነበልባል እሣት፤ልጆች ነው፤ ዛሬ “አመድ ሁኑ” የሚላቸው። የነ ደጃዝማች፤  ገረሱን፤ የጃጋማ ኬሎን፤ ጀግናውን የኦሮሞን ሕዝብ ነው፤እንደ ላም ካልነዳሁህ፤ የሚለው። የመይሣውን ዘር፤የጣይቱን ልጆች፤የጎንደርን አንበሣ ነው፤ እንደእንዝርት ላሽከርክርህ፤ የሚለው።የነበላይን፤የነ አጅሬን ጎራ ጎጃምን ነው ዳንኪራ ልርገጥብህ፤ የሚለው። የራስ ደስታን ልጆች፤ የመላው ጉራጌን ዘር ነው፤ልንቀባረርብህ፤ነግጄ ላትርፍብህ የሚለው። የጀግናውን የባልቻን ዘር፤ የሲዳማን ሕዝብ ነው፤ወያኔ ዛሬ ጦርነት ልማርብህ የሚለው። ደፋሩ ወያኔ የንጉሥ ጦናን ዘርነው ዛሬ ቁማር ልጫወትብህ፤የሚለው። በይበልጥ የሚገርመው፤የአጼ ዮሐንስን፤የአሉላ አባ፤ነጋን አገር፤የኢትዮጵያን፤ የሥልጣኔ ማሕጸን ትግራይን ነው ካልገነጠልኩ፡ የሚለው። ባለታሪኩንና ጀግናውን ጨዋውን የትግራይን ሕዝብ ነው፤ ወያኔ፤ከወገኑ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ደም ሊያቃባው የሚፈልገው። የአሊ ሚራን ዘር፤ ጀግናውን ያአፋርን ሕዝብ ነው፤ በራስህ ላይ ተቀምጬ ልቦርቅብህ የሚለው። ይገርመናል! በጣም ይገርመናል!! ኧረ ተው ወያኔ!ነካክተህ፤ነካክተህ፤ደሜን አታፍላው። አንድ ምክር ልስጥህና ለዛሬው ከዚህ ላይ ዓይን ለዓይን፤ ለመተያየት ያብቃን ልበልህና።የምትከተለዋን ግጥም ልጋብዝህ።

ተው ተመለስ የወያኔ በሬ፤የአጋዚ በሬ፤
ከጠመደ አይፈታም የኢትዮጵያ ገበሬ።
እንዴት ታርሰዋለህ የመተማን መሬት፤
ኧረ እንዴት፤ኧረ እንዴት፤
እንደ ግልገል ፈረስ ሳንፈተንበት።
ቸር ይግጠመን ጎበዝ፤ሳምንት ጣርማበር እንገናኝ።

ኢትዮጵያ በነጻነቷ ለዘለዓለም ትኑር!

በጀግኖች ልጆቿ ደም፤በክብር ዙፋኗ ላይ ኮርታ ትቀመጣለች።

ይፍሩ ኃይሉ

– See more at: http://ecadforum.com/Amharic/archives/16855/#sthash.UWFeu66p.dpuf

Posted on August 30, 2016, in Andinet, Andinet party, esat.com, ETHIOPIA AMHARIC, Ginbot 7, OLF. Bookmark the permalink. Leave a comment.

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google photo

You are commenting using your Google account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

Connecting to %s

%d bloggers like this: